የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
የመጀመሪያዎቹ አሜሪካውያን
በዋናው የበረዶ ዘመን አብዛኛው የዓለም ውሃ በተንጣለለው አህጉራዊ የበረዶ ግግር ተዳፍኖ ነበር። በዚህ የተነሳ የቤሪንግ ባህር አሁን ከሚገኝበት ከፍታ ከመቶዎች ኪሎ ሜትሮች በታች እንዲቀበር እና ቤሪንጋ የተባለውን እስያን እና ሰሜን አሜሪካን የሚያገናኘውን የየብስ ድልድይ እንዲከሰት አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አህጉሮች የሚገናኙበት የመሬት ሰርጥ፤ ቤሪንጊያ ከበረዶ ሽፋን ተገልጦ በወጣ ጊዜ ስፋቱ 1500 ኪሎ ሜትሮች እንደነበር ይታሰባል። በእርጥበት በሳር እና በአትክልቶች የተሸፈነው ይህ አካባቢ የቀድሞ ሰዎች ለእለት ጉርሳቸው ሲሉ ያድኗቸው የነበሩ እንስሳትን እየሳበ መጣ።
የመጀመሪያዎቹ ወደ ሰሜን አሜሪካ የገቡት ሰዎች አዲስ አህጉር አቋርጠው መግባታቸውን አያውቁም ነበር። እነርሱ ከሺዎቹ ዓመታት በፊት በሳይቤሪያ ጠረፍ በኩል አልፈው እና በየብስ ድልድዩ በቤሪንጋ ሰርጥ በኩል አቋርጠው ይጓዙ የነበሩ አባቶቻቸውን ፈለግ እየተከተሉ ነበር።
አላስካ ውስጥ መኖር እንደጀመሩ፤ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ሰሜን አሜሪካውያን ወደ ዛሬዋ አሜሪካ ግዛቶች ሰርገው ለመግባት ሺዎቹን ዓመታት የወሰደባቸው መሆኑን ታሪክ ያስረዳል። በዚህ አካባቢም የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የእንስሳት አደን ይከናወን ነበር። ነገር ግን እንስሳቱ በጊዜ ሂደት ከመጠን በላይ በመታደናቸው እና በአየር ንብረት ለውጥ አለመስማማት የተነሳ በመጥፋታቸው እርሻ የቀደምት ሰሜን አሜሪካውያን መተዳደሪያ ሆነ።
አሁን በማዕከላዊ ሜክሲኮ በሚባለው ስፍራ ተወላጅ አሜሪካኖቹ በቆሎ፣ ስኳሽ ድንች እንዲሁም ባቄላ የማብቀል የእርሻ ስራ ለመጀመር ተገደዋል። ምናልባትም ይህ በ8000 ቅድመ ዓለም መጀመሪያ ላይ ነበር። “እንቁላል ቀስ በቀስ …” እንዲሉ፤ ይህ እውቀት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተስፋፍቷል። በ3000 ቅድመ ዓለም በኒው ሜክሲኮ እና በአሪዞና በቆሎ በኋላቀር መንገድ ያተክሉ ነበር። ከዚያም የመስኖ ምልክቶች እና የቀደምት የገጠር መንደር ሕይወት የመኖር ምልክቶች መታየት እንደጀመሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ተወላጅ አሜሪካውያን አሜርኢንዲያኖች የሚባሉ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ተመናምነዋል። ተወላጆቹም በበሽታ እና በተለይ ደግሞ ከአውሮፓ በመጡ ቅኝ ገዥዎች ወታደራዊ የበላይነት ተገድደው ቁጥራቸው በእጅጉ ቀንሷል።
ቀደምት ሰፈራዎች
በ1600ዎቹ መጀመሪያ ከአውሮፓ ወደ ሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ ፍልሰት መካሄድ ጀምሮ ነበር። ሶስት ክፍለ ዘመን ለሚሆን ጊዜ የተደረገው ይህ እንቅስቃሴ በመቶዎቹ ከሚቆጠሩ ጥቂት የእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች ስደት እስከ ሚሊዮኖች በሚቆጠር አዳዲስ መጤዎች የስደት ጎርፍ ተጥለቅልቋል። በሀይለኛ እና ልዩ ልዩ አላማዎች ተገፋፍተውም በሰሜን አሜሪካ አህጉር ውስጥ አዲስ ስልጣኔ ገነቡ።
የመጀመሪያዎቹ የእንግሊዝ ስደተኞች አትላንቲክን አቋርጠው በአሁኗ አሜሪካ መጤዎቹ ስፔኖች በሜክሲኮ፣ ዌስት ኢንዲስ እና በደቡብ አሜሪካ የስፔናውያኑ ቅኝ ግዛቶች ከተመሰረቱ ረጅም ዓመታት በኋላ ነበር የመጡት። ልክ እንደ ሁሉም ተጓዦች ወደ እንግሊዞችም በአነስተኛ እና በብዙ ሰዎች በተጣበበ መርከብ ነበር አዲሱ ዓለም የመጡት። ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ሳምንታት በሚያደርጉት ጉዞ በቂ ምግብ አያገኙም። አብዛኞቹ አውሮፓውያን ስደተኞች የትውልድ ሀገራቸውን ለቀው ወደ አዲሲቷ የአሜሪካ ምድር ይመጡ የነበረው ከፖለቲካዊ ጭቆና ለማምለጥ፣ ሀይማኖታቸውን የመተግበር ነፃነት ለማግኘት፣ ወይም ከሀገራቸው የተከለከሉትን እድል ለማግኘት ነበር።
በ1612 እና በ1627 ዓ.ም መካከል በነበሩት ዓመታት እንግሊዝ ከፍተኛ በሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተመታለች። በርካታ ሰዎች ስራ ማግኘት አይችሉም ነበር። የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንኳ ለመኖር የሚያስችል እስኪያጡ ተቸገሩ። የሰብል ምርት መዳከም “ከእንቅርት ላይ…”እንዲሉ ሆነ። በተጨማሪም በወቅቱ የተነሳው የንግድ አብዮት የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዉን ፈጥሮ ነበር። ይህ ደግሞ ፋብሪካዎቹ የሚፈልጉት የሱፍ ግብአት ፍላጎት እንዲጨምር አድርጎታል። እናም የመሬት ከበርቴዎችም በጎችን ለማርባት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በመከለላቸው አርሶ አደሮቹን አፈናቀሏቸው። ቅኝ ግዛት ማስፋፋት ተፈናቃይ አርሶ አደር ሕዝብን ማስወጪያ ቀዳዳ ሆነ።
የቅኝ ገዥዎቹ በአዲሱ ምድር የመጀመሪያ የአይናቸው ማረፊያ የሆነው ሰፊ ጥቅጥቅ ባሉ ዛፎች የተሞላው ምድር ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች እንግዳ ወዳጅ ሕንዳውያን እርዳታ ባያደርጉላቸው ኖሮ በሕይወት መቆየት ባልቻሉ ነበር። የአካባቢውን እንደ ዱባ፣ ባቄላ እና በቆሎ እንዴት ማብቀል እንዳለባቸው አስተምረዋቸዋል።
በተጨማሪም በግምት ወደ 2100 ኪሎ ሜትር በሚሆን መሬት ላይ የተዘረጉ ሰፋፊ ድንግል ጫካዎች ያለበት ስፍራ የብዙ የእንስሳት እና የማገዶ ምንጭ መሆኑን አረጋገጡ። እንዲሁም ከራስ አልፈው ለቤት፣ የቤት ቁሳቁስ፣ ለመርከቦች መስሪያ እና ለሌሎች ቁሳቁስ የሚጠቅሙ ጥሬ እቃዎችን ለገበያ ያቀርቡ ነበር።
የሰሜን አሜሪካ ጠረፋማው ክፍል ስደተኞቹን በደንብ አገልግሏል። ጠረፋማው ክፍል ከውቅያኖስ ጋር የሚያገናኝ ወደቦች ነበሯቸው። ሰሜን ካሮሊና እና ደቡባዊ ኒውጀርሲ የተባሉ ሁለት ቦታዎች ነበሩ ወደብ ያልነበራቸው። ኬኒቤክ፣በርካታ ሁድሰን፣ ዴላዌር፣ ሱስቁሃና፣ ፖቶማክ፣ እና በርካታ ሌሎች ትላልቅ ወንዞችም በጠረፉ እና በአፓላቺያን ተራሮች መካከል ያሉ መሬቶች በባህር ማገናኛነት አገልግለዋል። ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች፣ የአንዳንድ ህንዳውያን ተግዳሮት እና የአፓላቺያን ተራሮች ጠንካራ አጥር ሰፈራራዎችን ከጠረፉ ባሻገር ማከናወን ተስፋ አስቆራጭ አድርጎት ቆይቷል። በመሆኑም ቅኝ ገዥዎቹ የመጀመሪያዎቹን መቶ ዓመታት ሰፈራዎችን ጠረፍ ለጠረፍ ገንብተዋል።
በሰሜን አሜሪካ 13 የእንግሊዝ የሰፈራ እና የእርሻ ቅኝ ግዛቶች ተመሰረቱ። በሰሜን ከካናዳ እስከ ፍሎሪዳ በስተደቡብ እና ከአትላንቲክ ውቂያኖስ ወደቦች እስከ አፓላቺያን ተራሮች ድረስ ይዘረጋል፣ ይህም አሁን አሜሪካ የሚባለው ነው። ከአፓላቺያን ተራሮች ባሻገር ማዶ ጥቂት የነጮች የሰፈራ መንደሮች ብቻ ነበሩ። የህዝቡ ቁጥር በፍጥነት ጨመረ፣ ምክንያቱም ቅኝ ገዥዎች በወጣትነት ስለሚያገቡ ብዙ ይወልዱ ስለነበር ነው። ስደተኞች ለተሻለ ሕይወት ወደ አዲሱ ዓለም መምጣታቸውንም ቀጠሉ። በ1767 ዓ.ም የ13ቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች የሕዝብ ቁጥር 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህል ሲሆን ነጮች ያልሆኑ ግማሽ ሚሊዮን ነበሩ፣ እነርሱም ትውልደ አፍሪካዊ ባሮች ነበሩ።
ምንጭ ፦ ብሪፍ ሂሰተሪ ኦፍ አሜሪካ፣
ይቀጥላል
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም