
የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም
ከፈጣሪ በታች በበሽታ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችልን ሞት የሚረቱ፣ ከተማን የሚገነቡ መሀንዲሶች፣ ሕይወትን ቀለል ለማድረግ እና የዓለም ሕዝብን ማኅበራዊ መስተጋብር ለመፍጠር የሚተጉ የቴክኖሎጂ ሰዎች፣ ሀገር ችግሯን በተማረ ዜጋ ለማራገፍ የምታደርገውን ጥረት ዕውን ለማድረግ የሚጥሩ መምህራን… የሚፈጠሩት በትምህርት በሚገኝ ዕውቀት ነው:: በኩር ጋዜጣ በዚህ እትሟ በስፋት የምትዳስሰው የትምህርትን አወንታዊ አስተዋጽኦ ነው::
ሰላም ግንባታ
ትኩረቱን ትምህርት ላይ አድርጎ የሚሠራው ‘ኮንሰርን’ ትምህርት ለሰላም ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኖ እያለ በየጊዜው እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ክፉኛ እየተጎዳ መሆኑን ያትታል:: በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከትምህርት ውጪ ከሆኑት 250 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ከ125 ሚሊዮን የሚልቁት በግጭት ምክንያት የራቁ ናቸው:: ለአብነት በቅርቡ በእስራኤል እና በጋዛ መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ምክንያት ብቻ በተለይ እ.አ.አ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በጋዛ የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት እና ለውድመት መዳረጋቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ የወደፊት የትምህርት እጣ ፋንታ ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጫና ከፍተኛ ነው:: ማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ፣ የመን፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ሴኔጋል፣ ጅቡቲ፣ ሴራሊዮን፣ አፍጋኒስታን፣ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ጋምቢያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐፕሊክ ለመማር ፈተና የሆነባቸው ሀገራት ናቸው:: አሁንም ግጭቶች መፍትሄ ባልተሰጡባት ኢትዮጵያ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት እንደራቁባት ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እ.አ.አ ነሐሴ 8 ቀን 2024 ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል:: በአማራ ክልል ለአንድ ዓመት በዘለቀው ግጭት ብቻ ከ2 ነጥብ አራት ሚለዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው ከርመዋል:: አሁንም በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ከታቀደው ሰባት ሚሊዮን ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንኳ ማሳካት እንዳልተቻለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል::
ግጭቶች እና ጦርነቶች በትምህርት ተቋማት ላይ እያደረሱት ያለውን ጉዳት እና ውድመት ለመታደግ ግጭቶች ውስጥ ትምህርትን ለመጠበቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል የሚለውን መግለጫ 120 ሀገራት እ.አ.አ በግንቦት 2024 የደገፉት ቢሆንም አሁንም መግለጫው እርባና ቢስ ሆኖ ቀጥሏል:: የዓለም ባንክ በ2005 እ.አ.አ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ደግሞ የጦርነት አደጋ በሦስት በመቶ ለመቀነስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪ ምዝገባ መጠንን በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ማድረስ ይገባል::
ትምህርት ሰብዓዊ መብት መሆኑን በማክበር እና ሁሉም ተማሪዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲማሩ በማድረግ ከትጠቅ ግጭት መውጣት ይቻላል:: ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የሚያዳብሩት ማኅበራዊ መስተጋብር፣ የሚያደርጉት የባህል ልውውጥ፣ የሚጎለብተው የመተሳሰብ እሴት ለሰላም ግንባታ ጉልህ አበርክቶ ይጫዎታል::
ድህነት ቅነሳ
ከፍተኛ የተማረ ዜጋ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገታቸውን ያረጋገጡት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት በሰጡት ልዩ ትኩረት እንደሆነ ትኩረቱን የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ላይ ያደረገው ‘አክሽን ኢዱኬሽን’ አስታውቋል:: የድርጅቱ ድረ ገጹ ላይ እንደሰፈረው ጽሑፍ ከሆነ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ሕጻናት በሚገባ ትምህርታቸውን ተከታትለው ማንበብ ከቻሉ ድህነትን በ12 በመቶ መቀነስ ይቻላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ የተሸጋገሩ ሁሉም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁ በዓለም አቀፍ ደረጃ 420 ሚሊዮን ህዝብን ከድህነት ማውጣት እንደሚቻል ጽሑፉ በጥናት ማረጋገጡን ጠቁሟል:: ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የድህነት ምጣኔ ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ ያደርገዋል።
ተማሪዎች የጀመሩትን ትምህርት እንዳያቋርጡ በማድረግ ግለሰባዊ ገቢን ማሳደግ እንደሚቻልም የአክሽን ኢዱኬሽን ጽሑፍ ያሳያል:: እያንዳንዱ ግለሰብ በትምህርት ላይ የሚያሳልፈው አንድ ተጨማሪ የትምህርት ዓመት የወንዶችን ገቢ ቢያንስ በ10 በመቶ፣ የሴቶችን ደግሞ በ20 በመቶ ይጨምራል።
ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር
ትምህርት የግለሰቦችን የአመጋገብ ሥርዓት በመቀየር፣ የግል እና የአካባቢ ንጽህና እንዲረጋገጥ ሥር ነቀል የአመለካከት ለውጥን በማስረጽ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጉልህ አበርክቶ ይጫወታል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2011 እ.አ.አ ሪፖርት እንደሚያመላክተው ትምህርት የማኅበረሰቡ አመለካከት እንዲለወጥ በማድረግ በተለይ መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች የኅብረተሰብ የጤና ስጋት ሆነው ብቅ እንዳይሉ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው:: በተጨማሪም በሕክምና ክትትል እና በመድሃኒት አወሳሰድ ላይ ያለው ግንዛቤ ከፍ እንዲል በማድረግ የሞት ምጣኔ በእጅጉ እንዲቀንስ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው:: ማንበብ እና መጻፍ የምትችል እናት የልጇ በሕይወት የመቆየት ዕድሉ ማንበብ እና መጻፍ ከማትችለው በሁለት እጥፍ የበለጠ የተሻለ እንደሚሆን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል::
በአንድ ሀገር የሚሰጠው ጥራት ያለው ትምህርት የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶች እንዲቀንሱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል:: ጽሐፉ ለዚህ ማሳያ አድርጎ የሚያነሳው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሴቶች ስለ ኤችአይቪ /ኤድስ የማወቅ ዕድላቸው ከማያነቡ ሴቶች በአምስት እጥፍ መብለጡን በመጠቆም ነው።
የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ልጃገረዶች ሥራ የማግኘት እድላቸው ከፍተኛ ሲሆን በገንዘብ ረገድም ራሳቸውን የቻሉ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሙ የመጡ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች በተለይም በሴት ታዳጊዎች መጻኢ ዕድል ላይ ከፍተኛ ስጋትን ደቅነዋል:: ለአብነት ኮንሰርን ኒውስ የመረጃ አውታር እ.አ.አ በወርሀ ነሐሴ 2024 ይፋ ባደረገው መረጃ በዓለም 250 ሚሊዮን ታዲጊዎች ከትምህርት መራቃቸው አስታውቋል:: ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው::
ሴት ታዳጊዎችን በማስተማር ከ30 ሚሊዮን በላይ ህጻናትን እና ከ15 እስከ 60 ዓመት የሆናቸውን ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከሞት መከላከል እንደተቻለ ‘የኢዱኬሽን ኮሚሽን’ ጥናት ያመላክታል:: የልጅነት ጋብቻ እንዲቀንስ ብሎም እንዲጠፋ በማድረግ በታዳጊዎች የወደፊት ሕይወት ላይ የሚያሳርፈው አዎንታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ከፍተኛ ነው::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት ትምህርት ለሰላም ግንባታ፣ ለሀገራዊ ዕድገት፣ ለዜጎች እኩልነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ተረድተው ለትምህርት ሽፋን ተደራሽነት እና ጥራት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ቢሆንም መፍትሄ ያልሰጧቸው ግጭቶች እና የተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባቶች የሰጡትን ትኩረት እያደናቀፉባቸው ይገኛሉ:: በመሆኑም የግጭት መንስኤዎችን ለይቶ ለዘላቂ መፍትሄዎች ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ማስቻል ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም