የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም
ኒያል ሹክላ ራሱን በራሱ ያስተማረ፣ በስስ ኘላስቲክ የተለበጠ መስታዉትን በመዶሻ በመምታት በሚፈጠሩ ስንጥቆች ምስል መስራት የቻለ ጠቢብ ለመሆን መብቃቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::
ሹክላ በዚሁ ትእግስትን፣ ደጋግሞ መሞከርን በሚሻው ስልት ያለመታከት ባደረገው ጥረት ለውጤት የበቁ ስራዎቹን በማህበራዊ ድረገፆች ለእይታ አብቅቷል:: ስራዎቹ በአራት ቀናት ከአራት ሚሊዬን በላይ ተመልካች በማግኘታቸው የተራራ ያክል የገዘፈ ትዕግስት በሚሻው የጥበብ ስልት እንደገፋበት ነው የተናገረው::
ጠቢቡ ሙዚዬም ዊክሊ ለተሰኘ መጽሄት ዘጋቢ በሰጠው አስተያየት “እያንዳንዱ የመዶሻ ምት በታቀደው፣ ቦታ እና አቀማመጥ በሚፈለገው የተመጠነ ኃይል ማረፍ ይኖርበታል:: በዚህ መልኩ ተሰርቶም እያንዳንዱ ሙከራ ስኬታማ አይሆንም:: አንድ የተሳሳተ ምት ስራውን ሙሉ በሙሉ ያበላሸዋል – በቃ በአዲስ መስታዉት መጀመር ግድ ይሆናል:: የመጨረሻውን የተዋጣ ምስል እስካገኝም ብዙ መስታውት ሊበላሽብኝም ይችላል:: “ሲል ነው የጥበባዊ ስልቱን እልህ አስጨራሽነት ያብራራው:: ኒያል ሹክላ በትምህርት ዝግጅቱ ፀሀፊ እና የፊልም አዘጋጅ ነው:: ሆኖም ከሰለጠነበት ሞያ ራሱን ለማራቅ ወይም ለማግለል ወስኖ እንጂ አዲሱን የጥበብ ስልት ሲሞክር፣ ይሳካልኛል፣ እዘልቅበታለሁ ብሎ አስቦ አልነበረም::
ኒያልሹክላ መስታዉትን በመሰነጣጠቅ አስደናቂ ጥበባዊ ምስል መፍጠር በእጅጉ ከባድ መሆኑን ነው የተናገረው ኒያል ሹክላ ምክንያቱ ደግሞ እንደ ሸራ እና ብሩሽ የተለያዩ ቀለማትን መጠቀም አለመቻሉ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስምሮበታል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም