“የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ”

0
221

የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

የወባ በሽታ ዋነኛ መተላለፊያ ወቅቶች ሁለት ሲሆኑ ከመስከረም እሰከ ታህሳስ ያለው ዋናው የመተላለፊያ ወቅት ነው። ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ድረስ ደግሞ በመለስተኛ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ እነዚህም ሁለቱ የመተላለፊያ ወቅቶች ከክረምትና ከበልግ ዝናብ ጋር ተያይዞ ለወባ አስተላለፊ ትንኞች ምቹ የመራቢያ ሁኔታ ስለሚያገኙ እና ቁጥራቸው በጣም ስለሚጨምር ነው፡፡

አማራ ክልል 80 በመቶ የሚሆነው የቆዳ ስፋት ለወባ መራቢያ ምቹ እና 80 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ ደግሞ ለወባ የተጋለጠ ነው፡፡ በዚህም 99.8 በመቶ የሚሆኑት ወረዳዎች የወባ ስርጭት ያለባቸው እና 82.5 በመቶ የሚሆኑ ቀበሌዎችም ወባማ ናቸው፡፡ 91 በመቶ የሚሆነውን የወባ ስርጭት የምዕራቡ ክፍል የሚሸፍን ሲሆን  የወባ ስርጭትን ወቅት ጠብቆ የሚጨምር ወይም የሚቀንስ ነው።

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሃብታሙ ተመስገን እንደገለፁት በ2016 በጀት ዓመት በአማራ ክልል በአጠቃላይ 1,511,906 የወባ ህሙማን የተመዘገቡ ሲሆን የ2016 የወባ ተጠቂዎች ቁጥር ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ በ34 ወረዳዎች 1,083,269 (71.6 በመቶ) የወባ ህሙማን ተመዝግበዋል፤ አስራ ሶስት የልማት ቀጠናዎች ደግሞ ከ24 እስከ 35 በመቶ ድርሻ ሸፍነዋል።

እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ የወባ በሽታ በአማራ ክልል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። በ2017 በጀት ዓመት እስከ ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም 696,325 የወባ ህሙማን ተመዝግበዋል። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 70 ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

 

ለወባ በሽታ መጨመር ምክንያቶች

አቶ ሃብታሙ እንደገለፁት የመኝታ አጎበር ሲበላሽ በወቅቱ አለመተካት፤ ማሕበረሰቡ የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀምና አለመያዝ፣ ለሌላ ዓላማ ማዋል፤ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን በመለየት ማህበረሰቡን በማሳተፍ መደበኛ የሆነ የአካባቢ ቁጥጥር ተግባር አለመፈጸም፤ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ የመስኖ ግድቦች ላይ ክትትል አለማድረግ እና ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ አለመሰራቱ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በኬሚካል እጥረት ምክንያት የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት የሚካሄድባቸው ቀበሌዎች ዝቅተኛ መሆን፣ ወደ ወባማ አካባቢዎች የሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲሁም ከግጭት ጋር ተያይዞ በርካታ ተፈናቃይ የህብረተሰብ ክፍሎች በክልሉ በመኖራቸው ተጨማሪ ጫና መፍጠሩንም የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ተናግረዋል።

 

የወባ በሽታን መከላከያ ስልቶች

እስካሁን ድረስ ለመከላከል የተደረጉት ስልቶች በቀበሌ ደረጃ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ከእቅድ ጀምሮ የሥራው ባለቤት እንዲሆን የማድረግ፣ በቀበሌ ደረጃ ያሉ የማህበረሰብ አደረጃጀቶችን በመጠቀም    በወባ መከላከል ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በትምህርት ቤት የጸረ-ወባ ክበብ ማቋቋም እና ማጠናከር፣ የወባ ቁልፍ መልዕክቶች በሚዲያ እንዲሁም ድራማዊ በሆነ መልኩ በገበያ፣ በት/ቤት እና ማህበረሰብ በተሰበሰበበት ቦታ የማስተላለፍ ተግባራት ተከናውነዋል።

የመኝታ አጎበሩን ከ3 እስከ 5 ዓመት እንዲያገለግል ማድረግ እና በቤት ውስጥ ያለው አጎበር ለሁሉም ቤተሰብ የማይበቃ ከሆነ ቅድሚያ ለህጻናትና ለነፍሰጡር እናቶች በመስጠት መገልገል እንደሚገባም አቶ ሃብታሙ አስገንዝበዋል።

የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ማካሄድና የተረጩ ቤቶችን ግድግዳ በእበት፣ በጭቃ እና በአመድ አለመለቅለቅ፣ በወረቀት ወይም በፕላስቲክ አለመሸፈን ተገቢ መሆኑም ተገልጿል።

የወባ በሽታ መከላከል ስልቶችን እየተጠቀምን ምናልባት የወባ ህመም ምልክቶች ቢታዩ በሽታው በስፋት እንዳይተላለፍ እና እንዳይከሰት ወዲያዉኑ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራና ህክምና ማድረግ ተገቢ ነው።

የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት

የአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ቢሮ፤ ከፌዴራል መንግስት እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በሽታው የከፋ ጉዳት  እንዳያስከትል የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ነው። እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከልም ሁሉን አቀፍ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራን ለማጠናከር ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ግብረ ኃይል እና ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡

የወባ ሁኔታ በድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ማሳለጫ ማዕከል እንዲመራ ተወስኖ በየቀኑ እና በየሳምንቱ እየተገመገመ ክትትል እየተደረገበት ይገኛል፡፡

በየሳምንቱ የወባ ስርጭቱን እና የመከላከል ተግባሩን በበይነ መረብ ከጤና ሚኒስትር እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዘወትር ሰኞ ሰኞ እንዲሁም ከሁሉም ዞኖች ጋር ዘወትር ማክሰኞ ክትትልና ግምገማ ይደረጋል።  በተመረጡ ዞኖች እና ወረዳዎች የተቀናጀ የድጋፍና ክትትል ስራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው 22 ወረዳዎች 26ሽህ 8 መቶ 42 ኪሎ ግራም መጠን ያለው የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ተካሂዷል።  ያጋጠመው የግብዓት እጥረት አሁን ካለው በከፋ ደረጃ እንዳይደርስ እቅድ ታቅዶ ክትትል እየተደረገም ይገኛል።

የስጋት ተግባቦት ስራዎች፣ የመኝታ አጎበር አጠቃቅም፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ እና የወባ ቅድመ ምርመራ እና ህክምና ስራዎች እየተሰሩ ነው። ሁሉም የህክምና ተቋማት በሃገሪቱ የወባ ምርመራ እና ህክምና መመሪያ መሰረት እንዲሰሩና የየዕለት የመረጃ ልውውጥ እንዲያደርጉም ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

 

መከናወን ያለባቸው ቀጣይ ተግባራት

የአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ ያለውን ከፍተኛ የወባ ጫና ለመቀነስ ሁሉን አቀፍ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ስራን ለማጠናከር ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ግብረ ኃይል እና ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተፈፀመ እንደሚገኝ ገልጿል።

ማህበረሰቡ በመኝታ አጎበር ዙሪያ ያለውን እውቀት፣ አመለካከትና ክህሎት እንዲያሳድግ መስራት፣ አጎበር በትክክል የወባ ትንኝ እንዳያስገባ ተደርጎ መሰቀል እንዳለበት ማስተማር እና በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ተግባራዊ መደረጉን መከታተል ከእያንዳንዱ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

የጤና ትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ መድረኮች በትምህርት ቤት፣ በእምነት ተቋማት፣  የህዝብ መሰብሰቢያዎች በማመቻቸት ለሕብረተሰቡ መስጠት ይገባል።  ሁሉም አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ በጋራ በመስራት የወባ በሽታ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል መከላከልና መቆጣጠር ይገባል።

በአጠቃላይ የወባ ስርጭቱ እንደ ክልል አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ማሳለጫ ማዕከል የወባ በሽታ በድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች የክስተት አስተዳደር ስርዓት እንዲመራ ተወስኖ በየቀኑ እና በየሳምንቱ እየተገመገመ ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡

“የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” በሚል መሪ ቃል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ የሚተገበር ክልላዊ ጤና ጣቢያ መር ማህበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በዘመቻ ዘወትር አርብ ጠዋት ከአንድ እስከ ሦስት ሰዓት ከጥቅምት 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 2017 ዓ.ም መጨረሻ እየተተገበረ ይገኛል።

የወባ አስተላላፊ ትንኞች የሕይወት ዑደታቸውን ለማጠናቀቅ ከ7 እስከ 12 ቀናት የሚጠብቅ በመሆኑ በሳምንት አንድ ቀን በመተግበር የወባ ትንኝ ቁጥርን ከምንጩ ለመቀነስ ይቻላል። በዚህም ሁሉም የክልሉ ነዋሪ በሚኖርበት አካባቢ እና በሥራ ቦታ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን፣ በወንዝ፣ በሃይቅ፣ በኩሬ፣ እንዲሁም ውሃ በሚቋጥር የዛፍ ቅጠል፣ የእንስሳት ዱካ፣ በተጣሉ ጎማዎች፣ በሰባራ ሸክላዎች፣ ሰው ሰራሽ የሆኑ የውሃ  ማጠራቀሚያዎችን የማፅዳት፣ የማፋሰስ እና የማዳረቅ ስራዎችን በመተግበር የወባ ስርጭትን መቀነስ እና መግታት ይገባል።

የበሽታውን ተፅዕኖ ለማህበረሰቡ ማስረፅ፣ ቤተ- እምነቶች፣ ሚዲያ ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላትና ጤና ባለሙያዎች ማህበረሰቡን አስተባብረው መሥራት፣ ተከታታይ የጤና ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር እያደረሰ ያለውን የጤና መቃወስ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮት ለመቀልበስ ማህበረሰቡ ሁልጊዜም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት መሥራት ይጠበቃል።::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here