አመጸኛዉ ጥበብ

0
197

የህዳር  2 ቀን 2017 ዓ.ም

ሪፖርተር መጽሔት የካቲት 1991 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ የሚገኙ የግድግዳ እና ጠረጴዛ ላይ ጽሑፎችን ሰብስቦ ነበር። ፍቅር የያዘው ወጣት 502 ሕንጻ መጸዳጃ ቤት ውስጥ እንዲህ ሲል ይጽፋል “ሰዎች መላ በሉኝ ከዲፓርትመንቴ አንዲት ልጅ አፈቀርኩ”፡፡ በመቀጠልም ሌሎች ሦስት ሰዎች ምላሽ ይጽፉለታል። አንደኛው “ራስህን አጥፋ” አለው። ቀጥሎም ሁለተኛው ሰው “ደፍረህ ጠይቃት” ይለዋል። ሦስተኛው ሰው “አርፈህ ተማር” የሚል ምላሽ ይሰጠዋል። የግድግዳ ላይ ጽሑፎች የንግግር መድረክ ናቸው። ብዙ ሐሳቦች ይንሸራሸሩባቸዋል።
ሙሉ እመቤት ዘነበ በ2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጻፉ የግድግዳ ላይ ጽሑፎችን በሚመለከት ጥናት አድርጋለች። በጥናቱ መሰረትም ግራፊቲ የሐሳብ መግለጫ መሳሪያዎች ናቸው ትላለች። ግራፊቲ የሚለው ቃል አመጣጡ ከጣሊያንኛው ግራፊቶ ቃል ነው። እነዚህ የግድግዳ ላይ ጽሑፎች ወይም ስዕሎች በእንግሊዘኛ ግራፊቲ ተብለው ይጠራሉ። ግራፊቲ ጭረት፣ ጽሑፍ፣ ምልክት፣ ስዕልን ያጠቃልላል። በጥናቱም አፍሪካ ውስጥ ሐሳብን በነጻነት መናገር ስለማይፈቀድ ነው የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ለሐሳብ ነጻነት ትልቅ ዋጋ የሚከፍሉት በሚል ተጠቅሷል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሐሳቦች በመታፈናቸው ሰዎች ግራፊቲዎችን እንደ መተንፈሻነት ይጠቀማሉ። በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ሃይማኖት እና ፓለቲካዊ ሐሳቦችን ማንሳት መከልከሉ ሌላ የመናገሪያ አውድ መፈለግን አምጥቷል። ለዚህ ነው ብዙ መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ፣ አዳራሾች፣ ቤተመጽሐፍቶች እና ስውር ግድግዳዎች ላይ በርከት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ተጽፈው የምንመለከተው። ሙሉ እመቤት በጥናቷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች መጻዳጃ ቤት፣ ቤተ መጽሐፍ እና መማሪያ ክፍሎች ውስጥ መገኘታቸውን አስቀምጣለች።
ወሲባዊ ጉዳዮች፣ ሃይማኖት እና ፓለቲካ ያዘሉ ሐሳቦችን በብዛት መመልከቷን በማንሳት ትንታኔዋን አስፍራለች። በኢትዮጵያ ወሲብ፣ ሃይማኖት እና ፓለቲካን በግልጽ እና በአደባባይ ማውራት አንድም ነውር ነው፤ ሁለትም ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ ናቸው። ሦስትም የኢትዮጵያ የፓለቲካ ባህል የሐሳብ ነጻነትን በመግፋት ስለሚጨቁን ይህንን ድንበር ማለፍ ዋጋ ያስከፍላል። የሞራልን ድንበርን በመጣስ ከሚመጣ ወቀሳ ለመዳን፤ ከሃይማኖት ጉዳዮች ክርክር በኋላ ከሚመጣ ወቀሳ ለማምለጥ እናም ከአፋኝ መንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ ላለመግባት በድብቅ መጻፍ ተመራጭ ይሆናል። ግራፊቲ ሐሳብ እና ስሜትን ያለተጠያቂነት የማስተላልፊያ መንገድ በመሆኑ ብዙዎች ይመርጡታል። በሙሉእመቤት ጥናት መሰረት ግራፊቲ የሐሳብ ነጻነት ሜዳ ነው። እንደ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ እና ሌሎች ማህበራዊ የሚዲያ አማራጮች ሁሉ ግራፊቲ ከተጠያቂነት በመሸሽ ሐሳብን የመስጫ ስልት ነው።
ግራፊቲዎች ጥበብ ወይስ ውንብድና በሚል ለብዙ ዓመታት ክርክር እና ውዝግብ ሲደረግባቸው ቆይቷል። ወንጀል ናቸው የሚለው እሳቤ መነሻው ሰዓሊዎቹ ወይም ጸሐፊዎቹ የሰዎችን መብት አያከብሩም፤ ፈቃድ እና ሕጋዊነት የላቸውም የሚል ነጥብ አለው። የህዝብ ሀብት ወይም አካባቢን ያለማንም ፈቃድ ለግላዊ ስሜት ማንጸባረቂያነት መጠቀም ውንብድና ነው ይላሉ። ለምሳሌ ግራፊቲ የሚሰሩ ሰዎች ሰፊ ግድግዳ ቢያገኙ የሚፈልጉትን ይጽፉበታል፤ ይስሉበታልም። ይህም ግድግዳውን ያበላሸዋል። የአካባቢንም ደህንነት ያውካል የሚል ሐሳብ ይነሳል። ሰዓሊዎች አንድ ግለሰብ በሰራው ሕንጻ ላይ ፈቃደኝነቱን ሳይጠይቁ በስውር መልእክታቸውን አስቀምጠው ይሰወራሉ። ይህም መብት ጥሰት ነው። ሕንጻውም ላይ ጉዳት ማድረስ ነው የሚሉ አሉ።
ኒዮርክ ታይምስ ግራፊቲ ውንብድና ነው ይልና “እስኪ ማነው ድንገት ሕንጻው ላይ የማይፈልገው ስዕል ተስሎ ወይም ተጽፎበት ቢያገኝ ደስ የሚለው?” ብሎ ይጠይቃል። እንዲያውም በታሪክ ውስጥ እ.አ.አ ከ1966 እስከ 1973 ኒዮርክን ከንቲባ ሆነው የመሩት ጆን ሊንድሰይ በግራፊቲ ላይ ጀምረውት የነበረውን የማጥፋት ዘመቻ ይጠቅሳል። ሕግጋዊ እውቅና እና ፈቃድ የሌለው የወንበዴ ተግባር ነው ይላል ኒዮርክ ታይምስ።
በአንጻሩ ግራፊቲ የመልእክት ማስተላለፊያ ጥበብ ነው የሚሉ አሉ። በስውር የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ በግልጽም የሚስሉ አሉ። ግራፊቲ የተጨቆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መብታቸውን ለማስከበር ትግል የሚያደርጉበት አማራጭም ነው። መልእክቶችን ማስተላለፊያ አማራጮች ናቸው፤ ብዙ የግራፊቲ ስራዎች በሚሊዮን ዶላር መሸጣቸውን የሚያነሱት የጥበብ ወገን ተከራካሪዎች፤ ግራፊቲ ዋጋ ያለው ጥበብ ነው ይላሉ። በታሪክ ውስጥ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጡ የግራፊቲ ስራዎችን በምሳሌነት በማንሳት ይሞግታሉ፤ ግራፊቲ ዋጋ ያወጣ፤ የሚወደድ ሐሳብ ማስተላለፊያ ጥበብ ነው ሲሉ።
አሜሪካዊው የግራፊቲ ጥበበኛ ጂያን ማይክል በሕይወት እና በሞት መካከል ያለን ሰው የራስ ቅል የገለጸበት ውስብስብ ስራውን የሰራው እ.አ.አ በ1982 ነበር። ከዓመታት በኋላ በ2017 ይህ ስራ አሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጫረታ በ110 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል። ሌላም በድብቅ ስሙ ባንክሲ በመባል የሚታወቀው ዝነኛ የግራፊቲ አርቲስት እ.አ.አ በ2020 ስራውን በ64 ሚሊዮን ዶላር ሸጧል። ባንክሲ በዓለም ከሚታወቁ የግራፊቲ ሰዓሊዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። ብዙ ጊዜ በስራዎቹ ፓሊሶችን ያሳያል። አንድ ጊዜ ፓሊስ ሕጻን ሲደበድብ ያሳያል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሕጻኑ ፓሊሱን መሳሪያውን ነጥቆ ሲማርከው ያሳያል። ፓለቲካዊ እና ማህበራዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በስራዎቹ ያነሳል። ገርል ዊዝ ባሎን (ፊኛው ጋ ያለችው ሕጻን) በሚል ተወዳጅ ስራ አለው። ግድግዳ ላይ እ.አ.አ በ2002 የተሰራው ይህ ስዕል ሕጻኗ የተነፋውን ቀይ ልብ ቅርጽ ፊኛ ለመንካት እጇን ዘርግታ ስትንጠራራ ያሳያል። ተስፋ እና ጽናትን የሚያሳይ ነው። በኢንተርኔት በተደረገ ጫረታ 1 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል። “ሁልጊዜም ተስፋ አለ” የሚል ጽሑፍም ሰፍሮበታል።
ግራፊቲዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረ ጅማሮ አላቸው። በጥንታዊ ግብጽ፣ ሮም፣ ግሪክ እና ቀደምት ስልጣኔ ባላቸው ሀገራት በግድግዳዎች እና ዋሻዎች ውስጥ ተጽፈው ወይም ተጭረው መልእክትን ለማስተላለፊያነት ውለዋል። በጊዜ ሒደት ግራፊቲዎች አድገው የጎዳና ላይ ጥበብ በሚል ዘመናዊ ስም እና አሰራር ተከሰቱ። እ.አ.አ በ1960 ዎች አሜሪካ ፊላደልፊያ እና ኒዮርክ ከተሞች ውስጥ ዘመናዊ የጎዳና ጥበብ በሚል ግራፊቲ መታወቅ ጀመረ።
አጀማመሩ አሻራቸውን ከተማዋ ውስጥ ማስቀመጥ በሚፈልጉ ወጣቶች ነበር። ከ10 ዓመታት በኋላ የግራፊቲ ጥበበኞች በቡድን መደራጀት እና አዳዲስ ስልቶችን መፍጠር ጀመሩ። አንጸባራቂ ቀለማትን በመጠቀምም ስራቸው በብዙዎች ዘንድ እንዲወደድ ማድረግ ቻሉበት። በአውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር 1980ዎቹ የጎዳና ላይ ግራፊቲ ጥበብ ዓለም አቀፍ ሆኖ፤ ሰሪዎችም ስራዎቻቸውን በአደባባይ ማስተዋወቅ የጀመሩበት ነበር። ነባሩን ጥበብ በመብለጥ የጎዳና ላይ ጥበብ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን መዳሰሱን ያዘው።
ቡክ አን አርቲስት ድረገጽ የግራፊቲ ጥበብ ለማህበረሰብ ያለውን ፋይዳ ያስገነዝባል። በዚህም ውበት ቀድሞ ይመጣል። በማህበረሰቡ ዘንድ የተዘነጉ እና በቸልተኝነት የሚውሉ ቦታዎችን በማስዋብ መልካም ገጽታን ያላብሳል። የቆሻሻ ማስቀመጫ የነበሩ ስፍራዎችን የውበት ጸዳል ማልበስ የሚያስችሉ የግራፊቲ ስራዎች እንዳሉም ይገልጻል።
ቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የጎዳና ግራፊቲ ስራዎችን ተከትሎ ሊመጣ ይችላል። ብዙ በቱሪስት የሚጎበኙ የጎዳና ላይ የግራፊቲ ስራዎች እሉ። ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ የጎዳና ጥበብ እና ስዕሎችን ለመጎብኘት ይንቀሳቀሳሉ። ይህም ለአካባቢው ማህበረሰብ ገንዘብን ያመነጫል። ግራፊቲ ማህበራዊ ሒስ እና ግንዛቤን የመፍጠር አቅም አለው። ትኩረት የሚገባውን ጉዳይ አጉልቶ ማሳየት እናም ማህበረሰቡ እርስ በርሱ እንዲወያይ ሐሳብ ይጭራል።
በፈረንጆች አቆጣጠር 2016 የተካሄደውን ሪዮ ኦሎምፒክ ለማድመቅ ኤድዋርዶ ዳውድ የሳለው የግራፊቲ ስራ በታሪክ ትልቁ ስራ ነው። 190 ሜትር ርዝመት እና 15 ሜትር ከፍታ ነበረው። ሦስት ወራት ደግሞ ስራውን ለማጠናቀቅ የወሰደው ጊዜ ነበር። የኦሎምፒክ አምስቱ ክብ ቀለበቶችን ወክሎ አምስት አህጉራትን የሚወክሉ የሰዎችን ገጽታ በስዕል አስቀምጦታል። አፍሪካ፣ ኤስያ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ኦሲያንያን (ኒውዝላንድ፣ አውስትራሊያ እና አጎራባች ሀገራትን ወክሎ) አሳይቷል። ሰላም እና አንድነት በግራፊቲው ተሰብኳል። ሁላችንም አንድ ነን የሚል ሐሳብ ነበረው።
በሰለጠነው ዓለም ያለው የግራፊቲ ስራ ግድግዳ ላይ ይሳል እንጂ ታትሞ ለህትመትም በቅቶ ይሸጣል። የሰው ልጅ አኗኗርን በውል ያሳያል። ግራፊቲ ከጽሑፍ አድጎ ትላልቅ ግድግዳዎች ላይ ሐሳብን እስከ መግለጽ ደርሷል። ድጋፍ፣፣ ፍልስፍና፣ ትችት፣ተቃውሞ፣ ሙግት፣ ደስታ እና ኀዘን ይገለጹበታል። ከገቢ አንጻርም ግራፊቲ በሚሊዮን የሚሸጥ የጥበብ ውጤት ነው። ብዙ የቀለም አማራጮችን በመጠቀም ደረጃውን ከስዕል ስራ ተስተካካይ እውቅና አግኝቷል።
በሀገራችን ደግሞ ግራፊቲ በቴክኖሎጂ አላደገም፣ በፈጠራም ይሁን በገቢ ብዙ አልተራመደም። የሚነሱት ርዕሰ ጉዳዮችም ከመጸዳጃ ቤት፣ቤተ መጽሐፍ እና መማሪያ ክፍሎች አልወጡም። ወደ አደባባይ ወጥተው የጎዳና ጥበብ ለመባል አልበቁም። በብዛት ጽሑፍ ላይ ያተኩራሉ። ሙሉ እመቤት በጥናቷ እንዳረጋገጠችውም ወሲብ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር እና ፓለቲካ ላይ ብቻ በብዛት ሙጥኝ ብለዋል። ብዙ የሀገራችን ግራፊቲዎች ከጭረት አሰራር፣ ከሽሙጥ እና ስድብ አልተሻገሩ። ይህንንም ለማረጋገጥ መጸዳጃ ቤቶችን መመልከት በቂ ነው። በብሔር፣ በጎጥ፣ በስልጣን፣ በቋንቋ፣ በጾታ፣ በፓለቲካ አቋም ልዩነት መተራረብ የተለመደ ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here