የዓየር ንብረት ቀውስ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች እየተባባሱ ሊተነበይ ወደ ማይችል ምእራፍ መሸጋገሩን የሚያመላክቱ ሁነቶች አገራቱ እየታዬ በመሆኑ የፓሊሲ ለውጥን የማድረግ ፈጣን ርምጃ እንደሚሻ ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::
በአሜሪካ የኦሪጐን ግዛት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተመራው ዓለም አቀፍ ጥምረት የደረሰበትን ድምዳሜ ለህትመት አብቅቷል:: የዓየር ንብረት ቀውስ መባባሱን በማረጋገጥም በቅርቡ የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤም አፋጣኝ ርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል::
በዩኒቨርሲቲው ጥናቱን ያካሄዱት ዌልያም ሪኘል እና ክሪስቶፈር ዎልፍ አፋጣኝ የፓሊሲ ለውጥ የሚሹት ኃይል፣ ብክለት፣ ተፈጥሮ፣ ምግብ እና ምጣኔ ሀብት መሆናቸውን “የ2024 የዓየር ንብረት ለውጥ” በሚል ርእስ በታተመ ፅሁፍ ላይ አመላክተዋል::
በዩኒቨርሲቲው የደን ልማት ኮሌጅ ኘሮፌሰር ዌልያም ሪኘል የሰው ልጅ ከዚህ ቀደም በማያውቀው ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል የዓየር ንብረት መዛባት ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል::
ተመራማሪዎቹ በየዓመቱ የዓየር ንብረት ለውጥን ከሚከታተሉባቸው 35 አስፈላጊ ዋና ዋና ምልክቶች 25ቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም አመላክተዋል::
በሪፖርቱ የሰዎች ቁጥር በየቀኑ በ200,000 መጨመሩ፣ መርዛማነት የሚለቁ የቤት እንስሳት ብዛት ማሻቀብ፣ የቅሪት አካል ነዳጅ እና የከስል ምርት ተጠቃሚት አለመቀነሱ ተጠቁመዋል::
የደን ሽፋን በ2022 እ.አ.አ 22 ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ሄክታር ከነበረው፤ በ2023 ወደ 28 ነጥብ ሦስት ሚሊዬን ከፍ ቢልም ከሚለቀቀው በካይነት አንፃር በደን የሚመጠጠው ተመጣጣኝ አለመሆኑን አስምረውበታል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሙቀት መጨመር የሰዎች ሞት ማሻቀቡ፣ የግግር በረዶ መቅለጥ፣ የባህር ወለል ከፍታው አሻቅቦ በዳርቻዎች የሚገኙ ኗሪዎችን ማፈናቀሉ አለመረጋጋትን አስፍኖ ውድቀት ማስከተሉን ይፋ አድርገዋል- ተመራማሪዎቹ በደረሱባቸው ማደማደሚያዎች::
የተመራማሪዎቹ ጥምረት በጥልቀት ተወያይቶ የደረሰባቸውን ማሳሰቢያዎች ለተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ያቀርባል። ከዚህም ባሻገር የዓየር ንብረት ቀውስን ለማቅለል የገንዘብ ድጋፍ ማለትም በበለፀጉ ሃገራት የሚለቀቀውን ልቀት ሊገድብ የሚችል የካርቦን ዋጋን ተግባራዊ ማድረግ፣ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: በተጨማሪም የቅሪት አካል ነዳጅን በታዳሽ ኃይል መተካት፣ የካርቦን ማከማቻ ማዘጋጀት እና የብዝሃ ህይወት እና የስነምህዳር ጥበቃን ማጠናከር፣ የአመጋገብ ልምድን መቀየር እና ብክነትን መቀነስ አስገዳጅ ፈጣን ውሳኔዎች መሆናቸውን ነው የጥምረቱ አባላት ያስገነዘቡት።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም