የአፅም ባህር ዳርቻ ብሔራዊ ፓርክ

0
129

የህዳር  2 ቀን 2017 ዓ.ም

የአፅም ባህር ዳርቻ ብሔሪዊ ፓርክ በአፍሪካ ናሚቢያ ነው የሚገኘው:: በ1978 እ.አ.አ በአዋጅ እውቅና ተሰጥቶታል:: ፓርኩ ናሚቢያ አትላንቲክ ውቅያኖስን በምትዋሰንበት ምእራባዊ ቀጠና ከደቡብ እስከ ሰሜን የተከለለ ነው::
ፓርኩ አሁን ያለው መጠን 16 390 ኪሎ ሜትር ካሬ ሲሆን ርዝመቱ ከደቡብ እስከ ሰሜን 500 ኪሎ ሜትር ወይም 310 ማይል ተለክቷል::
የውቅያኖስ ዳርቻው አሸዋና ጠጠር የለበሰ ነው:: የአሸዋ ክምር፣ በወንዝ የተፈጠሩ ሸለቆዎች፣ የበረሃ ቁጥቋጦዎች የዓይን ማረፊያ ናቸው::
ከዱር አራዊት ዝሆን፣ አንበሳ፣ አቦሸማኔ፣ አዞ፣ የሜዳ አህያ፣ ሳላ፣ ኤሊ መኖራቸው ተረጋግጧል:: ከዓእዋፍ 306 ዝርያዎች እንደሚገኙም ነው ድረ ገፆች ያሰፈሩት::
በፓርኩ ክልል በርካታ የድንጋይ ሽበት “lichen” በበረሀው ስነ ምህዳር ለተጠለሉ ዝሆን፣ አውራሪስ ለመሳሰሉት መኖ ሆኖ ያገለግላል:: ረግረጋማ ርጥብ ቀጣናውም በኩኒን ወንዝ የተቸረ ገፅታ ነው::
በፓርኩ ክልል ምንም ዓይነት ሰውሰራሽ የውኃ ጉድጓድ፣ የስነምህዳር አስተዳደር ኘሮግራምም የለውም:: በቀጣናው የሚገኙ የዱር አራዊት ወደ ምእራብ የሚፈሱ ወንዞች የጥም መቁረጫዎቻቸው ናቸው:: ሞቃታማውን ቀጣና አቋርጠው የሚፈሱ ወንዞች እምብዛም ቢሆኑም በከርሰ ምድር ውኃ እና ምንጮች ሳር እና ቅጠላ ቅጠል፣ ቁጥቋጦን በማለምለም ለእንስሳቱ በመጠለያ እና በመራቢያ ከለላነት ያገለግላል::
በአነስተኛ አውሮኘላን በሚደረግ በረራ በቀላሉ ወደ ፓርኩ መድረስ ይቻላል:: በፓርኩ ቆይታ ለማድረግም በቂ ማረፊያ ቦታዎችም አሉት:: የፓርኩን ገፅታ ለመመልከት ታስበ የተዘጋጁ በመሆናቸው በአህጉሯ ከሚገኙ ማረፊያዎች ከቀዳሚዎቹ ረድፍ የሚመደብ ነው::
የአፅም ባህርዳርቻ ብሔራዊ ፓርክ በመጨረሻም ስያሜው ከውቅያኖስ የወጣ የእንስሳት አፅም ወይም ቅሪት፣ እንዲሁም በማእበል ተገፍተው ዳርቻውን የያዙ የመርከብ ፍርስራሾችን መሰረት ማድረጉን ልብ ይሏል::
ለዘገባችን አፍሪካ ኦዲሴይ፤ ጐንድ ዋና ኮሌክሽን፤ ኤን ደብሊው አር ናሚቢያ ድረ ገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here