የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም
ሰብአዊ መብቶች የሰው ልጆች ሁሉ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች ናቸው::
እነዚህ መብቶች ከሰዎች ተፈጥሮአዊ ባህሪ የሚመነጩ ሰዎች እንደሰው የተሟላ ኑሮ ለመኖር ሊከበሩላቸው እና ሊሟሉላቸው የሚገቡ መሰረታዊ መብቶች እንጂ በመንግሥት ወይም በማንኛውም አካል የሚሰጡ ወይም የሚከለከሉ አይደሉም::
መንግሥት መብቶቹን የማክበር እና የማስከበር ሀላፊነት ሲኖርበት ግለሰቦች ደግሞ መብቶቹ እንዲከበሩላቸው የጠየቅ መብት እና የሌሎች ግለሰቦችን ሰብዓዊ መብትን የማክበር እና ያለመጋፋት ግዴታ አለባቸው::
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን፣ አንቀጽ ስድስት ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብት አለው:: ይህ መብት በሕግ ሊከበር ይገባል፤ ማንኛውም ሰው ያላግባብ ሕይወቱን ሊነፈግ አይገባም::
አባል ሀገራት ሕግ የማስከበር ተልዕኮ የተሰጣቸውን ወታደሮች ጨምሮ ሕግ አስከባሪ ኃላፊዎቻቸው ሕይወትን ያላግባብ እንዳይነፍጉ ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃዎችን በሙሉ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
ሰብዓዊ መብቶች የሲቪል፣ ፖለቲካል፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶችን ያካተቱ ሲሆን እነዚህ መብቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሀገራት ሕጎች ውስጥ እውቅና ያገኙ ናቸው::
ሰብዓዊ መብቶች ለሰዎች በግል ወይም ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር በጋራ ሊከበሩላቸው የሚችሉ ሲሆን እነዚህን መብቶች የግል መብቶች ወይም የጋራ መብቶች በማለት ማየት ይቻላል:: ለምሳሌ ያህል በህይወት የመኖር መብት፣ የግል ነፃነት መብት፣ የአካል ደህንነት መብት፣ ከኢሰብዓዊ አያያዝና ከባርነት የመጠበቅ መብት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ፣ የሥራ መብት፣ ትምህርት የማግኘት መብት ፣የጤና መብት፣ ደረጃውን የጠበቀ ኑሮ የመኖር መብት ሰዎች በግላቸው ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶች ሲሆኑ ንፅህናውን በጠበቀ አከባቢ የመኖር መብት፣ የባህላዊ፣ ፖለቲካል እና የኢኮኖሚያዊ አድገት መብት ሰዎች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በመኖራቸው እንደ ማህበረሰብ አባል ሊያገኟቸው የሚችሉ መብቶች ናቸው::
የጋራ መብቶች ደግሞ ሰዎች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ሀይማኖታቸውን በጋራ ማንፀባረቅ እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ እድገት ተጠቃሚ መሆን የሚያስችሉ ናቸው::
በአጠቃላይ የግል መብቶች በአንደኛ እና ሁለተኛ ትውልድ መብቶች ውስጥ የተካተቱ ሲሆን የጋራ መብቶች ደግሞ በሶስተኛ ትውልድ ሰብዓዊ መብቶች ስር ይመደባሉ::
የሰብዓዊ መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንደኛው እና በሁለተኛው የአለም ጦርነት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና እልቂት ከደረሰ በኃላ እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ1945 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መቋቋምን ተከትሎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብአዊ መብቶችን ሀገራት እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ለማበጀት የተለያዩ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን በማርቀቅ በአባል ሀገሮች እንዲፀድቁ አድርጓል::
በብዙ የዓለም ሀገራት ተቀባይነት ካገኙ እና ከፀደቁ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ወይም ኮንቬንሽኖች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለአብነት እንመልከት::
እ.ኤ.አ በ1948 የወጣው ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) (በአሁኑ ወቅት የአለም አቀፍ ልማዳዊ መብት (customary international law) ደረጃን ያገኘው)፣ እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም የወጡት የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን (ICCPR) እና የኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና የባህል መብቶች ኮንቬንሽን (ICESCR) ፣ ሁሉንም ዓይነት የዘር መድልዎ ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አለም አቀፍ ስምምነት ፣ ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት ለማስጠበቅ የወጣ ኮንቬንሽን፣ የህፃናት መብት ኮንቬክሽን እና የመሳሰሉ በርካታ አለም አቀፍ ስምምነት ተረቀው በአባል ሀገሮች ፀድቀው በአሁኑ ወቅት በተለያየ መልክ ተፈፃሚ ሆነው ይገኛሉ::
ኢትዮጵያም የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን ተቀብላ በማፅደቅ እና የሀገሪቱ የህግ አካል በማድረግ እንዲሁም የህግ ማዕቀፍ በመስጠት ለመሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እና አጠባበቅ ትኩረት ሰጥታለች::
በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እውቅና እና ተቀባይነት የሚጀምረው የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው በኢ.ፊ.ዴ.ሪ. ህገመንግስት ነው ::
በህገ-መንግስቱ የተካተቱ ዝርዝር የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ውስጥ ተለይተው የታወቁ መብቶችን አካቶ የያዘ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው::
በህገ መንግስቱ ሰብዓዊ መብቶች በዝርዝር ከመካተታቸው በላይ በአንቀፅ 9 ንኡስ አንቀፅ 4 ስር ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል መሆናቸው ተደንግጎ ይገኛል:: እንዲሁም በአንቀጽ 13 ንኡስ አንቀፅ አንድ ስር በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግሥት እና የክልል ሕገ-አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና የዳኝነት አካሎች በህገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሶስት የተካተቱ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸዉ ይደነግጋል ::
በተጨማሪ በምዕራፉ ስር የተካተቱ መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና ዓለም አቀፍ ሠነዶች መርሆች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም እንዳለባቸው ተመልክቷል:: (የኢ.ፊ.ዴ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 13 ንኡስ አንቀጽ ሁለት)
በመሆኑም መንግስት መብቶቹን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ ( የመብት ጥሰት እንዳይፈፀም የመከላከል እና ጥሰት በተደረገ ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ግዴታ) አለበት ማለት ነው::
ከህገ መንግሥቱ በተጨማሪ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ሕግ እና የአሰሪና ሰራተኛ ሕጎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕጎች ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት በመስጠት በስራ ላይ ይገኛሉ::
በተጨማሪም የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች፤ የሰራተኞች መብት፣ የልማት መብት፣ የአካባቢ ደህንነት መብት ከአለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ በሆነ መልኩ በህገ መንግሥቱ በመካተታቸው መንግሥት ለመብቶቹ መከበር ወይም መሟላት ግዴታ እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል::
በመሆኑም ለእነዚህ መብቶች ተፈፃሚነት በሁሉም የመንግሥት ደረጃ ያሉ የፌደራልም ይሁን የክልል የመንግሥት አካላት ከፍተኛ ሀላፊነት እና ግዴታ አለባቸው::
ህብረተሰቡ መብቶቹ እንዲከበሩለት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፣ የሌሎች ሰዎችን መብት ማክበርና ያለመጋፋት እንዲሁም የመብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ ለፍትሕ አካላት ተባባሪ በመሆን በአጥፊዎች ላይ ተገቢው ቅጣት እንዲጣል በማገዝ የሰብዓዊ መብቶች የተከበሩባት ሀገርን የመገንባት ሀላፊነት አለበት የፌደራል አቃቢ ሕግ ድረ ገጽ አስፍሯል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም