ደን አልባሹ ጡረተኛ

0
133

73ኛ ዓመታቸውን ያከበሩት ብራዚላዊው ጡረተኛ ሂሊዮ  ዳ ሲልቫ በተወለዱበት ሳኦፖሎ ከተማ ባለፉት 20 ዓመታት አርባ ሺህ የዛፍ ችግኝ ተክለው ማፅደቃቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

በብራዚል ዋና ከተማ ሳኦፖሎ ተሽከርካሪ በሚጨናነቅባቸው  ሁለት አውራ ጐዳናዎች መካከል ሦስት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት በ100 ሜትር ስፋት በተለካ ክፍት ቦታ 41,000 የዛፍ ችግኝ መትከል ችለዋል:: አዛውንቱ መትከል ብቻ ሳይሆን ገንዘባቸውን ሳይቀር አውጥተው መንከባከብ በመቻላቸው  88 በመቶው መፅደቁን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው::

ተከላ የተካሄደበት ቦታ ቀደም ብሎ የወዳደቀ ቁስ መጣያ እንዲሁም የአደገኛ እፅ ተጠቃሚዎች መሰባሰቢያ ነበር።  ከ2003 እ.አ.አ ጀምሮ ግን ደን ወደ ለለበሰ መናፈሻነት ተቀይሯል።

አሁን ላይ “ቲኳቲራ ሊኒየር ፓርክ” በመባል የሚታወቀውን ደን የለበሰ ስፍራ ለ20 ዓመታት ሳይታክቱ ጉልበት፣ ገንዘብ እና ጊዜያቸውን ተጠቅመው የለሙት ጡረተኛ አዛውንት ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው ተብሏል።

አዛውንቱ ለፈረንሳይ የዜና አገልግሎት (AFP) ተወልደው፣ አድገው ለአዛውንትነት ላበቃቻቸው ከተማ በቅርስነት አሻራቸውን አኑረው ለማለፍ ወስነው እንደጀመሩት ነው የተናገሩት:: በመጀመሪያዎቹ ዓመታትም አምስት ሺህ ችግኝ በራሳቸው እጅ ተክለዋል:: ጅምራቸው የከተማዋን መዘጋጃ ቤት ኃላፊዎች ትኩረት ስቦም እውቅና አግኝተዋል::

የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊዎች ዳ ሲልቫ ባለሙት ደን 45 የዓእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙም አረጋግጠዋል:: በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በደኑ ከ41,000 በላይ ዛፎች እንደሚገኙ ያስነበበው ድረገጹ አዛውንቱ 50,000 እስኪደርሱ መትከላቸውን እንደማያቆሙም ቃል መግባታቸውን ጠቁሟል::

በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በአንዳንዶች እንደ እብድ ይታዩ እንደነበር የጠቆሙት አዛውንቱ አሁን በአካባቢው ጀግና ተብለው እንደሚወደሱም በልበሙሉነት ተናግረዋል::

አሁን ላይ ተፈጥሮን አድናቂና ወዳጆች በሚለግሱት ድጋፍ በፓርኩ ጠረጴዛ፣ ወንበሮች የመጫወቻ ቁሳቁስ ተሟልቶ፤ መፀዳጃ ቤቶች ተሰርተው የሳኦፓሎ “ቲኳቲራ ሊኒየር ፓርክ” ታዋቂ ሊሆን መቻሉ ነው የተገለጸው።

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ጥቅምት 11  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here