የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም
ሶፍ ዑመር ዋሻ በሀገራችን የቱሪዝም መስህቦች መገኛነት አንጋፋውን ስፍራ ከሚይዙ አካባቢዎች አንዱ ነው። የባሌ ዞን እጅግ በርካታ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የታደለ ምድር ነው:: ከመስህቦቹ ውስጥም የሚያስገርም የተፈጥሮ ስጦታ የሆነውና በአፍሪካ ካሉ ትላልቅ ዋሻዎች አንዱ የሶፍ ዑመር ተፈጥሮአዊ ዋሻ ይገኝበታል:: 15ነጥብ1 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ይህ ዋሻ በኢትዮጵያም ረጅሙ እንደሆነ ይነገርለታል:: ዋሻው በጊዜያዊ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል::
የዋሻው ውሰጥ ለውስጥ መንገድ ርዝማኔ 15 ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር ሲሆን የጎን ስፋቱ ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ነው። ይህም በኢትዮጵያ በርዝመቱ አቻ የሌለው ያደርገዋል። ከአርባ በላይ በሮች አሉት።
ከመግቢያው እስከ መውጫው ድረስ ከሁለት እስከ ሶስት ሰዓት ጉዞ እንደሚጠይቅ የሚነገርለት ይህ ሚስጥራዊ ዋሻ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በርዝመቱ ቀዳሚ ነው። በዓለም 306ኛ ደረጃን እንደያዘ የሚነገርለት ይህ አስደማሚው የተፈጥሮ ዋሻ ከአዲስ አበባ 532 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መነሻውን ያደርጋል፤ ወደ መቶ አሥር ኪሎ ሜትር ተጉዞ ዋሻውን የምድር ውስጥ መሻገሪያ መንገድ የሚያደርገው የዌብ ወንዝ ሌላው ተጨማሪ የዋሻው ድምቀት ነው። ዋሻውን አቋርጦ የሚያልፈው ይህ ወንዝ ውስጥ ለውስጥ ሰባት ጊዜ የሚተጣጠፍባቸው ቦታዎች አሉት። በዋሻው የሚጓዝ ሰውም ሰባት ጊዜ ወንዙን መሻገር ይጠበቅበታል። አምስት ጊዜ በእግርዎ ሁለት ጊዜ ደግሞ በዋና ያቋርጣሉ። ይህ ተፈጥሮ ያበጃጀው ሚስጥራዊ ዋሻ ውስጣዊ ውበቱ እና የተፈጥሮአዊ ሥነ ህንፃ ጥበብ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዛና የሚያስደምም አድርጎታል።
ከአምስት ሚሊዮን ዓመት በፊት እንደነበረ የሚነገርለት የተፈጥሮ ዋሻው፤ የወይብ ወንዝ በጊዜ ሂደት ቦርቡሮ የፈጠረው መሆኑ ይነገራል። ስያሜውን ያገኘውም ከ1000 ዓመት በፊት ሶፍ ዑመር ከሚባሉ የሀይማኖት አባት ነው። ሼክ ሶፍ ዑመር በዋሻው ለብዙ ዓመታት ኖረዋል፤ ሀይማኖታዊ ትምህርትም ያስተምሩበት ነበር። የሶፍ ዑመር ዋሻ በናሽናል ጂኦግራፊ 10 ታዋቂ አምልኮ የሚደረግባቸው ዋሻዎች ውስጥ አንዱ ነው:: መስህቡም በርካታ ምሰሶዎች ያሉት ሲሆን፤ በተለይም በውስጡ ባሉ የክፍሎቹ ማእዘናት ውበትም ታዋቂ ነው::
የሶፍ ዑመር ዋሻ 42 መግቢያዎች አሉት:: ከእነዚህ መግቢያዎች መካከል በአሁኑ ሰዓት የሚያገለግሉት አራቱ ብቻ ናቸው:: ይህ ዋሻ ከሰሜን ወደ ደቡብ እንዲሁም ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ያስኬዳል:: በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘው የዌይቭ ወንዝ ዓመቱን ሙሉ በዋሻው ውስጥ ይፈሳል::
ዋሻው በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ መንፈሳዊ ትርጉም የሚሰጠው ስፍራ ነው:: ወደ ዋሻው መግቢያ በድንጋይ የታጠረ ቦታ ክር ቅዱስ ኡመር ይባላል:: ይኸውም ከበሮ በመምታት የሚያመሰግኑበትና የስለት ከብት በማረድ የሚበላበት ቦታ ነው:: የሚሳሉ ሰዎች ከታረደው በግ ወይም ፍየል ላይ ትንሽ ቆዳ ተቆርጦ ዋሻ ውስጥ ለፀሎት ይንጠለጠልላቸዋል:: በስተቀኝ በኩል ከዋሻው ፊት ለፊት ወንዙ ውስጥ በጣም ትልቅ የሆነ የተከፈተ መሶብ ቅርፅ ያለው ተፈጥሮ የተራቀቀበት ወጥ ድንጋይ የሶፍ ኡመር መቀመጫ አለ::
የሶፍ ዑመር ዋሻ መግቢያ ጉለንተናየው መኩ ሲባል መውጫው ደግሞ ሁልቃ ይባላል:: ጉለንተናየው መኩ የሶፍ ኡመር ልጅ ከራዮሞኩ የምትቀመጥበት ቦታ ነው:: ወደ ዋሻ ውስጥ ሲገባ ጀባ ቢቂላ የሚባል ትልቅ ክብ ድንጋይ አለ:: በዚህ ቦታ ከድንጋዩ በላይ ግንድ የነበረ ሲሆን ግንዱ ላይ እናትና አባት የረገሟቸው በጣም የሚያስቸግሩ ወጣቶች የሚታሰሩበት ቦታ ነው ይባላል:: ጀባ ቢቂላ የተባለው በወቅቱ ከታሰሩ ወጣቶች አንዱ ነው:: ጥፋተኞቹ የሚወጡበት ትልቁና ክቡ ድንጋይ በጀርባው በኩል የኢትዮጵያ ካርታን ቅርፅ ይዟል::
ዋሻው የተለያዩና በርካታ ክፍሎች ሲኖሩት ወደ መሀል ሰፊ የሆነው ክፍል አለይህም ፊጢ ሱማ አብዲ ይባላል:: በሶፍ ኡመር ልጅ ስም የተሰየመ ቦታ ነው:: ክፍሉ መካከል ላይ በክብ ቅርፅ ጎርጎድ ብሎ ወደ ላይ ከፍ ያለ ሲሆን ተፈጥሮአዊ መሆኑ ያስገርማል::
የተለያዩ ገፅታዎችን በማሳየት አንዱን አድንቀን ሳንነሳ ሌላ የተፈጥሮ ገፅታን የሚያሳየን፤ የማያልቅበት ይህ ዋሻ የሶፍ ኡመር አዳራሽ ተብሎ ወደ ተሰየመው ዋሻ ክፍል ያሸጋግረናል። በዚህ ክፍል ችግር ያለባቸው ሰዎች ከሶፍ ኡመር ጋር ተገናኝተው ችግራቸውን የሚያስረዱበት ቦታ ነው:: ሌላው አስገራሚው የዋሻ ክፍል ደግሞ ስጋጃ የተባለው ነው:: ይህ ክፍል መስገጃ ሲሆን በዚህ ክፍል አራት ትልልቅ ጠፍጣፋና ሰፋፊ ድንጋዮች አሉ። እነዚህም የሶፍ ኡመር፣ የሼህ ሁሴን፣ የከራዩ መኮ እና የሼህ አበል ቃሲም መስገጃ ስጋጃዎች ናቸው ::
በሶፍ ዑመር ዋሻ ውስጥ ዓሣ እንዲሁም ከ50 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች፣ የዱር ድመቶች፣ ግዙፍ ኤሊዎች እና ሌሎች የዱር እንስሳትን ይዟል::
ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት ከሚያስብሏት ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነውን የሶፍ ዑመር ዋሻ ካሉት በርካታ ልዩ ገጽታና ሳቢነት በጥቂቱ ከዚህ የበለጠ ለመረዳት በስፍራው ተገኝቶ መጎብኘት ልዩ ስሜት ይፈጥራል።
ይሄ ግዙፍ ዋሻ ከአዕምሮ የማይጠፋና እጅግ አስገራሚ የሆነ ተፈጥሮ ኪናዊ ጥበብን ያሳየችበት ስራ ነው:: ጣራው ልምድ ባለው ባለሙያ ተስተካክሎ የተገጠመ ወጥ ኮርኒስ ይመስላል:: ሁለቱም ተጣምረው መኖራቸው በራሱ አስገራሚ ትዕይንት ነው::
ምንጭ፦ኢትዬ ጅኦግራፊክ ዶት ኮም፤ ባሌ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም)