የመስኖ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

0
147

የተሻለ የመስኖ ልማት ማልማት ከሚችሉ ዞኖች መካከል የሰሜን ጎጃም ዞን አንዱ ነው። ለመስኖ ልማት ምቹ መሬት እና በርካታ ወንዞችን የያዘ ነው።
በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሁለቱ ይጎማ ቀበሌ መስኖ እያለሙ እንደሚገኙ የነገሩን አርሶ አደር ጥሩነህ አላምር አንዱ ናቸው። በመኸሩ ወቅት በይዞታ እና በጥማድ መሬት በቆሎ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ በዋናነት አምርተዋል። በዚህ ወቅት የጤፍ ሰብላቸውን ሙሉ በሙሉ ሰብስበዋል። የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብም ለመስኖ የሚሆነውን መሬት እያረሱ መሆኑን በስልክ ነግረውናል።
አርሶ አደር ጥሩነህ ባለፈው ዓመት አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም በአራት ጥማድ መሬታቸው ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ ስንዴ እና ሌሎች ሰብሎችን ለማምረት ማሳቸውን የማለስለስ ሥራ ላይ ናቸው። ለዚህም በአካባቢው ለመስኖ አገልግሎት የሚውል የመስኖ ግድብ መኖሩን አስረድተዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ አለኸኝ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት- በተያዘው የምርት ዘመን በነባር እና በአዲስ 27 ሺህ 769 ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 19 ሺህ 500 ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት አቅዷል። በልማቱም 84 ሺህ 200 አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 13 ሺህ 63 ሔክታር መሬት ታርሷል። ከታረሰው ውስጥ ደግሞ 6 ሺህ 919 ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል። ለዚህ ዕቅድ መሳካትም የግብዓት እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ከመኸር ሰብል ስብሰባው እና ጥበቃው ጎን ለጎን ለመስኖ ልማት በትኩረት እንደሚሠራም አስረድተዋል። አርሶ አደሩ ማሳውን በመለየት እያረሰ እና እየዘራ መሆኑንም ተናግረዋል። ለመስኖ ልማቱ ጥቅም ላይ የሚውል 111 ሺህ 418 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል። እስካሁንም ከ37 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል።
ለመስኖ ልማቱ ባሕላዊ ወንዝ ጠለፋ፣ የምንጭ ማጎልበት እና ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን ወደ ሥራ በማስገባት የሚሠራ ይሆናል ነው ያሉት። አምስት ሺህ 482 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ማሰራጨትም ተችሏል ብለዋል።
በዞኑ በአንደኛ ዙር መስኖ አንድ ሚሊዮን 368 ሺህ 372 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውስጥ 780 ሺህ ኩንታሉ ከስንዴ ልማት የሚጠበቅ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here