ሀገር ለመስራት የሚሆነንን አቅምና እውቀት ሀገር ለማፍረስ አናውለው!

0
158

ዓለም ስለሰላምና ስለአብሮ መኖርና ለመስበክ ከከንፈር መምጠጥ አልፎ ከልብ የመነጨ ፍላጎት ባለማሳየቱ በየቦታው የጦርነትና የግጭትን ዜና መስማት ከብስራት እኩል ጆፘችን የለመደው መርዶ ሆኗል፡፡
በተለያዬ ቦታ በተካሄዱት ጦርነቶች መሃል ካሉት ወታደሮች እኩል በተመሳሳይ ሰዓትና ቀን የተተኮሰውን መሳሪያ ድምጽ የደረሰውን ጉዳት እንዲሁም የፈረሰውን ሀገር ዓለም እኩል ተመልክቷል፡፡ ትናንት ዓለም በጉጉት ለመጎብኘት ዓይኑን የማይነቅልባቸው፤ በጎብኝዎች የረ³ም ጊዜ እቅድ ውስጥ ለመታየት ምኞት የነበሩ ውብ ሀገራትን ታሪክ በቅጽበት ወደፍርስራሽ የቀየረ፤ የሰዎችን ህልም ከመኖር ወዳለመኖርና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያኖረ ክስተት ነው ጦርነትና ግጭት፡፡ ከተደላደነ ኑሮ ወጥቶ መጠለያ ብርቅ ሆኖበት በየጥጋጥጉ የተበተነን ቤተሰብ ስቃይና እንግልት ዓለም ዓይኑን ሳይከድን ጆሮውን ከፍቶ እያየ የኔስ ተራ መች ይሆን እያለ በስጋት እንዲኖር ያስገደደ ክስተት ሆኗል፡፡
ከጦርነትና ግጭት ጋር ተያይዞ አብሮ የመጣውን የኑሮ ውድነት እንደ ዓለም አብረን እየተቸገርነው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ጦርነት ለአእምሮ ጤና ችግር የመጋለጥ እድልን ይጨምራል፡፡እንደ ዓለም አቀፉ ሳይካትሪክ ማሕበር አንድን አሰቃቂ ምስል በማሕበራዊ ሚዲያ በቀናት ወስጥ ከ6 መቶ ሚሊየን ጊዜ በላይ ተደጋግሞና ተቀባብሎ የመታየት እድል አለው፡፡ ይህ ቅብብሎሽ ደግሞ ከማየት ያለፈ የዓዕምሮ ጤና ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፎ ያልፋል ይላል ማሕበሩ፡፡ በጦርነቱ መካከልም እንሁን በሩቅ በሌሎች የማሕበራዊ ሚዲያ አማራጮች እንመልከተው አሊያም እንስማው ከመቶ ሰዎች አስሩ በዓዕምሮ ሕመም የመጠቃት መጥፎ እድል ይገጥማቸዋል ይላል፡፡
በግጭትና በጦርነት የሚደርሰውን ሰብዓዊ እልቂት፤ቁሳዊ ውድመት፤ስነልቦናዊ ስብራት፤ ማሕበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት እንዲሁም ቋሚ ጠባሳን ለማከም ሀገር የሰራንበትን ያህል ረጅም ጊዜ ቢሰጥ እንኳ የነበረን ለመመለስ ቀርቶ የሆነውን ለመርሳት፤ የምንታመመውን ህመም ለማከም ልዩ ብርታት ይጠይቃል፡፡
ጥያቄ አለኝ ያለን ማዳመጥና ተነጋግሮ መስማማት፤ ተደማምጦ መፍትሔ መፈለግ፤ ለጦርነት ከሚወጣው ጉልበት በታች ስክነትና ስለነገ ማሰብን ብቻ የሚጠይቅ መንገድ ሆኖ ሳለ የመሪዎች እልህ አስጨራሽ የጉልበትን መንገድ መምረጥ ዓለምን እኩል ዋጋ እያስከፈለ ያለ አማራጭ ሆነ፡፡ ዓለም በየጊዜው የራሱን ባለጊዜ እያመጣ ህዝብን የባለጊዜ ጉልበት መፈታተኛ መድረክ አደረገው፡፡
እኩል በታመመና ጤናማ ባልሆነ ዓለም ውስጥ መኖር ሰላምንና ጤናን ሳይሆን የታወከና ስለነገው ሳይሆን የዛሬን ብቻ ላሸንፍ በሚል አዙሪት ውስጥ ያለ መፍትሔ አልባና የተበተነ ትውልድ የሞላት ዓለም እንድትሆን የበኩልን መጥፎ አሻራ ከማስቀመጥ አይተናነስም፡፡ ሀገርን ለመስራት እንዴት እናሸንፍ ከሚል በሃይልና በጉልበት ከተሞላ መንገድ ይልቅ እንዴት ሀገር እንስራ የሚለው ሃሳብ የሚጠይቀው አቅም መጠቀም ለሀገርም ለህዝብም ይበጃል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here