በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም እጦት እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መብዛት ቀድመው በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያሳደረ ነው:: በተለይ እነዚህ ችግሮች ከፍተኛ የልማት ሥራ በሚከናወንባቸው እና በዚህ ወቅት ሚሊዮን ሠራተኞችን በሚፈልጉት የወልቃይት እና ምዕራብ ጎንደር አካባቢዎች ጉልህ ተጽእኖ እያሳደረ ነው:: እነዚህ አካባቢዎች ሁሉንም የሰብል አይነቶች ማብቀል የሚችሉ ቢሆኑም በዋናነት የሚታወቁት በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እና ለፋብሪካ በጥሬ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ምርቶችን በስፋት በማምረት ነው:: ለአብነት የምዕራብ ጎንደር ዞን በተለይ የኤክስፖርት ምርት በሆነው ሰሊጥ ክልላዊ ድርሻው 29 ነጥብ 8 በመቶ፤ የምርት ድርሻው ደግሞ 27 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል::
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንም በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎች በስፋት የሚመረቱበት ነው። የፋብሪካ ጥሬ ግብዓት የሆኑ ምርቶች እና ሌሎች የምግብ ሰብሎችንም በከፍተኛ መጠን በማምረት ይታወቃል:: ዞኑ ከ561 ሺህ 856 ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት እንዳለው ግብርና መምሪያው አስታውቋል:: ከዚህ ውስጥ በ2016/17 የምርት ዘመን 12 ሚሊዮን 664 ሺህ 860 ኩንታል ምርት ማግኘትን ታሳቢ በማድረግ 561 ሺህ 30 ሄክታር መሬትን በሁሉም አይነት ሰብሎች ሸፍኗል:: ይህ በ2015/16 ዓ.ም በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ ከነበረው የማሳ መጠን ከ56 ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ አለው:: በወቅቱ 6 ሚሊዮን 582 ሺህ 382 ኩንታል ምርት መገኘቱን የግብርና መምሪያው መረጃ ይጠቁማል:: ይህም በዚህ ዓመት ለማግኘት በዕቅድ ከተያዘው ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ነው:: በእርግጥ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ በዕቅዱ ላይ ተጽእኖ አይፈጥርምን?
አቶ ራሳቸው አሰግድ አሥራ አምስት ዓመታትን በእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ሠርተዋል:: “በዘርፉ ተሰማርቼ ይህን ያህል ዓመት ስኖር እንደ ዘንድሮው አይነት ተስፋ የሚያስቆርጥ ክስተት አጋጥሞኝ አያውቅም” ሲሉ ዓመቱ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ጫና በዝርዝር ያስረዳሉ:: ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን 600 ሄክታር መሬትን በሰሊጥ እና በማሽላ እንደሸፈኑ ተናግረዋል:: ከዚህ ውስጥ 200 ሄክታር የሚሆነው በሰሊጥ እንደተሸፈነም አስታውሰዋል:: በየዓመቱ በዚህ ወቅት ለሚደርሱ እንደ ሰሊጥ ለመሳሰሉ ሰብሎች ስብሰባ ይፈጠር የነበረው የሥራ ዕድል ዘንድሮም ቀጥሎ ጥሪ መደረጉን ያስታውሳሉ:: ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የሚፈለገው ሠራተኛ ወደ አካባቢው ባለመምጣቱ የሰሊጥ አዝመራው መሬት ላይ እንዲቀር እያደረገው ነው ይላሉ:: ሰሊጥ በታጨደ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መወቃት እንዳለበት የሚገልጹት ባለሐብቱ፤ ይሁን እንጂ በቂ የሰው ኀይል ባለመገኘቱ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ለፀሐይ እና ለዝናብ ተጋልጦ ለሰሊጥ መጣጭ ተባዮች ቀለብ ሆኖ መቅረቱ ያንገበግባቸዋል:: ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብም ሰሊጥ ገበያ ሳይደርስ ከማሳው እያስቀረው መሆኑን ተናግረዋል:: የሰሊጥ ሰብል ምርታማነት በእነዚህ ችግሮች ምክንያት እየቀነሰ መሆኑን ባለሐብቱ አቶ ራሳቸው ተናግረዋል:: በአሁኑ ወቅት አንድ ኩንታል ሰሊጥ ለማግኘት ከ25 ሂላ (እስራት) በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት ግን ከግማሽ ሂላ በታች ይገኝ እንደነበር አስታውሰዋል:: በመሆኑም አሁንም አካባቢው በርካታ ሠራተኞችን የሚፈልግ በመሆኑ ሠራተኞች ወደ አካባቢው ሂደው የሚባክነውን ሰብል ለመታደግ የሚመለከታቸው አካላት በትብብር እንዲሠሩ ጠይቀዋል::
የዞኑ ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ እና የኤክስቴንሽን ቡድን መሪ በሪሁን ጸጋዬ እንደገለጹት በዚህ ዓመት ከሚጠበቀው አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከሰሊጥ፣ ቦለቄ እና ማሾ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል:: ባለፈው ዓመት 276 ሺህ 969 ሄክታር መሬትን በሰሊጥ በመሸፈን 1 ሚሊዮን 384 ሺህ 845 ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል። በዚህ ዓመት ግን የሰሊጥ ሽፋኑ የቀነሰ ሲሆን የተሸፈነው 281 ሺህ 63 ሄክታር መሬት ብቻ ነው:: ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከአራት ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ የማሳ መጠን ብልጫ አለው::
ማሾ ሌላው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የቅባት እህል ነው። በ2014/15 ዓ.ም በዘርፉ አጋጥሞ በነበረው የዋጋ ችግር ምክንያት በርካታ አርሶ አደሮች ከማሾ ማምረት ውጭ እየሆኑ መምጣታቸውን አቶ በሪሁን ጠቅሰዋል:: በ2016/17 ዓ.ም 2 ሺህ 348 ሄክታር መሬት በማሾ ተሸፍኗል:: በእርግጥ ይህ ሽፋን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ 193 ሄክታር ብልጫ ያለው መሆኑ ምናልባትም የማሾ ልማቱ ተስፋ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ይታመናል::
ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች በጥሬ ግብዓትነት ከሚውሉ ምርቶች ውስጥ የሚመደበው አኩሪ አተር ባለፉት ዓመታት የነበረው ተፈላጊነት እና የዋጋ መቀነስ ልክ እንደ ማሾ ሁሉ የማሳ ሽፋኑ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ እንዲሄድ አድርጎታል:: በዚህም ዋና ማሳያው በዘንድሮው የመኸር እርሻ 81 ሺህ ሄክታር መሬትን በአኩሪ አተር ለመሸፈን ታቅዶ ተግባራዊ የሆነው 17 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ነው:: በእርግጥ ይህ የማሳ ሽፋን ከባለፈው ዓመት ጋር በንጽጽር ሲታይ 12 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ የማሳ መጠን ብልጫ ያለው ነው::
በዞኑ ከሚመረቱ የጥራጥሬ እና የቅባት ምርቶች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል:: ነገር ግን የምርቶቹ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አጎራባች ክልል ወረዳዎች መውጣት ዕቅዱ ከዕቅድ የዘለለ እንዳይሆን አድርጎት መቆየቱን ገልጸዋል:: በዚህም ምክንያት በ2015/16 ዓ.ም ከተመረተው አጠቃላይ የሰሊጥ ምርት ውስጥ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ የተቻለው 113 ሺህ 429 ኩንታል ብቻ ነው:: ይህም በዓመቱ ከተገኘው የሰሊጥ ምርት ጋር ሲነጻጸር በ1 ሚሊዮን 271 ሺህ 416 ዝቅ ያለ ነው:: 29 ሺህ 261 ኩንታል ማሾ እና 27 ሺህ 34 ኩንታል አኩሪ አተር ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለ አቶ በሪሁን ሲገልጹ አፈጻጸሙ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል::
በዚህ ዓመትም በአጠቃላይ ከሚመረተው የኤክስፖርት እና የፋብሪካ ምርቶች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል:: ሕገወጥነት እና የጥራት መጓደል ግን አሁንም በስጋትነት መለየታቸውን አቶ በሪሁን ያስረዳሉ::
በክልሉ ያጋጠው የሰላም መደፍረስ እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ለምርት መቀነስ እና ለጥራት መጓደል ስጋት መሆናቸው ተመላክቷል:: አቶ በሪሁን የዝናብ መብዛት ዞኑ ያስፈልገኛል ካለው የቀን ሠራተኛ ቁጥር በጊዜ ካለመግባት ጋር ተዳምሮ በዞኑ የምርት አሰባሰብ ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ በዘር ከተሸፈነው ውስጥ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል መሰብሰቡን፤ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሰሊጥ እንደሆነ ጠቁመዋል:: በተለይ የዝናብ መብዛቱ የምርት ጥራት መጓደል እንዲፈጠር፣ ምስጥ እና ሰሊጥ መጣጭ ተባዮች መነሳታቸው፣ የግብርና ግብዓት እጥረት፣ የዘር አሸፋፈኑ በምክረ ሐሳቡ መሠረት እንዳይከወን ማድረጉ የምርት መቀነስ እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመዋል:: በተለይ እንደ ዞን ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ለዞኑ የቀረበው ከ17 በመቶ ያልበለጠ መሆኑ ችግሩ እንዲሰፋ ማድረጉን አቶ በሪሁን ጠቁመዋል:: በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ የምርት ብክነት እየደረሰ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የምርት መቀነስ ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል::
የመካናይዜሽን ጅምር አለመስፋቱ የምርታማነት ዕድገቱ ላይ ጉልህ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝም አስታውሰዋል:: በዞኑ ከሚታረሰው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆነው ለመካናይዜሽን እርሻ ምቹ ነው:: “በተለይ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች ቢኖሩ ኖሮ ዛሬ ክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ የገደበው የሠራተኛ ቁጥር አነስተኛ መሆን በምርት አሰባሰብ ላይ ስጋትን ባልፈጠረ ነበር” ሲሉ ለጅምሩ መስፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል::
ሕገወጥ ግብይትን ለማስቀረት ሌላው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት ጉዳይ እንደሚሆን አቶ በሪሁን ተናግረዋል:: በተለይ የኬላ ፍተሻዎችን እና የጸጥታ ሥራዎችን በማጠናከር የህገ ወጥ ንግድ ግብይትን ለማስወገድ በትኩረት ይሠራል ብለዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ አምራቹ ተጠቃሚ እንዲሆን፤ ዞኑም የተጣለበትን ሀገራዊ አበርክቶ እንዲወጣ የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሠሩ ይገኛሉ:: በዚህም እስከ አሁን ከ300 በላይ ባለሐብቶች ከአምራች አርሶ አደሮች ምርት ለመረከብ ውል መውሰዳቸውን አስታውቀዋል:: ውል የወሰዱ ነጋዴዎችም በገቡት ውል መሠረት በወቅቱ እንዲረከቡ ጥሪ ሲያቀርቡ ዞኑ ለደኅንነታቸው ከፍተኛ ትብብር እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል::
መንግሥት ለጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል:: በ2017 ዓ.ም ከጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች የወጪ ንግድ ከ750 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል:: ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ቁጥር1026/2017 መጽደቁን አስታውቀዋል:: ይህም በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የግብይት ማነቆዎችን ከመፍታት ባሻገር ወጪን በመቀነስ፣ ተደራሽነትን በማሻሻል እና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን እንደሚያረጋግጥ ጠቁመዋል:: በመሆኑም ላኪዎች ምቹ ሁኔታውን በመጠቀም ምርት እንዲገዙ እና ለፈላጊ ሀገራት እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል::
ተወካይ ግብርና መምሪያ ኅላፊዉ አቶ በሪሁን ጸጋዬ ምርቱ ሳይባክን በወቅቱ በመሰብሰብ አምራቹ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ክልሉም በዘርፉ ላለው ሀገራዊ ድርሻ የበኩሉን እንዲወጣ የሰብል ስብሰባው ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል:: በተለይ ወልቃይት ከሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች የተሻለ ሰላም የሰፈነበት ቢሆንም ሠራተኛው ከመነሻው ተነስቶ ሥራው ያለበት ቦታ እስኪደርስ ያለው የመንገድ ላይ የጸጥታ ችግር ፈተና መሆኑ የሚፈለገው ሠራተኛ በወቅቱ ደርሶ የምርት ብክነትን እንዳይታደግ እና ራሱን ተጠቃሚ እንዳያደርግ አድርጎታል ብለዋል:: እንዲህም ሆኖ ግን መምሪያው የሚፈለገው የሰው ኀይል አሁንም ወደ ዞኑ እንዲገባ ከአጎራባች ወረዳዎች እና ዞኖች ጋር ጠንካራ ትስስር እየፈጠረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም