ከ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በፊት የነበረውን ሕይወቱን የሚያውቁት ሰዎች እጅግ በኑሮው ቄንጠኛ እንደነበር ይመሰክሩለታል፤ ነግር ግን ከዚያ በኋላ ብዙዎች የሚያውቁት ለአለባበሱ የማይጨነቀውን፣ ሕይወትን ቀለል አድርጎ የሚኖራትን ፣ ራሱን ሆኖ የኖረውን የሁሉም የትንሽ የትልቁ ሁሉ ጓዳኛ የሆነውን…ብዙ አድናቂዎችን ያፈራውን፣ መምህር፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ አርታኢ፣ ፈላስፋ፣ አንባቢውን ጋሽ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔርን እነሆ ለዚህ ሳምንት የየኛ ገፅ እንግዳ አድርገነዋል አብራችሁን ቆዩ።
ስብሃት በ66ኛ ዓመት ልደቱ ዋዜማ ላይ ጋዜጠኛ ደረጀ ስብሃትን፡-
“የዛሬ 66 ዓመት የት ነበርክ? “ ሲል ጠየቀው።
“አሃ..” አለ፣ ልክ ሲወለድ የነበረውን አስታውሶ የሚናገር ያህል “እሪባ ገረድ ትባላለች። አድዋ አውራጃ ውስጥ ያለች መንደር ናት፤ የገጠር መንደር ውስጥ ነው የተወለድኩት ። የገረድ ወንዝ ማለት ነው።” በማለት አስረዳ። ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ላይ የተወለደው ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ከአባቱ ከቄስ ገብረ እግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከእናቱ ከወይዘሮ መአዛ ወልደ መድኅን ተወለደ።
“ሚያዚያ 27 ቀን ከአንተ ጋት የተወለዱ እነማንን ታውቃለህ?”
“ብዙ ናቸው! ከእነርሱ መካከል ሲግመንድ ፍሩድ፣ አዶልፍ ሂትለር እና ስብሃት ገብረ እግዚአብሄርም ናቸው” አለው።
እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብት ጠብቆ እንዳደገ ይህንም እንደሚደሰትበት ታሪኩ ላይ ተፅፏል። ለቤተሰቡ 7ኛ ልጅ የሆነው ስብሃት ልጆቻቸውን በማይጋረፉ ወላጆች መሃል በደስተኛነት ነው ያደገው። ደስተኛ አስተዳደግ ይኑረው እንጂ ቤተሰቡ ግን በጣም ደሃ ስለነበሩ እያንዳንዱ ልጅ ሕይወትን ለመቋቋም ለቤተሰቡ የየራሱን ድርሻ ለመወጣት ገና ከልጅነት ጀምሮ መስራት ነበረበት።
ስብሃት የ9 ዓመት ብላቴና ሳለ አባቱ ከሚያስተምሩበት ለስ ትምህርት ቤት በአንድ አመት ውስጥ ግእዝ ማንበብ ችሎ እንደወጣ በታሪኩ ውስጥ ተፅፎ ይገኛል። አስር አመቱ ላይ በታላቅ ወንድሙ እገዛ አማካይነት ወደ አዲስ አበባ መጣ። በዚያም ትምህርቱን በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል ተምሮ በቀጣይ አመት ሁለተኛ ክፍልን መማር ሳይጠበቅበት ወደ ሦስተኛ ክፍል ተዛውሮ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተማረ። በአብዛኛው የትምህርት አይነቶች ጥሩ ውጤት የነበረው ስብሃት በእንግሊዝኛ ክህሎቱ ጎበዝ ስለነበር ገና የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የትምህርት ቤቱ መፅሄት አርታኢ ሆኖ ነበር። ትምህርት ቤቱ ያዘጋጃቸው በነበሩ ተውኔቶች ይሳተፍም ነበር።
አስራ ሁለተኛ ክፍልን ሲያጠናቅቅ ደህና ውጤት ስለነበረው ወዲያውኑ በ1952 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትሎ በትምህርት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። በኮሌጅ ቆይታው ደስተኛ እንደነበር የሚናገረው ስብሃት በርካታ መፃህፍትንም የማንበብ እድል አስገኝቶለታል። ዶስቶቪስኪ፣ ሳመረስት ማሆጋን፣ ለላ ማዎፓሳንት፣ ቼኮቭ እና ሌዊስ ካሮል የጿፏቸውን አጫጭር ልቦለዶች እና ኖቭሎችን ማንበብ ያስደስተው ነበር። በኮሌጅ ቆይታው ከእነ ተስፋየ ገሰሰ እና ሰሎሞን ደሬሳ ጥብቅ ጓደኝነት ነበረው። አብረው ያነቡ ነበር። አብረው ውቤ በርሃ እየሄዱም ስለተለያዩ ነገሮች ሲወያዩ ይውሉ እንደነበር የስብሃት ታሪክ በተካተተበት ብላክበርን ላይንስ መፅሀፍ ላይ ተፅፎ ይገኛል።
ጋሽ ስብሃት ኮሌጅ ተምሮ ከተመረቀ በኋላ በአንድ ትምርት ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛ መምህር ሆኖ ለስምንት ወራት ያህል እንደሰራ የውጭ የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ ሄደ። 1953 ዓ.ም ላይ መሆኑ ነው። በአሜሪካ እንዲማር የተፈቀደለት የቤተ መጽሃፍት ሳይንስ ትምህርት ነበር፤ ነገር ግን ስብሃት ይህን አልፈለገውም፤ ሌላ ዘርፍ እንዲቀይሩለት ጠይቆ አልተፈቀደለትም፤ ስለዚህ ክፍል አይገባም ነበር:: መጨረሻ ላይ የሚፈልገውን ትምህርት ቢፈቀድለትም ሳይጨርስ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
በአስፋ ወሰን ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት ለ2 ዓመት አገልግሏል። በመቀጠልም ከየተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ ሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ባገኘው የትምህርት እድል አማካይነት ወደ ፈረንሳይ በመሄድ ከ1962-1964 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል።
ወደ ፈረንሳይኛ «Les Nuits d’Addis-Abeba» ተብሎ በፍራንሲስ ፋልሴቶ የተተረጎመውን የልብ-ወለድ ድርሰቱን “ሌቱም አይነጋልኝ”ን ብዙውን ለመጻፍ የበቃው እዚያው በፈረንሳይ እንደሆነም ይናገራል። ይኸው ድርሰቱም ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ የተተረጎመ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልብ-ወለድ ነው።
ሌቱም አይነጋልኝ በውቤ በረሃ በ1957 ዓ.ም. ተጀምሮ በፈረንሳይ አገር ኤክስ አን ፕሮቫንስ የተፈጸመ መጽሐፍ ነው። ደራሲው ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር መጽሐፉ እንዲታተም እሱ ደንታ ባይኖረውም በመጽሐፉ ውስጥ እንደጠቀሰው «እኔ ‘ኮ ያደረብኝ ለዘብተኛ ልዝብ ዛር በበቂ ደሞዝና ‘ትርፍ’ ስዓት እያምበሻበሸ ስላበረታታኝ ፃፍኩ እንጂ ይታተም አይታተም ደንታ አልነበረኝም።»
ወዳጆቹ ቢሞክሩም በመንግስት ሳንሱር «ለአንባቢያን የማይገቡ ግልጽ የወሲብ ቃላቶች አሉበት» በሚል ምክንያት እየታገደ ለሃያ አምስት ዓመታት በአንባቢዎቹ እጆች በእጅ እየተገለበጠ ሲነበብ ኖሯል።
በአሁኑ ሰዓት በመጀመሪያ እነዚያ ወሲባዊ ቃላቶችን «ለስለስ» ባሉ ቃላት በመተካት ለአንባቢያን እንዲደርስ መጽሐፉ ታትሞ ለገበያ የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም በአገራችን አቆጣጠር በ1999 ያንኑ መጽሐፍ ደራሲው የተጠቀመባቸውን ቃላት ትክክለኛ ግልባጭ የያዘ “ሌቱም አይነጋልኝ… እንደ ወረደ” ለአንባቢያን ቀርቧል።
ስብሐትም እዚሁ ዕትም ላይ «እንግዲህ አንባብያን ሆይ! በገዛ ታሪኬ፣ በገዛ ሦስት ሺ ዘመን ያገሬ ክርስትና፤ በገዛ ውቤ በረሀዬ፤ የኖርኩትን፣ ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ በተቻለኝ አቅምና በታደልኩት የትረካ ተሰጥዎ ለአራዳዎችም ለፋራዎችም ያገሬ ልጆች (ያውም ከሊቅ እስከ ደቂቅ!) ለምን አላበረክትላቸውም? አራዳዎቹም አብረውኝ ደስ ይላቸዋል፤ ፋራዎቹም ድብርታቸው ይብስባቸውና አንጀቴ ቅቤ ይጠጣል፤ ቀኑ የፆም ቢሆንም፤ እና እኔ የቄስ ልጅ፤ የደብተራ የልጅ ልጅ በመሆኔ የምኮራ ብሆንም። ያውም መብቴ በህገ መንግስት እየተጠበቀልኝ! ለሁላችሁም እንሆ በረከት!» እያለ ይኼንን የሚይስቅ፤ የሚያዝናና እና የ’ውቤ በርሀን’ የ1950ዎቹ ታሪክ ‘የሚያስተምረን’ መጽሐፍ አቅርቦልናል።
ስብሃት ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በመነን መፅሄት የዝግጅት ክፍል ውስጥ ሰርቷል። በ1966 ዓ.ም. ወታደራዊው ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲቋቋም በአርታኢነት ተቀጥሮ ሰርቷል። በመንግሥት ትእዛዝም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን የካርል ማርክስ ሥራ የሆነውን ካፒታልን (Das Capital) ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመመለስ ሥራ ላይ ተሳትፏል።
ብዙዎቹ የስብሃት ሥራዎች በተጻፉበት ጊዜ ለመታተም ባይታደሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የህትመትን ብርሃን ለማየት በቅተዋል። ጽሁፎቹ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይታተሙ ለመቆየታቸው ዋነኛው ምክንያቱ ስብሃት በመጽሐፉ የሚጠቀማቸው ቃላት ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ባህል ያደገ አንባቢን አይን የሚያስፈጥጡ፣ ጆሮ የሚያስይዙ በመሆናቸው ነው። በገበያ ላይ በቅርብ የወጡት ድርሰቶቹ ከመጀመሪያ ቅጂያቸው ብዙ ለውጥ እና የአርትኦት ሥራ የተደረገባቸው እንደሆኑ ይነገራል። ስለዚሁ ጉዳይ ለአዲስ ላይቭ በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ ሲናገር «በጨለማ ያልተደረገውን ነገር አንድም የጻፍኩት የለም… ያለውን እንዳለ ነው የምጽፈው» ብሏል። ይህንኑም ከኤሚል ዞላ የአጻጻፍ ዘይቤ የወሰደው እንደሆነ ይናገራል።
ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ደራሲ፣ አርታኢ፣ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም – የልብ-ወለድ ድርሰት ገጸባህርይም ነው። ለኢትዮጵያ የአጫጭር ልብ ወለዶች ማደግም ያበረከተው አስተዋጽኦው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ሀያሲም ነው።
‘‘ደራሲው’’ የተሰኘው የበአሉ ግርማ ልብ-ወለድ በስብሃት ህይወት ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው።
ይቀጥላል….
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም