ለፍቶ መና እንዳንሆን!

0
148

ምዕራባዊው የሀገራችን ክፍል ለሰብል ምርት የሚመች ለም መሬት ነው:: ከዚሁ ሰፊ መሬት ውስጥ በተለይ ከጠገዴ እስከ ሁመራ፣ ከአብድራፊ እስከ ቋራ የተንጣለለው ምዕራባዊው የአማራ ክፍል ሱፍ እና ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ጥጥ በስፋት የሚመረትበት ነው:: ለውጪ ገበያ እየቀረቡ እንደ ቡና ሁሉ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚያስገኙትን እነዚህኑ ነጫጭ ምርቶች የሚያበቅል በመሆኑም “የነጩ ወርቅ ምድር” ለመባል በቅቷል::
አካባቢው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ፣ የሚውለውን ማሽላ ጨምሮ እነዚህኑ ነጫጭ ወርቆች፣ ቦለቄ እና ማሾን በማምረት በየዓመቱ በተለይ በሰሊጥ ምርት በአስርት ሚሊዮኖች ኩንታል ለውጪ ገበያ በማቅረብ በውጭ ምንዛሪ ግብአት ረገድ ለሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ሲሆን ናሯል::
ዘንድሮ ግን ይኸው የነጩ ወረቅ ምድር የለፋበትን መና የሚያስቀሩ ችግሮች ተጋርጠውበታል – ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና በሠላም እጦት ምክንያት የደረሰውን ሰብል የሚሰበሰብ የሰው ኃይል እጦት::
የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቅመን በተለይ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡትን ምርቶች በሜካናይዝድ እርሻ አዘምነን እጥፍ ድርብ በማሳደግ ያለብንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ልናቃልል ሲገባ የተመረተውን የሚሰበስብ የሰው ኃይል ማቅረብ አለመቻላችን ችግሩን “በእንቅርት ላይ …” አድርጐታል::
በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እየታጨደ ያለው የሰሊጥ ምርት በቂ የሰው ኃይል አግኝቶ ካልተሰበሰበና ካልተወቃ ለምስጥ እና ለሰሊጥ መጣጭ ተባይ ከመጋለጡም በላይ አሁን በሚጥለው ዝናብ ረግፎ ይቀራልና በአካባቢው የሚኖር ዜጋ ሁሉ በዘመቻም ጭምር ምርቱን ሊሰበስብ ይገባል::
ከአሁን በፊት በምርት አሰባሰብ ተግባር ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሄደው የሰው ኃይል እንዳይንቀሳቀስ እክል የፈጠረበት የሰላም እጦት እንዲፈታም ሁሉም ተዋጊ ኃይሎች በዚህ በመኸር ወቅት የሚያካሂዱትን ጦርነት በማቆም የዜግነት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል:: እንዲያ ካልሆነ ግን ነጩን ወርቅ ውኅ ይበላዋል!ብቻ ሳይሆን የምንዛሪ ምንጫችንን በማድረቅ ድህነትን እናባብሳለንና ለሰብል ምርት አሰባሰብ ትኩረት እንስጥ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here