ትርምስ የፈጠረዉ ሽልማት

0
207

የ2024ቱ የባሎን ዶር ሽልማት የዓለም እግር ኳስ ቤተሰቡን ለሁለት ከፍሎ ተጠናቋል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የእግር ኳስ ደጋፊው እና ቤተሰቡ ሮድሪ ይገባዋል! አይ ቬኒሺየስ ነው የሚገባው! የሚሉ ሁለት ጽንፍ ሀሳቦች ላይ እንዲዋልል አድርጎታል።
እ.አ.አ 1956 ጀምሮ በፍራንስ ፉትቦል መጽሔት አማካኝነት እየተሰጠ ያለው ሽልማት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጋር ነው በጥምረት ሽልማቱ የተዘጋጀው። በሁለቱም ጾታዎች ይህን ሽልማት ስፔናውያኖቹ አሸንፈዋል።
የማንቸስተር ሲቲው የተከላካይ አማካይ ሮድሪ ሄርናንዴዝ እና የባርሴሎናዋ አማካይ አይታና ቦንማቲ የወርቅ ዋንጫውን ወስደዋል። በሁለቱም ጾታ ሽልማቱን የአንድ ሀገር ተጫዋቾች ሲያሸንፉ በባሎን ዶር ሽልማት ታሪክ የመጀመሪያው ነው። በውድድር ዓመቱ ከፍተኛ ግብ በማስቆጠር የባየርሙኒኩ አጥቂ ሀሪ ኬን እና የሪያል ማድሪዱ ተጫዋች ኬሊያን ምባፔ አሸናፊ ሆነዋል። አርጀንቲናዊው የአስቲንቪላው ግብ ጠባቂ ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ የያሺን ዋንጫን በተከታታይ በማሸነፍ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል። ስፔናዊቷ አይታና ቦንማቲም ለሁለት ተከታታይ ዓመታታ ነው ሽልማቱን ያሸነፈችው።
በወጣቶች ዘርፍ የሚሰጠውን የኮፓ ዋንጫ የመጪው ዘመን የእግር ኳስ መሲህ ላሚን ያማል አሸንፏል። ላሚን ይህን ሽልማት የወሰደ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ በአሰልጣኞች ዘርፍ የዓለም ምርጥ አሰልጣኝ ተብሎ የዩሀን ክራይፍ ዋንጫን ሲወስድ ቡድኑ ሪያል ማድሪድም የዓመቱ ምርጥ ቡድን ተብሎ ተመርጧል። በሴቶች ዘርፍ ደግሞ የቀድሞዋ የቸልሲ አሰልጣኝ ኤማ ሀይስ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሆና ስትመረጥ፤ ባርሴሎና የሴቶች ክለብ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ ቡድን ሽልማትን ወስዷል።
እ.አ.አ በ2008 ክርስቲያኖ ሮናልዶ የባሎን ዶር ሽልማትን ካሸነፈ በኋላ ሮድሪ ባሎን ዶርን ያሸነፈ የመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋች ሆኗል። ሪያል ማድሪድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሳክቶ ተጫዋቾቹ ባሎን ዶር ሳያሸንፉ ሲቀር የዘንድሮው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የ2024ቱን የባሎን ዶር ሽልማት ብራዚላዊው ቬኒሺየስ ጁኔር እንደሚያሸንፍ ቀደም ተብሎ ግምት ቢሰጠውም ግምቶቹ ፉርሽ ሆነዋል። በወርሀ ነሐሴ የባሎንዶር 30 ዕጩዎች ስም ዝርዝር ይፋ ሲሆን የእግር ኳስ ተንታኞች ብራዚላዊው ባለተሰጥኦ ያሸንፋል በማለት ቅድመ ግምታቸውን ማስቀመጣቸው አይዘነጋም። የተለያዩ የእግር ኳስ ጋዜጦች እና መጽሔቶችም ቬኒሺየስ ጁኔር ሊያሸንፍ እንደሚችል በስፋት ሲዘግቡ ከርመዋል። ይሁን እንጂ የሽልማት ስነ ስርዓቱ ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጣሊያናዊው ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ባሎን ዶሩን ብራዚላዊው ኮከብ እንደማያሸንፍ መረጃውን በማውጣት የሎስ ብላንኮዎችን ቤት አደበላልቆታል።
ያልታሰበ መርዶ የሰሙት ሎስ ብላንኮዎች በቤርናቢዮ ሀዘን እና የተደበላለቀ ስሜት ተፈጥሯል። ብዙዎችም እንዴት ሊሆን ይችላል? ሲል ጠይቀዋል። በእርግጥ የ24 ዓመቱ የፊት መስመር ተሰላፊ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አስደናቂ ጊዜ ማሳለፉ አያጠያይቅም። በአጠቃላይ በሁሉም ውድድሮች 26 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። 12 ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል።
ሎስ ብላንኮዎቹ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የላሊጋ እና የስፔን ሱፐር ዋንጫን እንዲያሳኩ የአንበሳውን ድርሻ ተወጧል። እናም ሪያል ማድሪዶች የሽልማት ስነ ስርዓቱ ሊከናወን ሁለት ቀን እስኪቀረው ብራዚላዊው ባለተሰጥኦ ልጃቸው፤ ሽልማቱን እንደሚያሸንፍ እምነት አሳድረው ነበር። ለፓሪሱ ድግስም ሽር ጉድ እያሉ እንደነበር ተሰምቷል። የኃያሉ ክለብ ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ተጫዋቾችን እና ልዑኩን ጨምሮ በአጠቃላይ 50 ሰዎችን ይዞ ወደ ፓሪስ ለመብረር ዝግጅቱን አጠናቆ እንደነበረ መረጃዎች ወጥተዋል።
ናይኪና ሌሎች የቬኒሺየስ ስፖንሰሮችም በግራን ቪያ በሚገኘው የስፖርት ትጥቅ መሸጫ ሱቃቸውን በወርቃማ ቀለም ለማድመቅ ዝግጅት እያደረጉ ነበር። ባለተሰጥኦው ብራዚላዊ ደግሞ የወርቅ ጫማውን ይዞ ወደ ስፔን ሲመለስ ከቅርብ ጓደኞቹ ጋር ዳንኪራ ለመምታት በሰፊው ዝግጅት በማድረግ ለጓደኞቹ አሳውቋል። ሮድሪ እንደሚያሸንፍ መረጃ ቀድሞ አፈትልኮ መውጣቱ ግን ህልማቸውን ቅዥት አድርጎታል፤ ነገሮችም ፉርሽ ሆነዋል። በሳንቲያጎ ቤርናቢዮም ሀዘን እና የተደበላለቀ ስሜት ተፈጥሯል።
የኃያሉ ክለብ ፈላጭ ቆራጩ ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ከእነ ልዑኩ ወደ ፓሪስ አንጓዝም በማለት ጉዟቸውን ሰርዘዋል። የባሎን ዶር የቀጥታ ስርጭትም በማድሪድ ቴሌቭዥን እንዳይተላለፍ አግደዋል። እንደ ማርካ መረጃ የሪያል ማድሪድ ኩርፊያ በሽልማቱ መስፈርት አማካኝነት፤ ቬኒሽየስ ባያሸንፍ እንኳ፤ ሽልማቱ ከ32 ዓመቱ ሌላኛው የክለቡ ኮከብ ዳኒ ካርቫል እጅ መውጣት አልነበረበትም ባይ ናቸው። የባሎን ዶር ሽልማት ጋዜጠኞች የሰጡት ድምጽ ተስብስቦ የሚሰጥ ሽልማት ነው። ድምጽ የሚሰጡ ጋዜጠኞች በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ የደረጃ ሰንጠረዥ እስከ መቶ በሚገኙ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
የሽልማቱ መስፈርትም ተጫዋቾች በግላቸው ባሳዩት አቋም እና የተጫዋቾች ባህሪ የመጀመሪያው መመዘኛ ነው። የሚጫወቱበት ቡድን ጥሩ እንቅስቃሴ እና ስኬታማነታቸው ሌላኛው መስፈርት ሲሆን፤ ስፖርታዊ ጨዋነትም ከመስፈርቶች መካከል የገኝበታል። ስፔናዊው የቀኝ ተመላላሽ ዳኒ ካርቫል በ2023/24 የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል። ስድስት ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ የላሊጋ፣ የስፔን ሱፐር ዋንጫ ከክለቡ ጋር አሳክቷል።
ከሀገሩ ጋር ደግሞ የ2024ቱን የአውሮፓ ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው። ካርቫል በግሉ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ግብ በማስቆጠር የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል። ታዲያ የሪያል ማድሪድ ክለብ አመራሮች ጉዳዩን ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጋር አያይዘውታል። ፕሬዝደንቱን ጨምሮ የክለቡ አመራሮች እና ደጋፊዎች የክለባችን ተጫዋቾች ሽልማቱን እንዳያሸንፉ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሴራ ጠንስሷል በማለት እየኮነኑት ነው። ሪያል ማድሪድ እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ውድድር ምስረታ ምክንያት ግንኙነታቸው መሻከሩን ተከትሎ ነው ሎስ ብላንኮዎች ቅሬታቸውን ያቀረቡት።
ብራዚላውያን እና የቬኒሺየስ ጁኔር ደጋፊዎች ደግሞ ወትሮም ዘረኝነትን በደማቸው ባሰረጹ አውሮፓውያን ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት እንዳደረሱበት በማስታወስ፤ ጥቁር በመሆኑ የባሎን ዶር ሽልማቱን ተዘርፏል እያሉ ነው። በ2003/04 የውድድር ዘመን የቀድሞው መድፈኛ ቴሪ ዳንኤል ኦነሪ የባሎን ዶር ሽልማቱን በክሮሺያዊው የቀድሞ የጁቬንቱስ ተጫዋች ፓቬል ኔድቪድ የተዘረፈበትን በማስታወስ ዘንድሮ የቬኒሺየስን ጉዳይ ከቆዳ ቀለም እና ከማንነቱ ጋር አያይዘውታል።
ቬኒሽየስ በቲዊተር ገጹም ይህንኑ መልዕክት አስተላልፏል። “ዐስር ጊዜ ምርጫ ቢደረግ ዐስሩንም የማሸንፍ እኔ ነኝ፤ ግን ሸላሚዎች መሸለም አልፈለጉም” በማለት ትችቱን ሰንዝሯል። በሀገሩ ብራዚል ምድርም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። አንዳንድ የመረጃ ምንጮች ደግሞ ከሽልማት ስነ ስርዓቱ ቀደም ብሎ ሪያል ማድሪድ በሜዳው በባርሴሎና አራት ለባዶ በተሸነፈበት የኤልክላሲኮ ምሽት፤ ቬኒሺየስ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ የሽልማቱ አዘጋጆች ሀሳባቸውን ቀይረው የወርቅ ጫማው ለማንቸስተር ሲቲው ሮድሪ ሄርናንዴዝ መስጠታቸው እየተወራ ነው።
ስፔናዊው የተከላካይ አማካይ ባሳለፍነው ዓመት በሁሉም ጨዋታዎች 63 ጨዋታዎችን አድርጓል። በእነዚህ ጨዋታዎች 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል። ሮድሪ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የፕሪሚየር ሊግ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ፣ የአውሮፓ ሱፐር ዋንጫ፣ ኮሚኒቲ ሺልድ እና ከስፔን ብሄራዊ ቡድን ጋር ደግሞ የአውሮፓ ዋንጫን አሳክቷል።
በግሉ ደግሞ የአውሮፓ ዋንጫ የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ሲሸለም በዓለም ክለቦች ዋንጫም አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህ ቁጥራዊ መረጃም በ2018 እ.አ.አ ክሮሺያዊው የሪያል ማድሪዱ የመሀል ሜዳ ሞተር ሉካ ሞድሪች ባሎን ዶርን ካሸነፈበት ወቅት ጋር ተቀራራቢ መሆኑን የስካይ ስፖርት መረጃ ያመለክታል። የ28 ዓመቱ ስፔናዊው ኮከብ የማንቸስተር ሲቲ የልብ ምት ነው። የላቀ ኳስ የማቀበል ክህሎቱ፣ የማይታመን የፈጠራ ክህሎቱ፣ እና በጠንካራ የአካል ብቃቱ አሁን ላይ በቦታው ካሉ ቀዳሚ የእግር ኳስ ኮከብ ስለመሆኑ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ይመሰክሩለታል።
ተጫዋቹ የፔፕ ጓርዲዮላ ታክቲክ ዋነኛው መሳሪያ እንደሆነም ይነገራል። በቪያሪያል እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጎልብቶ በኢትሀድ ያንጸባረቀው ኮከብ፤ ታታሪ እና ጠንካራ ሠራተኛ ነው። ትኩረቱም እግር ኳስ ሙያው ላይ ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል። ሮድሪጎ ሄርናንዴዝ ምንም ዓይነት የማህበራዊ የትስስር ገጽን አይጠቀምም። በየጊዜው ደም ስለሚለግስ እንደ ብዙዎቹ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሰውነቱንም በንቅሳት አላዥጎረጎረም። ምስጉን ስብዕና ያለው፣ የኋላ ታሪኩን የማይረሳ አስደናቂ ኮከብ ነው። የተቀናጣ እና የበዛ ምቾት እንደማይማረከውም የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል።
ከእግር ኳሱ ጎን ለጎን በሀገሩ ስፔን ከካሴቴሎ ዴ ላ ፕላን በሚገኝው ዣዋም ዩንቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር እና አመራር የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። በወቅቱ አትሌቲኮ ማድሪድ ሳምንታዊ 120 ሺህ ዩሮ ደሞዝ ይከፈለው የነበረ ቢሆንም፤ በዩንቨርሲቲው ከተማሪዎች ጋር መኗሪያ ተጋርቶ ይኖር እንደነበር ዘ ሰን አስነብቧል። የደሞዙን አንድ አራተኛ ለበጎ አድራጎት ድርጅት የሚሰጥ ሲሆን ከአንዲት ስፔናዊት አዛውንት ጋርም የበጎ አድራጎት ድርጅት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል። ሮድሪ አምስተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከአርሴናል ጋር በነበራቸው መርሀ ግብር ከባድ ጉዳት የገጠመው በመሆኑ ከውድድር ዓመቱ ውጪ መሆኑ ቀደም ብሎ ተዘግቧል። ታዲያ ለማገገም ረጅም ጊዜ ይወስድበታል የተባለ ሲሆን በባሎንዶር ሽልማት ስነ ስርዓቱም በክራንች በመታገዝ ታድሞ የወርቅ ጫማውን ወስዷል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here