የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና ለዜጎቿ የኑሮ መሠረት ነው። አርሶ አደሩ አምርቶ ቤተሰቡን ከማስተዳደር ባለፈ ለገበያ ያቀርባል። በኢትዮጵያ አጠቃላይ ለእርሻ ከሚውለው መሬት ውስጥ 34 በመቶ የሚሆነውን የአማራ ክልል እንደሚሸፍን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ በዋናነት የሰብል ምርት በመኸር ወቅት ይመረታል። ክልሉ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ከማምረት ባለፈ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶችም በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።
ለአብነትም ጥጥ፣ ሰሊጥ እና ቡና ይመረታል። ሆኖም በክልሉ ሁለተኛ ዓመቱን ይዞ የቀጠለው ግጭት በግብርናው ዘርፍ ተፅዕኖ ማሳደሩን አርሶ አደሮቹ ምስክሮች ናቸው።
በፈተና ውስጥ ሆነው የሚያመርቱትን ምርት በወቅቱ ለገበያ ለማቅረብ መቸገራቸውንም አርሶ አደሮቹ በተለያዩ ጊዚያት አስተያየታቸውን ለበኩር ጋዜጣ አጋርተውናል።
ከግጭቱ ባሻገር ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የተባይ ክስተት የአርሶ አደሩ ፈተናዎች ናቸው። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባልተሰበሰቡ እና ተሰብስበው ወደ ጎተራ ባልገቡ ሰብሎች ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። አርሶ አደሩ ብርድ እና ዝናቡን ተቋቁሞ ሲለፋበት የከረመውን ሰብል በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል። በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በስልክ መረጃ ያደረሱን አርሶ አደሮች እንደነገሩን በ2016/2017 የምርት ዘመን በግጭት ውስጥ ሆነው በዘር የሸፈኑትን ሰብል እየሰበሰቡ ይገኛሉ። አርሶ አደሩ ፈጣሪውን አምኖ ሰማዩን አይቶ አርሶ፣ አለስልሶ፣ ዘርቶ፣ ኮትኩቶ፣ አርሞ፣ ከወፍ እና ከተባይ ጠብቆ… በአጠቃላይ በችግር ውስጥ ሆኖ ተንከባክቦ ለፍሬ ያደረሰውን ሰብል በደቦ እየሰበሰበ ነው።
“ጎበዝ እንበርታ እንጨድ ፈጥነን
በአንድ ላይ ከበን በደቦ ሆነን” ብሏል። በደቦ መሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ፍቱን መድኃኒት መሆኑንም ተገንዝበዋል። ሀገር መጋቢው አርሶ አደር በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተቋቁሞ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ተጋፍጦ የልፋቱን ውጤት በእጁ ለማስገባት ሩጫ ላይ ነው። አራሹ እና አጉራሹ አርሶ አደር ሩጫው እንዳይስተጓጎል እና ሰብሉ ባክኖ እንዳይቀር የዘወትር ፀሎቱም ነው። ለዚህም ፈጥኖ ለመሰብሰብ እና ወቅቶ ለማስገባት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ አስፈላጊ ነው። የጉልበት ሠራተኛው ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ፣ አርሶ አደሩ እና ባለሀብቱ የጉልበት ሠራተኛ እንዲያገኝ፣ ሲለፋበት የከረመው ሰብሉ እንዲታጨድ፣ እንዲከመር፣ እንዲወቃ እና በወቅቱ ወደ ቤት እንዲገባ፣ ገበያ ወጥቶ ተረጋግቶ ሸጦ ችግሩን እንዲቀርፍ ግጭቱን ማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ማምጣት የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል። ምርቱ በወቅቱ ካልተሰበሰበ፣ ጉዳት ከደረሰበት እና በከንቱ ፈሶ ከቀረ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸው አይቀሬ ነው። በመሆኑም አርሶ አደሩ ምርቱን በወቅቱ እንዲሰበስብ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩለት ይገባል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ በ2016/2017 የምርት ዘመን በ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ነው። ይህን ዕቅድ ለማሳካትም ለሰላም ቅድሚያ መስጠት፣ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይላል። በመሆኑም የክልሉ አርሶ አደር፣ የግብርና ባለሙያዎች እና መሪዎች በተቀናጀ መንገድ የሰብል ስብሰባ ሥራውን ባሕላዊ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት እንዳይከሰት አርሶ አደሩ በደቦ ሰብሉን መሰብሰብ፣ መውቃት እና በጥንቃቄ ወደ ጎተራ ማስገባት እንዳለበት በክልሉ ግብርና ቢሮ ጥሪ ቀርቧል።
በመሆኑም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም እና በተቀናጀ የሰው ኃይል (በደቦ፣ በወንፈል) በፍጥነት እና በጥራት መሰብሰብ እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ። ለዚህም መንግሥት የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂ (ኮምባይነር) እንዲሁም የምርት መፈልፈያ እና መውቂያ ቴክኖሎጂ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ይኖርበታል። የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ እንደሚያሳው በተለያዩ ምክንያቶች 34 በመቶ ያክል የምርት ብክነት ይከሰታል። በአግባቡ፣ በወቅቱ እና በጥንቃቄ አለመሰብሰብ፣ ሲከመሩ ለተባይ እና ለብልሽት ከሚዳርጉ ቦታዎች አለመራቅ፣ የሰብሉን ትክክለኛ የመድረቅ ደረጃ አለመለየት፣ የተሻሻሉ አሰራሮችን አለመከተል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አለመጠቀም፣ የግንዛቤ እጥረት እና ሌሎች ጉዳዮች ለምርት ብክነት ምክንያቶች ናቸው። በመሆኑም አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ፤ በዘመቻ መሰብሰብ (ማጨድ)፣ የተሰበሰበውን በእንጨት ርብራብ ሰርቶ መከመር፣ ሸራ ማልበስ፣ ማገላበጥ፣ ማድረቅ፣ አይጥ እና መሰል ተባይ እንዳይበላው መከታተል፣ የሰብል መፈልፈያ፣ መውቂያ፣ ማጓጓዣ፣ ማከማቻ፣ መሰብሰቢያ እና ማድረቂያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ የምርትን ብክነት ከመቀነስ ባሻገር የምርት ጥራትን ይጨምራል። ምርቱም በገበያው ተፈላጊ ይሆናል። ምርቱ ለገበያ እና ለምግብነት እስኪውል ለብክነት እንዳይዳረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።
በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚያመዝን መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ አከባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ቀጣይነት እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ አስገንዝቧል፡፡ በጥቂት ቀናቶች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለዉ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለሆነም በሚኖሩት ደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም