በታላቁ መድረክ ይሳካለት ይሆን?

0
173

የ2024ቱ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 14 2017 ዓ.ም በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ይደረጋል። በየዞኑ ከተሳተፉ 36 ክለቦች መካከል የበረቱት ስምንቱ ክለቦች ናቸው በሻምፒዮንስ ሊጉ የሚሳተፉ። ቀደም ብሎ ይፋ በሆነው የምድብ ድልድል የሞሮኮው አስፋር፣ የሴኔጋሉ አይግልስ ዴ ላማዴና፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ማዘምቤ፣ የደቡብ አፍሪካው ዩንቨርሲቲ ኦፍ ማስተርን ኬፕ በምድብ አንድ ተደልድለዋል። የደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሚሎዲ ሰንዳውንስ፣ የናይጀሪያው ኦዶ ኪዊንስ፣ የግብጹ ክለብ ማሳር እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛው ምድብ ነው የተደለደሉት።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ምስራቅ አፍሪካን ወክሎ ነው በአራተኛው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የሚሳተፈው። የሀገራችን ስኬታማው ክለብ በዘንድሮው በሴካፋ ዞን የሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ፍጻሜ የኬኒያውን ፖሊስ ቡሌትን በማሸነፍ ነበር ወደ ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ ያለፈው። ክለቡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊግ የተሳተፈ የመጀመሪያው ክለብም ይሆናል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን በሻምፒዮንስ ሊጉ ረጅም ርቀት ለመጓዝ የተለያዩ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሜዳ ላይ ዝግጅት ጎን ለጎን በክረምቱ የዝውውር ወቅት በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን የማጠናከር ሥራ ሠርተዋል። የፊት መስመር ተጫዋቾችን ንግስት በቀለን ከመቻል፣ መሰረት ወርቅነህን ከአርባ ምንጭ፣ ሳራ ነብሶን ከአዳማ ከተማ አስፈርመዋል። ከኋላ ክፍል ደግሞ ታሪኳ ዴቢሶምን ከመቻል እና ቅድስት ዘለቀን ደግሞ ከሀዋሳ ከተማ በማስፈረም ቡድናቸውን አጠናክረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከአሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ጋር በነበረው ቆይታ በሻምፒዮንስ ሊጉ መድረክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራችንን አጠናቀናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ንግድ ባንክ ለካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ጥቅምት ሦስት ቀን 2017 ዓ.ም ነው ቅድመ ዝግጅት የጀመሩት። በዚህ የዝግጅት ወቅትም የቡድናቸው አምስት ተጫዋቾች ጉዳት ገጥሟቸዋል። እንደ አሰልጣኙ ገለጻ ሁለቱ ተጫዋቾች የከፋ ጉዳት የገጠማቸው በመሆኑ ለሞሮኮው ግዙፍ የሴቶች የክለብ ውድድር አይደርሱም። ሦስቱ ተጫዋቾች ግን ቀላል ጉዳት እንደገጠማቸው ነው የተናገሩት። በአጠቃላይ ግን በስነ ልቦና፣ በአካል ብቃት፣ በቴክኒክ እና በታክቲክም ውድድሩን በሚመጥን መልኩ ዝግጅት እያደረጉ ነው።
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ምክንያት ክለቡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ውድድር ላይ መቆየቱ ለዝግጅት አልተቸገሩም። የተጫዋቾችን የውድድር አቅም ለማሳደግም የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል። ታዲያ አሁን ላይ ቡድኑ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ጥሩ የቡድን መንፈስ ገንብቷል። ይሁን እንጂ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ በዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ቢታጀብ ዝግጅታቸውን ሙሉ ያደርገው እንደነበር አሰልጣኙ ተናግሯል። የአዲሱ የውድድር ዓመት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ቀደም ብሎ ቢጀመር ኖሮ የበለጠ ቡድናቸው ተጠቃሚ ይሆን እንደነበርም ገልጸዋል አሰልጣኝ ብርሃኑ።
አፍሪካውያን ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች በአካል ብቃትም በስነ ልቦናም ጠንካራ ናቸው። በርካታ ቡድኖችም ረጃጅም ኳሶችን የሚጫወቱ ናቸው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን ከቲኪ- ታካ ጋር የሚመሳሰል ኳስን መስርቶ እና ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን ነው። በዚህ የጨዋታ ፍልስፍና አዝናኝ እና ውጤታማ ክለብ መሆኑን ለማስመስከር ጭምር ነው ወደ ሞሮኮ የምናቀነው ብለዋል ዋና አሰልጣኙ። የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ በአፍሪካ ታላላቅ እና የተሻሉ የሴት ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ነው። ታዲያ ከዚህ ውድድር እና ከሌሎች ክለቦች ልምድ የሚያገኙበትም ጭምር ነው።
“በውድድሩ የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኝነት (VAR) ተግባራዊ ስለሚሆን ብዙ ልምድ እናገኛለን፤ በአጠቃላይ ከፍ ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ምን እንደሚመስሉ እንማርበታለን” ሲል ተደምጧል አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወቅቱ የኢትዮጵያ አለፍ ሲልም የምሥራቅ አፍሪካ ንግስት ናቸው። በአዲስ አበባ በተደረገው የሴካፋ ዞን የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። ታዲያ በሞሮኮ ቆይታቸውም ኢትዮጵያ ጠንካራ ክለብ እንዳላት የሚያሳዩበት አጋጣሚ እንደሆነ ነው አሰልጣኙ አስተያየታቸውን የሰጡት።
ምንም እንኳ ከአፍሪካ ምርጥ ቡድኖች ጋር የሚወዳደሩ ቢሆኑም የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ እምነት አሳድረዋል። “ የምንሄደው ሀገር ለመጎብኝት ሳይሆን ጥሩ ውጤት ይዘን ለመመለስ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ዝግጅት እያደርግን ነው” በማለት ዋና አሰልጣኙ በስልክ በነበረን ቆይታ ተናግሯል። የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የቅርብ ጊዜ መድረክ ሲሆን ከተጀመረ አራት ዓመታትን ብቻ ነው ያስቆጠረው። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየተሻሻለ መሆኑን የካፍ ኦንላየን መረጃ ያመለክታል።
ባለፉት ሦስት የውድድር መድረኮች የደቡብ እና የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ናቸው የነገሱት። የደቡብ አፍሪካው ማሚሎዲ ሰንዳውን ሁለት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚዎች ናቸው። የደቡብ አፍሪካው የሴቶች ክለብ በ2021 እና 2023 እ.አ.አ ዋንጫውን ማንሳታቸው አይዘነጋም። በፈረንጆች 2022 ደግሞ የሞሮኮው አስፋር ከለብ ዋንጫውን አንስቷል። ዘንድሮ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ለሚሳተፉ ሁሉም ክለቦች የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል። በተለይ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ለሚጓዙ ክለቦች ዳጎስ ያለ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው የአወዳዳሪው አካል መረጃ ያሳያል።
ለውድድሩ አሸናፊ ክለብ 400 ሺህ፣ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለሚጨርስ 250 ሺህ፣ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ለሚያጠናቅቅ 150 ሺህ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ለሚያጠናቅቀው ክለብ የመቶ ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል። ውድድሩ በስምንት የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ የቴሌቭዥን ባለመብቶች እና በማህበራዊ ድረግጽ ይተላለፋል። በኮሮና ቫየርስ ወረርሽኝ ምክንያትም በዝግ ስቴዲየም እንደሚደረግ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል። የደቡብ አፍሪካው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ የሴቶች ክለብ እና የአዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ አስፋር ክለብ ዋንጫውን ያሸንፋሉ የሚል ከወዲሁ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል። አሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ክፍል በመድረኩ ሀገራችንን ለወከለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here