ስለ አዕምሮ ጤና ይህ ነው ተብሎ ቁርጥ ያለ መገለጫ መስጠት ቢያስቸግርም የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚከተለው ይገልጸዋል። ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር ሲችል፣ ሥራ ሠርቶ ለራሱም ሆነ ለማህበረሰቡ ፍሬ ያለው ነገር መሥጠት እና ሕይወቱን በአግባብ መምራት ሲችል እንደሆነ ያብራራል፡፡
በወራቤ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው ከበኩር ጋዜጣ ጋር የስልክ ቆይታ አድርገዋል። ባለሙያው የአዕምሮ ጤና ችግር በሦስት ነገሮች ሊገለፅ ይችላል ይላሉ፤ እነዚህም የአስተሳሰብ (Tought)፣ የስሜት (Feeling) እና የድርጊት ወይም የባህሪ ችግሮች (Behavioral disorder) መሆናቸውን ነው ያነሱት። እነዚህን ሦሰት ነገሮች ታሳቢ ያደረገ መዛነፍ ከማህበረሰቡ እሳቤ የወጡ፣ ውስጥንም የሚረብሹ ስሜቶች እንደሆነ ይገለፃል ብለዋል፡፡
እንደ የአሜሪካ ሳይካትሪክ አሶስየሽን ቅፅ (DSM) ከ360 በላይ የአዕምሮ ችግሮች ያሉ ሲሆን የድብርት፣ የጭንቀት፣ … በሚል በተለያዩ ማዕቀፎች ይገለፃሉ፡፡
ከዓለማችን ሕዝብ 60 በመቶ ያህሉ ሥራ ላይ እንዳለ ይታመናል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 15 በመቶ ገደማ ለተለያዩ የአዕምሮ ችግሮች የተጋለጡ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በየዓመቱ በመስከረም ወር መጨረሻ የአዕምሮ ጤና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። የዘንድሮ ዓአለም የአዕምሮ ጤና ቀንም በመስከረም ወር መጨረሻ ተከብሮ ውሏል። በሥራ ቦታ ቅድሚያ ለአዕምሮ ጤና “IT’S TIME TO PRIORITISE MENTAL HELTH IN THE WORK PLACE” በሚል መሪ ሐሳብ ነው ተከብሮ የዋለው።
የሥራ ቦታ ለአዕምሮ ጤና፣ የአዕምሮ ጤና ደግሞ ለሥራ ቦታ ከፍተኛ ግንኙነት አለው የሚሉት ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው የአዕምሮ መታወክ ሲኖር ምርታማነት ይቀንሳል ብለዋል። ከሥራ መቅረት በተጨማሪ በሥራ ቦታ መገኘት ቢቻልም በሙሉ አቅም ለመሥራት እንደማያስችል ነው ያስገነዘቡት።
የሥራ ቦታ ጤናማ ካልሆነ ለተለያየ አዕምሮ ችግሮች ያጋልጣሉ። ሥራችን ተጨማሪ ጉልበት (አቅም) የሚጠይቅ ሲሆን በቀኑ ለማድረስ የሚደረግ ሩጫ እና የሥራ መደራረብ ሲኖር ውጥረት ውስጥ ያስገባል። ይህ የሥራ መደራረብ እና በቀኑ ለማድረስ የሚደረግ ሩጫ ጤናማ ላይሆን ይችላል።
በሌላ በኩል የተመጠነ ውጥረት ጥሩ ጎን እንዳለው የጤና ባለሙያው ይናገራሉ። ይህም የበለጠ ለመሥራት ያተጋል የሚሉት ባለሙያው በጣም ውጥረት የሚያበዙ ከሆነ ግን ወደ ጭንቀት ወይም መታከት (ዲስትረስ) ያድጋል። ይህ ማለት የሚያስጨንቀን ነገር እንኳን ቢያልፍ ልንቋቋመው የማንችለው የሰውነትን ሥርዓትን የሚያዛባ ዓይነት ውጥረት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከዚህ ችግር ለመውጣት ባለመቻላችንም ችግሩ ወደ መሰላቸት (በርን አውት) ያድጋል። ይህ ደግሞ እንደ አንድ የአዕምሮ ሕመም ይታያል፡፡
ምልክቶቹ ደግሞ ሥራ ቦታ ገና ስንገባ ኃይል ማጣት (መድከም)፣ የሥራ ቦታ ማስጠላት፣ መሰላቸት፣ የሥራ አፈፃፀም መቀነስ፣ … የመሳሰሉት ናቸው።
እነዚህ ምልክቶች ከሥራ ውጪ በሆነ ሰዓት ላይኖሩ ይችላሉ፤ ከሥራ ውጭ ከቀጠሉ ግን ተስፋ መቁረጥ እየተሰማ ወደ ድብርት ስሜት እና ሌሎች የአዕምሮ ሕመሞች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቀደም ሲል የአዕምሮ ሕመም ካለባቸው ሰዎች ላይ ይህ ችግር ከተከሰተ ደግሞ ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡
በሥራ ላይ የሚከሰተውን የአዕምሮ ችግር ለመከላከል ዋናው መፍትሔ የሚሆነው በሥራ ቦታ አካባቢ ያሉ አመራሮች በተቻለ መጠን የሠራተኞቻቸውን አዕምሮ ጤና መከታተል፣ የሥራ አካባቢውን ጤናማ ማድረግ (ጤና መሆኑን ማረጋገጥ)፣ ሠራተኞች ችግር ካጋጠማቸው ቀድሞ ለይቶ አስፈላጊ እገዛ ማድረግ እና ለዚህ ደግሞ ጥሩ ግንኙነት መመሥረት እንደሚገባ ዶ/ር እስጢፋኖስ አስገንዝበዋል፡፡
ጥሩ ቀረቤታ ከሌለ እና አምባገነናዊ አመራሩም አምባገነን ከሆነ ለሠራተኞቹ ጭንቀትን ሊፈጥር ይችላል፡፡
ሠራተኞች ከሥራ ውጭ በሻይ ሰዓት፣ ከሥራ ሊወጡ ሲሉ ወይም በሥራ ሰዓት ራሳቸውን ዘና የሚያደርጉበትን ቦታ (ሻይ፣ ቡና፣ … ማዕከላት)፣ ማመቻቸት እና የእንቅስቃሴ ማዕከል (wellness corner) ማድረግ ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም ማሕበራዊ ሕይወትን የሚያጠናክሩበት የመጽሐፍ ዳሰሳ ዓይነት ዝግጅት ማድረግ የሠራተኛውን ተግባቦት በመጨመር ችግሮቻቸውን ተነጋግረው የሚፈቱበትን መንገድ ሊፈጥር ይችላል፡፡
ባለሙያው እንደሚያነሱት ከነዚህ በተጨማሪ የጭንቀት አስተዳደር (Stress management) ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ችግሮች ቢገጥሟቸው እንዴት መውጣት ይችላሉ የሚለውን እንዲገነዘቡ ማድረግ ይገባል፡፡
ተቋማቱ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሠራተኞች ካላቸው ደግሞ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይባል፤ ይህም ሕመሙ ከታከመ ከመሥራት የማይከለክል በመሆኑ ሕክምናውን ማመቻቸት፣ ሕመም ላይ ሲሆኑ ደግሞ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሥራቸውን ቤታቸው ወስደው እንዲሠሩ ማድረግ፣ የሠዓት ቁጥጥር አለማድረግ፣ ተመካክሮ ረፍት እንዲወጡ መስጠት፣ አግላይ ቃላትን ባለመጠቀም ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ ይገባል፡፡
በኛ ሀገር ውስጣዊ ችግሮቻችንን የምንገልፅበት የራሳችን መንገድ አለ የሚሉት ዶ/ር እስጢፋኖስ ጭንቀት የሚገለፀው በአካላዊ ምልክቶች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አዕምሮ ውጥረት ውስጥ ሲሆን እና ችግሩ ካልተፈታ ወደ አካላዊ ምልክት ይቀየራል፤ ለምሳሌ ራስ ምታት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ የልብ ምት መዛባት፣ የደረት እና የሆድ ሕመም፣ ምንም ሳይሰሩ መዛል፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መነጫነጭ፣ የተግባቦት ችግር፣ ሥራ መጥላት፣ … የመሳሰሉ ምልክቶች ከታዩ የውጥረት እና የመታከት ስሜት ውስጥ እየገባሁ ነው ብሎ መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
እነዚህ ስሜቶች ሲፈጠሩ የሥራ ባልደረባን ማማከር፣ ከተቻለ ደግሞ በአቅራቢያ ካለ የሥነ ልቦና ባለሙያ ጋር በመመካከር መድኃኒት ሳይወሰድ በምክክር መፍትሔ ማምጣት ይቻላል፡፡
በተጨማሪም በቤት ውስጥ የተለያዩ ዘና የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን (ዮጋ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ) ማድረግ፣ ራስን መንከባከብ፣ ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ፣ ረፍት ወስዶ ከራስ ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚገባ ነው የጤና ባለሙያው ዶ/ር እስጢፋኖስ የሚመክሩት፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም