ከመኸሩ ባሻገር

0
163

የህዳር  2 ቀን 2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ከመኸር እርሻ ሥራ በተጨማሪ የመስኖ ልማትን በትኩረት እየሠራች ነው። ከክረምት ዝናብ ጥገኝነት ባለፈ የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር የውኃ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም በዓመት ሁለት እና ሶስት ጊዜ ለማልማት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። ሆኖም ካላት ሰፊ መሬት እና የውኃ ሀብት አኳያ የሚጠበቀውን ሥራ አከናውናለች ማለት አያስደፍርም። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንዳመላከተው በኢትዮጵያ አሥር ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ መልማት የሚችል ቢሆንም እ.አ.አ እስከ 2024 እየለማ የሚገኘው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ ነው:: በአማራ ክልልም ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ለመስኖ ልማት ምቹ ቢሆንም እስካሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ግን ከ11 በመቶ እንደማይበልጥ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። ለመስኖ ልማት ምቹ የሆነውን መሬት በሙሉ አቅም መጠቀም ካላስቻሉት ምክንያቶችም የመስኖ መሠረተ ልማቶች አለመስፋፋት፣ የበጀት እጥረት፣ የግንዛቤ ፈጠራ በትኩረት አለመሰራት እና ሌሎች ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው። ሆኖም አርሶ አደሩ ከመኸር የግብርና ሥራው በተጨማሪ በመስኖ የተለያዩ ሰብሎችን እንዲያለማ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል። አርሶ አደሮችም በየአካባቢያቸው የሚያገኙትን የውኃ ሀብት በመጠቀም የመስኖ ልማት ለማከናወን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን ለበኩር ጋዜጣ ሐሳባቸውን በስልክ አጋርተዋል። ከቅድመ ዝግጅቶቻቸው መካከልም የመሬት ልየታ፣ የማሳ ዝግጅት፣ ደጋግሞ ማረስ፣ የግብዓት እና የዘር ዝግጅት፣ የውኃ ጠለፋ… እና ሌሎች ተግባራት ይገኙበታል።
አርሶ አደር ደመላሽ አጥናፉ የምሥራቅ ጎጃም ዞን የቢቡኝ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በመኸር ወቅት በአምስት ጥማድ መሬታቸው በቆሎ፣ የቢራ ገብስ፣ ባቄላ እና ስንዴ አምርተዋል። የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑም ነግርዉናል። አርሶ አደር ደመላሽ በዓመት ሁለት ጊዜ ለማምረት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። ካሁን በፊት የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ በማከናወን በትንሽ መሬት ላይ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ነግረውናል። አርሶ አደር ደመላሽ በወቅቱ ማረስ እና መዝራት ከዛም በመንከባከብ ለፍሬ ማብቃት ይገባል ብለዋል። ለመስኖ ልማት የሚያገለግል የውኃ ተፋሰስ የቦይ ጠረጋ ሥራን ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ቀድመው አዘጋጅተዋል። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለመስኖ ልማት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑንም ነግረውናል። “የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀሜ የመሬቴ ለምነቱ ተጠብቋል እንዲሁም የተሻለ ምርትም እያገኘሁ ነው” ብለዋል። በቀጣይም የበቆሎ ሰብላቸውን በመሰብሰብ ለመስኖ ዘር እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመስኖ ልማት ላይ በትኩረት በመሥራቴ የተሻለ ምርት እያገኘሁ ነው” ብለዋል። አርሶ አደሩ እንዳሉት የመስኖ ልማት በማልማት ራሳቸውን ከመጥቀም ባለፈ ለገበያም እንደሚያቀርቡ ነው የተናገሩት።
በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪው አታላይ ፀጋ ሌላው ለመስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ሐሳባቸውን በስልክ ያጋሩን አርሶ አደር ናቸው። በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አታላይ ግብርና ለእርሳቸው ህይወታቸው እና መሠረታቸው ነው። በመኸር (በክረምቱ) በአስራ ሁለት ጥማድ መሬታቸው የተለያዩ ሰብሎችን ሸፍነዋል። ከዚህም መካከል ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ በቆሎ እና ኑግ በስፋት የተመረቱ ሰብሎች ናቸው። በምርት ዘመኑ የተሻለ ግብዓት በመቅረቡ፣ በወቅቱ በመዝራታቸው እና ምቹ የዝናብ ሥርጭት በመኖሩ የሰብሉ ቁመናው ያማረ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የጤፍ ሰብላቸውን ሰብስበው ጓያ ዘርተዋል። በቀጣይም ሽንኩርት፣ ድንች እና ስንዴ ለመዝራት ተዘጋጅተዋል። አምስት ጥማድ መሬታቸውንም በመስኖ ለማልማት አቅደዋል::
ወደፊት መንግሥት በቂ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂ ቢያቀርብ ከዚህ የበለጠ አምርቶ ለገበያ ማቅረብ እንደሚቻልም አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017 ዓ.ም ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል:: በምርት ዘመኑ በዞኑ በመስኖ ልማት በዘር የሚሸፈነው ከ29 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት እንደሆነ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ተናግረዋል:: እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ አርሶ አደሩ ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት በመሰብሰብ ለመስኖ ዘር እንዲያዘጋጅ ርብርብ እየተደረገ ነው። የመሬት ልየታ፣ የመስኖ ካናል (ቦይ) ጠረጋ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ሥራዎች በቅድመ ዝግጅት የተከናወኑ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት 29 ሺህ 740 ሔክታር መሬት (25 ሺህ 861 ሔክታር መሬት በነባር እና 3 ሺህ 879 በአዲስ) በመስኖ ለማልማት መታቀዱን ነው መምሪያ ኃላፊው በስልክ ለበኩር የተናገሩት። በዘር ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውስጥ 16 ሺህ 15 ሔክታር መሬት በመስኖ ስንዴ የሚሸፈን መሆኑን ጠቅሰዋል::
በዕቅድ ከተያዘው ከ29 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም 5 ሺህ 571 ሔክታር መሬት ታርሷል። ከአራት ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል። በመኸር ተዘርተው ምርቱ የተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ቀድመው ወደ እርሻ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። የታቀደውን መሬት በዘር ለመሸፈን መልካም ጅማሮ ቢሆንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ለውጤታማነቱም 40 ሺህ 380 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ በዕቅድ ተይዟል።
ለመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ቀሪ ግብዓቶች እንዲቀርቡ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል። የምርጥ ዘር እጥረት መኖሩን የገለጹት መምሪያ ኃላፊው ሆኖም ግን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በተለይም የአካባቢውን ዘር አበጥሮ በመጠቀም መዝራት አንዱ የመፍትሔ አካል መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት ለአርሶ አደሮች ከተሰራጩት 7 ሺህ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች በተጨማሪ ሌሎች 335 የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች በአዲስ መቅረቡን አስታውቀዋል። አርሶ አደሩም በራሱ ወጪ እየገዛ የመጠቀም ልምዱ እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸዋል። ይህም ለመስኖ ልማት ውጤታማነት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ ማሳውን በወቅቱ ማረስ፣ መዝራት፣ የሚፈሱ ወንዞችን በአግባቡ ገድቦ መጠቀም፣ ለመስኖ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ቀድሞ መያዝ፣ የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን እና ሌሎች ለመስኖ ሥራ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ በማከናወን የተሻለ ምርት ማምረት ይጠበቅበታል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ከመስኖ ልማት ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም በመስኖ ከሚለማው የእርሻ መሬት 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል:: በቢሮው የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና መስኖ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት በ2017 ዓ.ም 342 ሺህ 480 ሔክታር መሬት በመስኖ በማልማት 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ከዚህ ውስጥ 250 ሺህ ሔክታር መሬት በስንዴ እንደሚሸፈን ተናግረዋል። ለዚህም በቅድመ ዝግጅት ወቅት በመስኖ የሚለማውን መሬት የመለየት፣ የካናል ጠረጋ እና ጥገና ሥራ፣ ለተሳታፊ አርሶ አደሮች ግንዛቤ የመፍጠር፣ የግብዓት አቅርቦትን የማፋጠን፣ የአትክልት ዘርን በመደብ የማዘጋጀት፣ አርሶ አደሮችን የመለየት እና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜም በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 54 ሺህ 984 ሔክታሩ ታርሷል:: ከዚህ ውስጥም 34 ሺህ 621 ሔክታሩ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል። ካሁን በፊት ከነበረው ልምድ አኳያ ለመስኖ ልማቱ ቀድሞ ወደ ተግባር መገባቱን ነው የተናገሩት። ከታረሰው ውስጥም 24 ሺህ ሔክታሩ ለስንዴ ዘር መታረሱን እና 1 ሺህ 861 ሔክታሩ በስንዴ ሰብል መሸፈኑን አብራርተዋል::
የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነት ለማሳደግም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ገልጸዋል። በቅድመ ዝግጅት የተሠሩ ሥራዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ፣ የመሬት ልየታ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ የተሻለ የምርት ጭማሪ ለማግኘት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። ለመስኖ ሥራው ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋል። የአፈር ማዳበሪያ ከተከማቸበት ቦታ ወደ አርሶ አደሩ የማዘዋወር ሥራ እየተሠራ ነው። ሆኖም በፍጥነት እና በወቅቱ ለማድረስ ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ የእርጥበት ጊዜው ሳያልፍ እና የውኃ መጠኑ ሳይቀንስ ፈጥኖ መዝራት እንዳለበት አመላክተዋል። የግብይት፣ የነዳጅ አቅርቦት፣ የሰብል ጥበቃ፣ እና የተባይ ቁጥጥር ሥራዎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። በግብርና ሥራ እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራት በመደገፍ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here