የ ‘ኤ’፣ ‘ቢ’ እና ‘ሲ’ ውጤት መገለጫ

0
179

ካለፈው የቀጠለ

በጥቅምት 4/2017 ዓ.ም ዕትማችን የዚህን ፅሑፍ ቀዳሚ ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል::

በመጀመሪያው ክፍልም የዘርፉ ጸሐፊ ሮበርት ኪዮሳኪ የአብዛኛው ዓለም ክፍል የትምህርት ስርዓት ተማሪዎች ገንዘብ እንዲሰሩ የማያስችል፤ ከዚህ ይልቅ ከሃብታም ወስዶ ለድሃ የሚሰጥ አይነት መሆኑን ጠቁሟል::

ሮበርት ዓለም የገጠማት የገንዘብ ቀውስ አይደለም፤ ቀውሱ የገንዘብ ትምህርት እጦት መሆኑንም በመጀመሪያው ክፍል ፅሑፍ አስገንዝቧል:: የዚህ ጽሑፍ ቀጣይ እና የመጨረሻው ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል::

በትምህርታቸው ጎበዝ የነበሩ ተማሪዎች በሥራቸውም ያን ያህል ውጤታማዎች እንዳልሆኑ ሮበርት ይናገራል:: በአንድ የተለመደ መንገድ በማሰብ ስኬታማዎች እንደነበሩ ይሰማቸዋል:: በትምህርት ቤት ቆይታቸውም መሳሳትን እንደ ውድቀት ምልክት አድርገው አልፈዋል:: አደጋዎችን መጋፈጥ አይሹም:: መሳሳትን ይሸሹታል:: ጎበዝ ተማሪዎች የይዘት ተማሪዎች ናቸው:: ሁለት ሲደመር ሁለት አራት ነው ብለው የሚቆሙ ናቸው:: ሁለት እና ሁለት ተደምረው አራት ዶላር ወይም ሚሊዮን ዶላር እንዴት መሆን እንደሚችሉ አያውቁም:: ካፒታሊስቶች ግን ሁለት እና ሁለትን ደምረው እንዴት አራት መቶ ሺህ ዶላር  ማድረግ እንደሚችሉ ያውቁበታል:: ካፒታሊስቶች ይሻገራሉ:: አውዱን በሚገባ ይረዱታል:: ዓለም እንዴት እንደሚዘወር፤ ማን እንደሚዘውረው ይረዳሉ፤ ጉዳያቸው ሒሳቡን መሥራት አይደለም:: ዶላሩን ማግኘት እና ማባዛት እንጂ:: ሮበርት “የተማረ ወድቆ አይወድቅም እና ጠንክረህ ከተማርህ ሥራ ታገኛለች የሚለውን ሐሳብ እብደት ነው” ይላል:: ተመሳሳይ ነገር በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ ነውና:: ሰዎች ያሉበትን አውድ በመቀየር ወደ ተሻለ ሕይወት ማምጣት ይቻላል የሚለው ሮበርት አካል፣ አዕምሮ፣ ስሜት እና መንፈስን በመቀየር ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዝባል:: “የ‘ኤ’ ተማሪዎች በሕይወታቸው የማይሳካላቸው መሳሳትን የደደብነት ምልክት አድርገው በመውሰዳቸው ነው:: በአንጻሩ የ’ሲ’ ተማሪዎች ስህተቶች የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ አጋጣሚዎች ናቸው ብለው ያምናሉ:: እንደ እድል ይቆጥሯቸዋል”  ይላል ሮበርት::

በስሜት መብሰል ሮበርት ሌላው የሚያነሳው ጉዳይ ነው:: ብዙ ሰዎች በአካል አድገዋል:: በስሜት ግን ገና ልጆች እና ጭቅላዎች ናቸው፤ ይማራሉ፤ ይመረቃሉ፤ ሥራ ይዘው ገንዘብ ያገኛሉ:: በሥራቸው ላይ ሕጻኑ ማንነት ይገለጻል:: ደሞዝ ይከፈላቸዋል:: ሕጻኑ ማንነት ገንዘቡን ያባክንባቸዋል:: በዚህ ሁኔታም ዓመታት ያልፋሉ:: አንድ ቀን ምንድን ነው እየሆነ ያለው ብለው ይባንናሉ:: ለዓመታት ሠርተዋል:: ግን ምንም ውጤት የላቸውም:: የስሜት ብስለት ማጣት ብዙ ጎልማሶችን ከእውነታው ዓለም ዕይታቸውን ይጋርደዋል ይላል ሮበርት::  መስራት የሚያስፈልጋቸውን ሳይሆን መስራት ያለባቸውን በመከወን የጡረታ ደጃፍ ላይ ይደርሳሉ:: ሮበርት የሰውን ልጅ ነጻ የሚያወጣው የአዕምሮው አለቃ መሆኑ ነው ይላል:: ገንዘብ ሀብታም አያደርግም ነው የሚለው:: ይልቁንስ ከገንዘብ ይልቅ የሰው ልጅ አዕምሮ ነው ሀብታም የሚያደርገው ይላል:: አስተዳደራዊ ካፒታሊስቶችን ሮበርት የ’ኤ’ ተማሪዎች ናቸው በማለት ይገልጻቸዋል::  ሥራ ፈጣሪዎች አይደሉም:: የግላቸው ሥራ የላቸውም:: ተቀጣሪዎች ናቸው:: የሥራ ፈጣሪዎችን ድርጅት የማስተዳደር ኀላፊነት እና ስልጣን ነው ያላቸው:: የገንዘብ ኪሳራዎችን በግላቸው አይጋፈጡም:: ድርጅቱ እስካለ ጊዜ ድረስ ጥሩም ይሁን መጥፎ ቢሰሩ  ደመወዛቸው ይከፈላቸዋል::  ሮበርት የ’ቢ’ ተማሪዎችን ቢሮክራት ሲል ይጠራቸዋል:: ዓለም እየተመራች ያለችው በቢሮክራቶች ነውም ይላል:: የዓለም ችግር ሁሉ ፈጣሪዎች ቢሮክራቶች ስለመሆናቸው የሚናገረው ሮበርት ባለስልጣናት፣ ፕሬዝደንቶች፣ የሽያጭ ማናጀሮች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያካትታል:: እነዚህ ሰዎች በግላቸው ምንም ዓይነት ኀላፊነት የማይወስዱ ናቸው:: ቢሮክራቶች ብዙ ገንዘብ ሊከስሩ ይችላሉ:: ከግላቸው ግን አንዲትም ሳንቲም አትጎድልም:: ተሿሚዎች ወይም ተቀጣሪዎች በመሆናቸው የሚከስረው ድርጅቱ ወይም ቀጣሪው ነው:: “ ‘ቢ’ ዎች ሀገር የሚመሩ ናቸው:: ብዙ ጠበቃዎችን እና የሕግ ሰዎችን በዚህ ዝርዝር  ውስጥ ታገኛላችሁ” ይላል ሮበርት:: ሮበርት ሲናገር ለካፒታሊስት ገንዘብ ስጠው በመቶዎች እጥፍ ያባዛዋል:: በአንጻሩ ለቢሮክራቶች ገንዘብ ብትሰጣቸው ያጠፉታልይላል:: እንደ ሮበርት ሐተታ የዓለም ገንዘብ ቀውስ ምንጮቹ ’ቢ’ ዎች ናቸው::

ሮበርት ተማሪ እያለ መምህሮቹ ስለገንዘብ ለምን እንዳላስተማሩት አሁን ያስባል:: ሀብታም መሆን እንዲችል ለምን እንዳልነገሩት በማስታወስ ይገረማል:: በሁለት ምክንያቶች አስተማሪዎች ስለ ገንዘብ እንዳላስተማሩትም ደርሼበታለሁ ነው የሚለው:: የመጀመሪያው እነሱ ራሳቸው የገንዘብ እውቀት የላቸውም:: ሁለተኛው መንግሥት ይጠብቀናል ስለገንዘብ መማር አስፈላጊ አይደለም ብለው በማሰባቸው ነው::

ሮበርት ኪዮሳኪ ካሽ ፍሎው ኳድራንት በሚለው መጽሐፉ በጣም ምጡቅ እና  ጎበዝ ተማሪዎች ስሜታቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ትምህርቶችን የግድ ማግኘት እስካልቻሉ ድረስ፤ ውስጣቸው የሚገኘው ፍርሀት አካላቸው የግድ ማድረግ የሚገባውን  ሥራዎች እንዳይከውን ያደርገዋል ይላል:: “ለዚህ ነው እነዚህ ሁልጊዜም በትምህርታቸው ’ኤ’ የሚያመጡ ጎበዝ ተማሪዎች  በትንተናዊ ሽባነት (አናሊሲስ ፓራሊሲስ) ውስጥ ታግተው እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገሮች በማጥናት ምንም ሳይከዉኑ ዝም ብለው የሚቆዩት” ሲል ያስረዳል:: ሮበርት እነዚህ ጎበዝ ተማሪዎች ሁልጊዜም ቢሆን ’ኤ’ ውጤት የሚያመጡት ጥቂት ስህተቶችን ከመስራታቸው የተነሳ ነው፤ የስሜታዊነት ነውጥ ችግሮች ጎበዝ ተማሪዎችን የተግባር ሰው  እንዳይሆኑ እክል ይፈጥርባቸዋል ይላል::

በእውነተኛ የሕይወት ጨዋታ ላይ ውጤታማ የሚሆኑ ሰዎች   ድርጊት ውስጥ የሚገቡ እና ደጋግመው የሚሳሳቱ፤ እንደገናም ከስህተታቸው መማር የሚችሉ ናቸው ብሏል:: አብዛኞቹ ሰዎች ያልተሳካላቸው ለብዙ ጊዜ ያህል ውድቀትን በመፍራታቸው እና በመሸሻቸው ነው:: ሮበርት ሰዎችን በአራት ይከፍላቸዋል:: ኢ߹ ኤስ ߹ቢ እና አይ በሚል ተቀጣሪ߹ የአነስተኛ ስራ ባለቤት߹ የትልቅ ስራ ባለቤት እና ኢንቨስተሮች በሚል:: እናንተ ከየትኛው ማዕዘን ውስጥ ናችሁ የሚለው ሮበርት መፍትሔው ያላችሁበትን ኳድራንት (ማዕዘን) መቀየር ነው ሲል ያስረዳል:: ብዙዎች ሰዎች በተቀጣሪነት እሳቤ እና ሕይወት ውስጥ የሚቆዩት እሳሳታለሁ እና ሥራ አጣለሁ በሚል ፍርሀት ነው::

አነስተኛ ሥራ ያላቸው ሰዎች በራሳቸው እምነት ስለሌላቸው ባሉበት  ይቀራሉ:: የራሳቸው አለቃ መሆን ይፈልጋሉ፤ ስራውን ለብቻቸው መስራት ይፈልጋሉ:: እነሱ ቢያቆሙ ስራው እና ገቢያቸው ይቆማል:: ስራውን ማስፋፋት ስለሚፈሩ ብቻቸውን እንደሰሩ ባሉበት ይቀራሉ:: ትልቅ ስራ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ስራው እነሱን አይፈልግም፤ ቢኖሩም ባይኖሩም ስራውን የሚያስኬዱትን ሰዎች ቀጥረዋል:: ድርጅታቸው ገቢ ማመንጨቱን ይቀጥላል:: ’ኢ’ እና ‘ኤስ’   ትኩረታቸው የስራ ዋስትና ነው:: ቋሚ ነገር ጥሩ ነው ይላሉ:: ’ቢ’ እና ’አይ’ ደግሞ ተጨማሪ ሀብት ስለማግኘት እና ምርት ላይ ነው የሚያተኩሩት:: ‘አይ’ ደግሞ ኢንቨስተሮች ናቸው::

በአጠቃላይ ገንዘብ ያወራል የሚለው ሮበርት፤ ገንዘብን የሚፈልግ ሰው ቋንቋውን አውቆ ሊያናግረው ይገባል ብሏል:: የአካዳሚክ ሰዎች ትምህርት መማር፤ ስራ ማግኘት፤ ጠንክሮ መስራት፤ ገንዘብ መቆጠብ፤ ብድርን ማስወገድ፤ ቤት መግዛት እና ጡረታ መውጣትን ግባቸው አድርገው ነው የሚኖሩት:: በአንጻሩ የገንዘብ እውቀት ያላቸው ሰዎች ገቢ ማግኘት፤ ወጪ ማድረግ፤ አሴት ማዘጋጀት፤ ሀብት መፍጠር፤ ተበድሮ መስራት፤ የገንዘብን ፍሰት መረዳት፤ የካፒታል ትርፍ ማግኘትን ታሳቢ አድርገው ይኖራሉ:: ሀብታም እና ደሀ የሚሉ ክፍፍሎችን የሚፈጥሩትም እነዚህ ሁለት የተለያዩ አረዳዶች ናቸው:: ሮበርት መቆጠብ የተቀጣሪዎች እና አነስተኛ ገቢ ስራ ባለቤቶች ቀዳሚ ምርጫ ነው ይላል:: ገንዘባቸውን ወደ ባንክ ይወስዱና ያስቀምጡታል:: እናም ታላላቅ ስራ እና ኢንቨስትመንት  ያላቸው ሰዎች ከባንክ ወስደው ለትርፋማ ስራ ይጠቀሙበታል:: በደሀዎች ብር ሀብታሞች የተሻለ ሀብት ይፈጥሩበታል:: ደሀዎች ግን ብከስርስ ብለው ስለሚሰጉ ትንሽ ገንዘባቸውን ወስደው ባንክ ቤቶች ማስቀመጥን ይመርጣሉ:: የገንዘብ እውቀት ነው ነጻ የሚያወጣው ይላል ሮበርት ኪዮሳኪ::

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here