ዞኑ ተማሪዎችን መዝግቦ እያስተማረ መሆኑን አስታወቀ

0
123

የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

የመማር ማስተማሩን ሥራ በውጤታማነት ለማስኬድ ሁሉም አካባቢ ሰላም መሆን እንዳለበት የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ አሳስቧል፡፡

በዞኑ በ2017 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት 768 ሺህ ተማሪዎችን ለማስተማር በእቅድ ይዞ 440 ሺህ ተማሪዎችን በመመዝገብ  ወደ ሥራ መገባቱን የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ  ዓለምነው አበራ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ አንድ ሺህ 210 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 68 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው ከነዚህ ውስጥ 70 የአንደኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች እና አራት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባ እንዳልጀመሩ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም በዞኑ ትምህርት ሳይቆራረጥ የመማር ማስተማር ሂደቱ የተጀመረባቸው አምስት ወረዳዎች ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ መንገድ ለማስኬድ የክልሉ  ግጭት እንቅፋት እንደሆነበት መምሪያው አስታውቋል። በትምህርት ቤቶች ምዝገባ ከተካሄደ በኃላ መልሰዉ የተቋረጡ ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ተናግረዋል::አሁንም ቢሆን ወደ ትምህር ቤት የሚመጡ ተማሪዎችን ያለማቋረጥ በመመዝገብ፣ ክትትል በማድረግ እና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል:: የበጀት  ዓመቱ የመጽሐፍ ችግር የተቀረፈበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመጻሕፍት ስርጭቱን ለማሟላት ክልሉ ሦሥት ነጥብ አራት ሚሊዮን መጽሐፍ እንደመደበ ኃላፊው ተናግረዋል:: መጻሕፍቱ ታትመው ወረዳዎች ለተማሪዎቻቸው ማሰራጨታቸውን ገልጸዋል::

መምሪያ ኃላፊው እንዳሉት ማንኛውም ተማሪ ያለስጋት በሰላም እንዲማር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት::

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here