ያልተጠሩት ታዳሚዎች

0
137

በካናዳ – ኩቤክ ባልና ሚስት የአባወራውን ልደት ለማክበር በዝግጅት ላይ እያሉ ቤታቸው በተኩላ መንጋ ተከቦ በማየታቸው ሁነቱ ያልጠበቁት፣ የማይረሳ አጋጣሚ ሆኖ ማግኘታቸውን እና በምስል ቀርፀው ማጋራታቸውን ኤንዲቲቪ ድረ ገጽ   አስነብቧል::

የ34 ዓመቱ ሚቹ ጁልስ እና የ33 ዓመቷ ባለቤቱ ማያ ጁልስ የአባወራውን የልደት በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ ነበሩ:: በዚሁ መካከል ያልጠበቁትን ሁነት መመልከት ችለዋል::

በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ተኩላዎች ስለ መኖራቸው ማስጠንቀቂያ ሲነገር ቢሰሙም በዚህ መልኩ በመስታዉት የተሸፈነው ቤታቸው በሚጨኹ በርካታ ተኩላዎች  ይከበባል ብለው አላሰቡም ነበር::

34ኛ ዓመት የልደት በዓሉን የሚያከብረው አባወራው ሚቹ ጁልስ በኒው ጀርሲ ፎቶ ግራፍ አንሺ ባለሙያ በመሆኑ የቀረፀውን ምስል ለኒው ዮርክ ፖስት አጋርቶታል:: ባለሙያው በህይወቱ በዚህ መልኩ ተኩላዎችን በቅርበት ተመልክቶ አለማወቁን እና አስደሳች የህይወት ገጠመኙ መሆኑንም ነው ያሰፈረው::

ፎቶ ግራፍ አንሺው ባለሙያ ለዱር እንስሳት ጥልቅ ፍቅር ያለው መሆኑን ገልፆ ጥንዶቹ ለሳምንት ያህል በክፍላቸው በቆዩባቸው እለታት  ተኩላዎቹን በቅርበት መመልከታቸውን አብራርቷል::

ከተኩላዎቹ ጋር በቅርበት ፊት ለፊት በመተያየቱ እድለኛ መሆኑን ነው የገለፀው፤ ፎቶግራፍ አንሺው ባለሙያ ርቀቱን ጠብቆ የቤቱን በር ሲከፍትላቸውም አለመሸሻቸው  እንዳስገረመው  ነው ያረጋገጠው::

ፎቶ ግራፍ አንሺው ሚቹጁልስ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኘው ገጠመኝ መደሰቱን ጠቁሞ ይህንኑ ገጠመኝ ዳግም ለመመልከት ወደ ካናዳ እንደሚመለስ ቃል መግባቱን አስነብቧል::

በማጠቃለያነት እንደ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ደህንነት ፈንድ ካናዳ ከሩሲያ ቀጥላ ባላት የተኩላዎች ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን እና ብዛታቸውም 50 ሺህ እንደሚገመት ሰፍሯል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here