ሺሬቶኮ ብሔራዊ ፓርክ

0
143

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ፓርኩ በጃፓን ሆካይዶ ክልል የሚገኝ ሲሆን ሰኔ 1/1964 እ.አ.አ ነው በብሔራዊ ፓርክነት የተሰየመው:: የፓርኩ ስፋት 38,954 ሄክታር ተለክቷል:: በመልካምድራዊ አቀማመጡም ከባሕር ዳርቻዎች እስከ ትልልቅ ተራራዎች የተለያዩ ስነምህዳሮችን  አካቶ ይዟል::

ፓርኩ በሰሜን ምስራቅ ሆካይዶ ከሺሬቶኮ ሰርጥ ጋር የተያያዘ ቀጠና ነው:: የፓርኩ ክልል በጃፓን ለጠረፍ  በቅርበት ከሚገኙ ቀጣናዎች መካከል ይጠቀሳል:: በመሆኑም ፓርኩን ለመጐብኘት በእግር ወይም በጀልባ ብቻ ነው የሚመከረው::

የሺሬቶኮ ቀጣና በልዩ ስነ ምህዳር መገኛነቱ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት እውቅና ተሰጥቶታል::  መመዘኛዎቹም የባህር በረዶ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በውቅያኖስ እና በየብስ መካከል ያለው ግንኙነት ማሳያነቱ፣ የመሬት፣ ወንዞች  የውቅያኖስ ትስስር ለስነምህዳር ሀብት እና ብዝሃነትን ማካተቱ፣ በሦስተኛነት በየብስ እና በባህር ላይ የተለያዩ የዱር አራዊት መገኛነቱ ናቸው:: በመሆኑም ሦስቱ የተዘረዘሩት እውነታዎች እና ልዩ ቀጣናነቱ በዓለም ቅርስ መዝገብ ለመካተት አብቅተውታል- ሺሬቶኮ ብሔራዊ ፓርክን::

በጥቅሉ 36 የየብስ አጥቢ እንስሳት፣ 22 የባህር ውስጥ  እንዲሁም 285 የዓእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙ ነው- ድረ ገፆች ያሰፈሩት::

እፅዋትን በተመለከተ በባህር ዳረቻዎች እና በተራራዎች ግርጌ ደን ለብሷል – የሺሬቶኮ ብሔራዊ ፓርክ:: ስነምህዳሩ በውቅያኖስ፣ ወንዞች እና በደን መካከል ህብር መፍጠሩ ለዱር እንስሳት ህልውና ምቹ እና ተመራጭ አድርጐታል::

ሺሬቶኮ ፓርክን ለመጐብኘት ከፀደይ እስከ መኽር ያለው ወቅት ተመራጭ ነው:: ምንው? ቢሉ በቀጣናው የሚገኙ  ሀይቆችን፣ የተደበቁ ፏፏቴዎችን በወጉ መመልከት በማስቻሉ ነው::

ወደ ፓርኩ ለመጓጓዝ ከቶኪዮ ዓየር ማረፊያ ወደ አቅራቢያው የአንድ ሰዓት ተኩል በረራ ማድረግ ግድ ይላል:: ከዚያም በበጋም ሆነ በክረምት ሁለት ሰዓት በአውቶብስ ተጉዞ በሁለት አቅጣጫ በሚገኙት በሮች ደርሶ መግባት ያስችላል::

ለዘገባችን ግሎባልናሽናል ፓርክ፣ ሺሬቶኮ ሲሪያ፣ ጃፓን ትራቭል ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here