ወረቀትን በመሰነጣጠቅ – ባለ ክብረ ወሰኑ

0
122

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ቻይናዊው ፔይ ሃኦዚንግ 20 በ30 ሴንቲ ሜትር የተለካን “ኤ4” ወረቀት በግማሽ ሚሊ ሜትር ስፋት በአንድ ወጥ 108 ሜትር ርዝመት መሰንጠቅ በመቻሉ ልዩ ክብረወሰን ማስመዝገቡን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሰሞን አስነብቧል፡፡

በጃፓን የወረቀት አስተጣጠፍ ጥበብ “ኦሪጋሚ” የተካነው ጠቢብ ለዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ባይተዋር አለመሆኑ ነው የተገለፀው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብሎ አንድ  “ኤ4” መጠን ያለውን ወረቀት 100 ሜትር በመሰነጣጠቅ የቀንዳ አውጣ ምስል ሰርቶ ስሙ በድንቃድንቅ መዝገብ በመስፈሩ ነው፡፡

ፔይ ሃኦዚንግ በመጀመሪያው ክብረወሰን ልምድ በማግኘቱ  የበለጠ ፈታኝ የሆነውን አንድ ወረቀትን በረዥሙ ለመሰንጣጠቅ ራሱን አዘጋጅቷል፡፡ የተለያዩ የመቁረጫ መሣሪያዎችንም ሞክሯል፡፡ በመጨረሻም ለስኬታማነቱ መቀስን መርጦ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ልምምድ እና ማብቂያው አንድ ዓመት ጊዜ እንደወሰደበት ነው የተናገረው- ፔይ ሃኦዚንግ፡፡

ባለተሰጥኦው ጠቢብ ያሰበውን በስኬት ለማጠናቀቅ “ኤ4” ወረቀቱን ይዞ በተነጠፈ መስታዉት ላይ ተቀምጦ ለመሰነጣጠቂያ በመረጠው መቀስ ትእግስት እና  ችሎታ የሚጠይቀውን የመጨረሻ ስራውን ይያያዘዋል፡፡

ፔይ ሃኦዚንግ ጥንታዊ መቆራረጫ መሣሪያ የሆነውን መቀሰን በመገልገል አንዱን ገፅ ወረቀት እንደሳር በቀጠነ ስፋት 108 ሜትር አንድ ወጥ ርዝመት መሰነጣጠቅ ችሏል፡፡

ጠቢቡ  የሰነጣጠቀውን 108 ሜትር የሚረዝም ወረቀት በጥንቃቄ በማጣጠፍ አስደናቂ ምስል መፍጠሩንም ነው ያበሰረው፡፡ ምስሎም የጭንቅላት ውስጥ የአንጐል ነርቭ አቀማመጥን የሚያሳይ መሆኑን ነው የአብራራው -ፔይ ሃኦዚንግ፡፡

በመጨረሻም ፔይ ሃኦዚንግ  “ኤ4” መጠን አንድ ገፅ ወረቀትን ከእግር ኳስ ሜዳ በሚስተካከል ርዝመት ሳይቆራረጥበት መሰነጣጠቅ መቻሉ ተዓምር መሆኑን እና በቅርብ ጊዜ ክብረ ወሰኑ ይሰበራል የሚል እምነት እንደሌለው ነው ያደማደመው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here