ለንብ ሃብት ልማት ትኩረት ያስፈልገዋል ተባለ

0
154

የአማራ ክልል ለንብ ሃብት ልማት ምቹ የአየር ጸባይ፣ የመሬት አቀማመጥ እና የተለያዩ የቀሰም እፅዋት ያሉበት ነው።

የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው የክልሉ 72 በመቶው መልክዓ ምድር ቆላ እና ወይና ደጋ፣ ከአራት ሺህ በላይ በተለያዩ ወቅቶች የሚያብቡ የእጽዋት ዝርያዎች የሚገኙበት መሆኑ ለንብ ሃብት ልማት ሥራው አመቺ አድርጎታል።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብ፣ ሃር ልማት እና ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን እንደገለፁት በ2017 በጀት ዓመት የማር ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው። የንብ ሃብት ልማት በአነስተኛ መነሻ ካፒታል (ገንዘብ) እና በውስን መሬት ላይ ወደ ሥራ በማስገባት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ  በ”ሌማት ትሩፋት” ትኩረት ከተሰጣቸው  የልማት ሥራዎች አንዱ ነው ብለዋል።

በክልሉ ያለውን ባሕላዊ ቀፎ ወደ ዘመናዊ የማዛወር ሥራም እየተሠራ ነው። በበጀት ዓመቱ ለማዛወር ከታቀደው 95  ሺህ ቀፎዎች ውስጥ  እስካሁን 51 ሺህ 836 ህብረ ንቦችን ወደ ዘመናዊ እና ሽግግር ቀፎዎች ማሸጋገር ተችሏል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 28 ሺህ 249 ወደ ዘመናዊ ቀፎዎች የተሸጋገሩ ናቸው።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ሌላው የበጀት ዓመቱ ትኩረት ደግሞ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ የህብረ ንብ የማባዣ ዘዴዎችን በመጠቀም አዲስ ህብረ ንቦችን ማግኘት ነው። 

በዓመት ለማግኘት ከታቀደው 183 ሺህ 720 አዲስ ህብረ ንብ አስከ ጥቅምት መጨረሻ 121 ሺህ 230 ሺህ ማሳካት መቻሉን ባለሙያው ገልጸዋል።

በክልሉ የሚመረተውን የማር ምርት እሴት ለመጨመር  አምስት የማር እና ሰም ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በማቋቋም ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት። የላሊበላ ብሔራዊ የንብ ሃብት ሙዚየም ወደ ሥራ መግባቱም ሌላው አቅም መሆኑን አስረድተዋል።

ለአረም እና ለተለያዩ ተባዮች በየጊዜው የሚረጨው ኬሚካል አሁንም የንብ ማነብ ሥራውን እየፈተኑት እንደሚገኙ አንስተዋል። በመሆኑም ለንቦች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አርሶ አደሩም ሆነ ባለሙያው በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል።

የዘመናዊ ቀፎ፣ የማር ማጣሪያ እና የመሳሰሉ የንብ እርባታ ግብዓቶች እና ቴክኖሎጅዎች ዋጋ መናር ከማኅበረሰቡ አቅም ጋር ተዳምሮ ወደ ዘመናዊ ንብ እርባታ ለመሸጋገር ፈተና ሆኗል፡፡

የዕውቀት፣ ሥልጠና እና የበጀት ችግርም ሌላው ማነቆ ነው።

የክልሉን የማር ምርት ለማሳደግ አሁን በክልሉ ያለውን 95 በመቶ የሚሆነውን ባሕላዊ አናቢ ወደ ዘመናዊ አናቢ ማሸጋገርም ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት በተደራጀ መንገድ በበጀት ሊደግፍ ይገባል። የብድር አቅርቦት ማመቻቸት፣ ለአናቢዎች ሥልጠናዎችን ማስፋት እና ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድ ይገባልም ተብሏል።

በ2017 ዓ.ም በክልሉ ከሚገኘው 492 ሺህ 800 አናቢዎች 31 ሺህ 531 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ 10 ሺህ 500 ቶን ማር ተመርቷል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here