ጥምር ዜግነት ማለት ጥምር መብትም፣ ጥምር ግዴታም ወይም ኃላፊነትም ነው። ጥምር ዜግነት ከ1990ዎቹ ጀምሮ እየተበራከተ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ብዝኃነት ባላቸው በተለይም አምባገነን ባልሆኑ ሀገሮች የሚተገበር፣ የሕገ መንግሥት እና ሕግ መሻሻል የተከሰተበት፣ የዜግነት ጉዳይ ቦርዶችን እና ካውንስል በመፍጠር እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ በተለይም ብዙ ዜጎቻቸው ከትውልድ ሀገራቸው የሚፈልሱባቸው ሀገሮች መልካም መፍትሔ እና ዘመናዊ የዜግነት ማሻሻያ እያደረጉ ይገኛሉ።
ጥምር ዜግነትን በማይፈቅዱ ሀገሮች ዘንድ የሌላ ሀገር ዜግነትን ሲጠይቅ እና በተለያዩ ምክንያቶች በትውልድ (በሚወለድበት ቦታ) ወይም በደም ያገኘውን ዜግነቱን ሊነጠቅ ይችላል። ይህም የስነ ልቦና ጉዳት ይኖረዋል፡፡
ጥምር ዜግነት በሚሰጡ ሀገሮች ግን ለምሳሌ ሰውየው የመጣው ወደ ኢትዮጵያ ከሆነ ጥምር ዜግነት ከተፈቀደለት ወደ ውጭ ሀገር ኤምባሲ ይሄዳል ማለት አይደለም። ጥምር ዜግነት ተፈቅዶለት ወደ ኢትዮጵያ የተጨማሪ ዜግነት መግለጫ የሆነን የመጓጓዣ ሰነድ ወይም ፓስፖርት ይዞ የሚመጣ ሰው፣ ልክ የኢትዮጵያን መሬት ሲረግጥ የሌላኛው ሀገር ዜግነቱ አይሠራም። እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው የሚሆነው ማለት ነው። ችግር ደርሶብኛል ብሎ ወደ ሌላኛው ሀገር ኤምባሲ ቢሄድ አቤቱታው ተቀባይነት የለውም። ወይም ከዚህ ሀገር አውጡኝ ማለት አይችልም። ይህ ማለት በአንድ ጊዜ አንድ ዜግነት ብቻ ነው መጠቀም የሚቻለው፡፡ ይህ አሠራር ጀርመንን ጨምሮ በብዙ ሀገሮች የተለመደ ሲሆን፣ ማኅበራዊ አድሎዎችን ‹‹ሶሻል ዲስባላንስን›› ማስተካከያ ነው። ኢትዮጵያን ለቆ ሲሄድ ግን በፈለገበት ሀገር ዜግነት ይጠቀማል።
የሁለተኛ ዜግነት የሚጠቅመው ሁለተኛ ዜግነት በወሰደበት ሀገር ላይ ወይም የኢትዮጵያ ዜግነቱ ከሁለተኛ ዜግነቱ በአብላጫ ሊረዳው የማይችልበት ሦስተኛ ሀገር ላይ ነው።
ለምሳሌ አንድ ፈረንሣይ የሚኖር እና ወደ ሌላ ሀገር ለሥራ የሚመላለስ ሰው የፈረንሳይ ፓስፖርቱ ለብዙ ሀገሮች ቪዛ ስለሚያስፈልገው ያለ ችግር ይሄዳል፡፡
ብዙ ሀገሮች የሀገራቸውን ፓስፖርት ለሚያመጣ ሰው እግሩ ሀገሩ ላይ ሲረግጥ እና ወዲያው የዚሁ ሀገር ዜግነቱ ሥራ ላይ ሲጀምር ሁለተኛው ዜግነቱ ደግሞ ሀገሩ እስኪመለስ ጊዜ ድረስ ይቆማል፡፡ ለምሳሌ በአርጀንቲና ከዘጠና ቀናት በላይ የቆየ ብቻ ነው የአርጀንቲና ዜግነቱ የሚያገለግለው፡፡
እንደ አርሜንያ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ዜግነታቸው የማይለቀቅ መሆኑን በማስቀመጥ አንድ ሰው የሌላ ሀገር ፓስፖርት ስለያዘ ብቻ ዜግነቱን ያጣል የሚሉትን አይቀበሉም። ይህም በብዛት የሚታወቀው “Jus Sanguins” (Right Of Blood) የሚለው ሲሆን፣ አንድ የዚህ ሀገር ትውልድ ያለው ሰው መቼውንም ዜግነቱን አያጣም።
በተመሳሳይ ቤተ እስራኤላዊያንን፣ ሩሲያዊያንን፣ ጀርመኖችን፣ ጣሊያኖችን፣ ለዚህ አብነት ተጠቃሽ ናቸው። ሌሎች ሀገሮችም ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎቻቸው በሚሄዱበት ሀገር ዜግነትን በተጨማሪ እንዲወስዱ ያበረታታሉ፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ተወላጆች በሄዱበት ሀገር ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ እና የእነሱን ሀገር ጥቅም እንዲያስጠብቁላቸውም ነው።
ጀርመን ዜግነትን ጀርመን ውስጥ ለተወለደ ይሰጣሉ። ይህም ማለት ዜግነትን በቦታው በመወለድ ነው የሚያስጠብቁት።
በሌላ በኩል ስልሳ በመቶ የሚሆነው የስዊዘርላንድ ዜጎች ከስዊዘርላንድ ውጪ ይኖራሉ። ይህም የጥምር ዜግነትን ለዜግነት መሠረታቸው እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል።
አውሮፓ ውስጥ የጥምር ዜግነት በአብዛኛው በተለይም ከአውሮፓ ኅብረት ለመጡት ይሰጣል። በጀርመን ለአውሮፓ ኅብረት ዜጎች ሁለቱንም ዜግነት ለመያዝ ይፈቅዳል። ከአውሮፓ ኅብረት ውጪ ለመጣ ሰው ግን የጀርመን ዜግነትን ለማግኘት ሂደቱ ከባድ ነው። ከዚህ በተቃራኒው የጀርመን ዜጋ ሆነው የሌላ ሀገር ዜግነትን ለማግኘት ሂደቱ ቀለል ይላል። የጀርመን ዜግነትን ብቻ ይዘው የሌላ የጥምር ዜግነት የሚፈቅድን ሀገር ዜግነት ለመውሰድ ለሚያመለክቱ ጀርመናዊያን የጀርመኑ እንዳይሰርዝባችው የዜግነት ማቆያ ሰርተፊኬትን በምክንያትነት አቅርበው ያገኛሉ። ዜግነትን ከማይለቁ ሀገሮች ዜጎች ለምሳሌ እንደ አፍጋኒስታን ያሉ የጀርመንን ዜግነት ደርበው መያዝ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ በጀርመን ሀገር የጀርመን ዜጋ ያልሆነ የውጭ ሀገር ዜጋ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ይችላል። በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥም ኃላፊነት መውሰድ እና መመረጥም ይችላል። የማይችለው በጀርመን ብሔራዊ ምርጫ መሳተፍ ነው። ለአብነትም ጀርመን ውስጥ በሚገኝ የአንድ ክልላዊ መንግሥት (Regional State) የታችኛው ሳክሶንያ (Lower Saxony) ርእሰ መስተዳድር የነበሩት ዴቪድ መክኤል ስተር የመጀመሪያው የጥምር ዜጋ ርእሰ መስተዳድር ነበሩ። የእንግሊዝና የጀርመን ዜጋ ናቸው።
አንዳንድ ሀገሮች በፕሬዚዳንትነት፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ በጦር አዛዥነት የሚመረጥ ወይም የሚሾም ሰው ሁለተኛው ዜግነቱ እንዲረጋ ያደርጋሉ። ይህ ማለት ዜግነቱን ይለቃል ማለት ሳይሆን፣ በሁለተኛው ዜግነቱ የሚጠቀምባቸው መብቶቹ ይረጋሉ (ይታገዳሉ) ማለት ነው።
የሚመረጠው ወይም የሚሾመው ሰው በሥራው እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ ፓስፖርቱን ለሁለተኛ ሀገሩ ይመልሳል። የሚሰጠውን አገልግሎት ሲጨርስ ተመልሶ በፓስፖርቱ መጠቀም ይችላል። ይህን እና መሰል ገደብ ያላቸው የአፍሪካ ሀገሮችም አሉ። ለምሳሌ የግብጽ ጥምር ዜግነት በወታደራዊ እና በደኅንነት በሚሠሩት ላይ ገደብ ያደርጋል። በፕሬዚዳንትነት፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ በጦር አዛዥነት፣ በደኅንነት ኃላፊዎች ላይ ገደብ ሊያስቀምጥ ይችላል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ጥምር ዜግነት የሚፈቀድላችው ሀገሮችን ዝርዝርም ሊያወጣ ይችላል።
የጥምር ዜግነትን በተመለከተ የግንዛቤ ግጭቶች ይስተዋላሉ። በአንዳንድ ቦታ በጥምር ዜግነት ላይ ተቃውሞ፣ ፍራቻ/ፎቢያ/ እና አለፍ ሲልም ጥላቻ ሊንፀባረቅበት ይችላል። ከመቆርቆር፣ ሉዓላዊነቷ እንዳይደፈር ከመሥጋት፣ ባሕልን እና ክብርን እንዳይነካ ከመፍራት ሊሆን እንደሚችልም በምክንያትነት ይነሳሉ፣ ከቅናት እና ከጭፍን ጥላቻ ሊመነጭም ይችላል። ለዚህ አብነትም ጀርመን ናት። በጀርመን ጥምር ዜግነት ተቃዋሚዎች እንደ ማሳመኛ የሚያነሱት ጀርመናዊነት ይጠፋል፣ መጠቀሚያ እንሆናለን፣ እኔ አንድ ዜግነት ብቻ ኖሮኝ እንዴት ሌላው ሁለት ዜግነት ይኖረዋል? የሚሉ ከቅናት እና ከጭፍን ጥላቻ የሚመነጭ ነው።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 38 የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ የዜግነት አዋጅ ቁጥር 378/1996 አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ 7 አንድ ሰው የኢትዮጵያ ዜግነት በሕግ ለማግኘት “የቀድሞ ዜግነቱን የተወ መሆኑን ወይም የኢትዮጵያን ዜግነት ቢያገኝ የቀድሞ ዜግነቱን ለመተው የሚችል መሆኑን ወይም ዜግነት የሌለው መሆኑን ማስረዳት መቻል አለበት” ይላል፡፡ ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን የሚከለክል መሆኑንም ያሳያል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም