“ወጣቶች የኢኮኖሚ የበላይነት ሊኖራቸዉ ይገባል ብየ አምናለሁ”

0
145

የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

ተመራማሪ፣ ነጋዴ፣ መሃንዲስ፣ የሥራ ፈጣሪ እና የሌሎች ሙያዎች ባለቤት ናቸው:: በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን የሥራ ፈጣሪዎች የሚያወዳድረው የነጋድራስ መርሃ ግብር ዳኛ ናቸው፤ በውድድሩ ላሸነፈ 100000 ብር ይሸልማሉ፡- አቶ ቢጃይ ናይከር::
በስማቸው የተሰየመ ቢጃይ ኢትዮ ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግ የተባለ ድርጅት መስራችና ስራ አስፈጻሚ ናቸው። በ2015 ዓ/ም በንግድ ስራ ዘርፍ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ የነበሩት አቶ ቢጃይ በድርጅታቸው ስራ ያልያዙ ወጣቶችን ያሰለጥናሉ። ለወጣቶች የሚሰጡትን የተግባር ስልጠና እንዲሁም ስራ መጀመርያ ገንዘብ ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ።
“እኔ 100 ሺህ ብር የምሰጠው ዘር ነው። ዘር ለገበሬ ሲሰጥ ማሳውን ይዘራዋል እንጂ አስፈጭቶ አይበላውም። ማሳውን የምትዘሪበት ደግሞ ከምታፍሺው ምርት ትንሹን ነው፤ እና ዝቅተኛውን ነው። ስለዚህ እኔ ዘር ነው የሰጠሁት። ይሄ ፈንድ የዘር ፈንድ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ያ ሰው ከእናቱ ከማኅበረሰቡ ከሌላ ሰው ጨምሮ ሀሳቡን ሊያደርግበት ይችላል፤ ወይም በራሱ ሊሰራበት ይችላል” በማለት ስለሚሰጡት ፈንድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ፈንዱ ‘ብድር፣ ኢንቨስትመንት ወይስ ስጦታ’ ሲል ቢቢሲ የጠየቃቸው አቶ ቢጃይ ናይከር “ስጦታ” ነው” ሲሉ መልሰዋል። በአጠቃላይ ውድድሩ መነቃቃትን ፈጥሯል የሚሉት አቶ ቢጃይ፤ 20 ሺህ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ፈንዱን ለማግኘት እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል። አሚኮ ከአቶ ቢጃይ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ እነሆ::

አሁን ያሉት ቢጃይ እንዴት ተፈጠሩ?
ቢጃይ የተፈጠረው አቃቂ ውስጥ ነው:: ምክንያቱም እኔ የሕይወትን ጣዕም ያወኩት፣ አኗኗርን የለመድኩት አቃቂ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው:: አቃቂ ሰፊ የሆነ የባቡር ጣቢያ ነበረ:: በባቡር መንጠልጠል፣ በባቡር መጓዝ፣ በባቡር ንግዶች ሲካሄዱ ማየት የመሳሰሉ ነገሮች ትልቅ ልምድ ሆነውኛል::
ሁለተኛው ደግሞ አቃቂ ውስጥ በጣም ትልቅ ገበያ አለ:: በዙሪያ ያሉ ከሁሉም ማኅበረሰብ የተወጣጡ ገበያተኞች የሚያቆሙት ገበያ ነው:: ያንን በጥሩ ሁኔታ ውጥንቅጥ የሆነ ገበያ ማየት እና በውስጡ መገኘት የራሱ የሆነ የሥራ ፈጣሪነት ባሕሪ ይሰጣል:: ለምሳሌ “አባባ እስኪ እግርዎትን?” የሚባል ሽቀላ ነበር:: አትክልቶች በመኪና መጥተው ሲወርዱ ተራርፎ መሬት ላይ የሚወድቅ ድንች ወይም ካሮት አሊያም ሌላ አትክልት ይኖራል:: እሱን ከመሬት ላይ አንስቶ ጉልት አቁሞ (መድቦ) መሸጥ ነው:: ያንን አትክልት መሬት ላይ ወድቆ በድንገት ሰው ረግጦት ከሆነ “አባባ እግርዎትን ያንሱልኝ?” ብሎ አትክልቱን በመውሰድ ንግድ መሥራት ነው:: ይህ ትልቅ ሥራ ፈጠራ ነው:: ይህን ወደ ዘመኑ ስናመጣው የወዳደቁ እና ተረፈ ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ገበያ እንደገና ማምጣት ማለት ነው::
አቃቂ ትልልቅ ወንዞች አሉ፤ መዋኘት የጀመርኩት እዛ ነው:: ውኃ ሰው መግደል እንደሚችል ይዋኙ የነበሩ ሰዎች ሞተው ያወኩት አቃቂ ነው:: ሳማ እና ቁልቋል እንደሚያቃጥሉ ያወኩት እዛው ነው:: ባቡር ስትንጠለጠል እግርህ ሊቆረጥ አሊያም ልትሞት ትችላለህ፤ ይህን ያወኩት አቃቂ ነው፤ ይህ አሰቃቂው ነገር ነው::
አቃቂ ውስጥ ትምህርት ቤቶች እና እምነት ተቋማት በብዛት አሉ:: በእናቴ በኩል ጥብቅ የሆነ የኦርቶዶክስ እምነት ቢኖርም ከጓደኞቼ ጋር ተከትየ ሄጄ ቁርአን ቀርቻለሁ:: አባቴ የሂንዱ እምነት ተከታይ ነው:: ከ30 ሚሊየን በላይ አምላክ አለን ብለው ያምናሉ:: ስለዚህ የአንተ አንድ ያልከው አምላክ የእነሱም አምላክ እንደሆነ ያምናሉ:: ስለዚህ እናቴ በኦርቶዶክስ እምነት መሠረት ተጠመቅ ስትለው ችግር የለበትም:: አባቴ ለእኔም የእምነት ነጻነት ይሰጠኝ ነበር::
አቃቂ ከእምነት፣ ከንግድ፣ ከእንቅስቃሴ፣ የተለያየ ማኅበረሰብ ከማስተናገድ እና ከሌሎች ነገሮች አንጻር ትልቅ ትምህርት ቤት ነበር:: ከሕንድ፣ ከኩባ፣ ከጃፓን የመጡ ሰዎች የሚኖሩበት እና ትልልቅ ፋብሪካዎች የነበሩበት ነው:: ይህ ደግሞ ዓለም አቀፋዊነትን ያሰርጻል:: በፊት 34 ትልልቅ የኢትዮጵያ ፋብሪካዎች የነበሩት አቃቂ ውስጥ ነው:: የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበርም መሠረቱ አቃቂ ይመስለኛል:: ይህ ማለት ደግሞ አቃቂ የፖለቲካ ትልቅ ቦታ መሆኑን ትረዳለህ::
አቃቂ የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ያለበት ቦታም ነው:: አማራው፣ ኦሮሞው ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ሶማሌው፣ ደቡቡ… የሚኖርበት ነው:: ስለዚህ ብዝሃነትን አውቄ ያደኩበት ነው:: ልዩነትን ማክበር ተምሬአለሁ::
አቃቂ የግብርና፣ የኢንደስትሪ፣ የንግድ እና የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሰፊው የነበረበት ነው፣ የሀገር መከላከያ መሣሪያ ቴክኖሎጂዎች የሚመረቱበትም ነበር:: የቴክስታይል፣ የብረት ኢንደስትሪዎች ነበሩ:: ስለዚህ ቤጃይ ማነው? ሲባል የእነዚህ ነገሮች ሁሉ ስሪት ነው ማለት ነው::

የትምህርት ሁኔታዎ ምን ይመስላል?
ትምህርት የጀመርኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ኢትዮጵያ ተምሬያለሁ:: ከዚያ ወደ ሕንድ ሄጄ ለተወሰነ ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከተማርኩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሻለሁ:: ቀጥሎ በጂማ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪየን እንደገና በቢዝነስ አስተዳደር ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪየን ይዣለሁ::
በአባቴ በኩል ዘመዶቼ ትልልቅ ነጋዴዎች በመሆናቸው ወደ ቢዝነሱ እንድገባ አድርጎኛል:: እናቴ ደግሞ ትምህርት ትወዳለች፤ ትምህርት እንድማር ነው የምትፈልገው፤ በዚህ ምክንያት ንግዱን እና ትምህርቱን አብሮ ማስኬድ ችያለሁ:: በኢትዮጵያ እና በሕንድ ሀገር የዶክትሬት ዲግሪየን ሁለት ጊዜ ጀምሬ ነበር:: ነገር ግን ውስጤ ወደ ንግዱ ዓለም መግባት እንዳለብኝ ነገረኝ:: ስሜቴም እሱ ሆኖ አገኘሁት:: እንደ ቀድሞ ሰዎች ረጅም እድሜ ላይኖረኝ ይችላል:: ትምህርቱ እዚ ከደረሰ ቢዝነሱን ልሥራ አልኩ:: ትምህርት የባሕሪ ለውጥ ማምጣት እና ራስን ማሰልጠን ነው:: ብዙ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት ከማሳተም አልቦዘንኩም:: ከትምህርቱ ያን ያክል ራኩም አይባልም:: በማሕበራዊ መገናኛውም ሌሎችን አስተምራለሁ፤ መረጃዎችን አጋራለሁ::

ተቀጥረው ለምን ያክል ጊዜ ሠርተዋል?
በቅጥር የሰራሁት ሁለት ዓመት አካባቢ ነው:: በሁለት ዓመት ውስጥ ግን ከ60 ቦታዎች በላይ ገብቼ ሠርቻለሁ:: ትንሹ አራት ሰዓት ትልቁ ሰባት ወር ያክል በቅጥር ሠርቻለሁ:: የተለያዩ ዘርፎች ላይ መሥራት እችል ነበር:: በዚህ አጋጣሚ ያሰበሰብኳቸው ደሞዞች ሁሉ ነበሩኝ:: ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት በኋላ ተቀጥሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠርኩት በ2000 ብር ነው:: ሳሙና ፋብሪካ እገባለሁ፣ እንጨት ፋብሪካ እገባለሁ፣ ብረት ፋብሪካ እገባለሁ፤ ስለ አሠራሩ ካወቅኩ በኋላ የመቀጠል ፍላጎቴ ይጠፋል:: ለሰባት ወራት ግን ቀልቤን ይዞ በአንጻራዊነት ለረጂም ጊዜ እንድቆይ ያደረገኝ የመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ነው::
የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ላይ የሳይት ስራ አስኪያጅ ነበርኩ:: በዚያም ለነዳጅ የሚሆነው የኢታኖል ማቀነባበሪያ ይገነባል:: ያንን ለማስፈጸም እና ፕሮጀክቱን እውን ሆኖ ለማየት ከነበረኝ እልህ የተነሳ ለሳባት ወራት በፋብሪካው በቅጥር ቆይቻለሁ:: በቅጥር ረጅሙ የሥራ ጉዞየ ይህ ነው::

ለአራት ሰዓት ተቀጥረው የሠሩበትን አጋጣሚ እስኪ ያጫውቱን?
እዚሁ እኛው አካባቢ ነው፤ ፋብሪካ ነው:: በደርግ ጊዜ የነበሩ አሮጊት እና ሽማግሌዎች የነበሩበት ነው(በእድሜ ለገፉ ሰዎች ክብር እየነሳሁ አይደለም) በፋብሪካው የቴክኒክ ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ነው የገባሁት:: የተሰጠኝ ቢሮ ያምራል:: እንደገና ሠራተኞቹ አብዛኞቹ ሽማግሌ እና አዛውንት ስለሆኑ በጣም አክባሪዎች ነበሩ:: የቴክኒካል ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ድርጅቱን ወደ ዘመናዊነት ይቀይራል ተብየ ነው የመጣሁት::
ነባር ባለሙያዎቹ ማሽኑ ላይ ረጃጅም ገመድ ያስራሉ፤ ማሽኑ ሲጮህ ገመዱን ሳብ ሲያደርጉት ድምጹን ይቀንሳል:: እንደገና ሲጮህ ውኃ ጠብ ያደርጉበታል፤ ያኔ ጸጥ ይላል:: ይህን ሳይ እኔ የምቀይረው ነገር እንደሌለ ተረዳሁ፤ ሰዎቹ ባላቸው አቅም በጥሩ ሁኔታ እያስኬዱት ነው:: ስለዚህ እዚህ ውስጥ ገብቶ ማምቦጫረቅ አግባብ አይደለም፤ እኔ እንደማላስፈልግ ተረዳሁ፤ ጠዋት ቢሮ ተሰጥቶኝ ለምሳ እንደወጣሁ በዛው ጠፋሁ::

ወጣቶች እና ንግድን እንዴት ያዩዋቸዋል?
የኔ አሪፉ ሙዴ ከወጣቶች ጋር ነው የምሆነው:: ወጣቶች የኢኮኖሚ የበላይነት ሊኖራቸው ይገባል ብየ አምናለሁ:: ትምህርት እስከምትሄደው ድረስ በቂ ነው:: ነገር ግን ወጣቶች የሀብት ባለቤት መሆን መቻል አለባቸው:: ይህ ማለት ገንዘብ በ20 ዓመት ልብ በ40 ዓመት ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ይቀራረባል:: አሁን ላይ ልጆች በ14 ዓመታቸው ላይ እንደ ድሮው የ20 ዓመት ልጅ ወይም ከዛ በላይ ብስለት አላቸው:: አሜሪካ ስትሄድ እኮ መንጃ ፈቃድ በ16 ዓመት እንድታወጣ ይፈቀድልሀል::
በትንንሽ እድሜያቸው በበየነ መረብ ንግድ እየሠሩ ቢሊየነር የሆኑ አሉ:: ስለዚህ ልብን በ40 ዓመት ከምናረገው ለምን በ30 በ20 አናመጣውም:: አፍሪካ ውስጥ ጦርነት ሲሆን በ14 ዓመትህ ትመለመላለህ። ሥራ እና ሀብት ሲሆን ግን 18 ካልሞላህ ይባላል:: አደጋ ያለውን ነገር እንዳውም ያስተውላሉ የሚባሉት አዋቂዎች ቢገቡበት እና ወጣቶች ብዙ አደጋ በሌለበት ስሜታቸውን በማይጎዳ ንግድ መሥራት ቢችሉ ዘመኑ ይፈቅድላቸዋል እላለሁ::
ልብ በ40 ዓመት የሚባለውን መጠበቅ አያስፈልግም:: ያ እድሜ መሞቻ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም የከተማ ኑሮ አስጨናቂ ነው:: ብዙ ጊዜ ረጃጅም ዛፎች እና እድሜ ጠገብ ሰዎችን የምናገኘው በእምነት ተቋማት ነው:: በሌላ በኩል ፖለቲከኞችም ረጅም እድሜ ይኖራሉ:: ያ ማለት ጭንቀት የለባቸውም ማለት ነው:: ወጣቶች ግን ሕይወታቸው አስጨናቂ ሆኖ እድሜያቸው ሲያጥር እናያለን:: ስለዚህ ሕይወት አጭር ነች፤ የነገን ሳይሆን ዛሬን ነው መኖር ያለብን::
ይቀጥላል

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here