የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሲፈተሸ

0
119

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በአማራ ክልል በተያዘው ዓመት ከ254 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዷል፤ በዚህም ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው መረጃው ያመላከተው::

በኩር ጋዜጣ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖሩ አርሶ አደሮች እንዳረጋገጠችው አርሶ አደሮች የመኸር ምርትን በመሰብሰብ ጎን ለጎንም ለበጋ መስኖ ልማት እየተዘጋጁ ነው፤ ለዚህም ኮምፖስትን በብዛት እና በጥራት እያዘጋጁ እንደሆነ ነው በስልክ ባደረሱን መረጃ ያረጋገጡልን::

ሐሳባቸውን ከሰጡን መካል አርሶ አደር አንተነህ መለሰ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓንጓ ወረዳ ጥሩ ብርሐን ቀበሌ ነዋሪው አንዱ ናቸው:: አርሶ አደሩ መሬታቸውን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የአፈር ለምነት እንዲጨምር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።  የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) በብዛት ይጠቀማሉ። ከዓመት ዓመት በተሻለ መንገድ በብዛት እና በጥራት እያዘጋጁ መሆኑንም ነግረውናል።

በ2016 ዓ.ም ከሦስት ሔክታር መሬታቸው ውስጥ ከግማሽ በላይ መሬታቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም እንደዘሩ አስታውሰዋል። በተለይም ለአትክልት እና ፍራፍሬ ሁልጊዜ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደሚጠቀሙ ነግረውናል። ስለ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ሲናገሩም “የመሬቱን ለምነት በመጨመር ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚናን ይጫወታል” ብለዋል። በሥራቸው ላይም የግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጓንጓ ወረዳ የሚኖሩት ሌላው አርሶ አደር ዘመኑ ሳህለው በበኩላቸው “እየሰጠ ያለውን ጥቅም ተረድቼ ኮምፖስት ማዘጋጀት እና መጠቀም ከጀመርኩ ስድስት ዓመታት ሆኖኛል” ብለዋል። ይህን በማድረጋቸው ምርታቸው መጨመሩን ነው የነገሩን። “የተፈጥሮ ማዳበሪያ የምጠቀምበት መሬት የአፈር ለምነቱ የተሻለ ነው፤ ይህም የተሻለ ምርት እንዳገኝ ረድቶኛል” ብለዋል።

ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በዚህ ዓመት አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ በብዛት እየተዘጋጀ ከሚገኝባቸው መካከል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ይገኝበታል፤ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አበርገሌ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ኃይሌ በላይ ኮምፖስትን በብዛት እንደሚጠቀሙ ነግረውናል፤ ለዘንድሮው የበጋ ወቅት የግብርና ሥራቸውም ኮምፖስት ማዘጋጀታቸውን ነው በስልክ የነገሩን።

አርሶ አደሩ እንደተናገሩት በመደበኛው የግብርና ወቅት የዘሩትን ማሳ በመሰብሰብ ላይ ናቸው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለበጋ መስኖ ልማት እየተዘጋጁ ነው::

ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በበጀት ዓመቱ ከ662 ሺህ ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ በእስካሁኑ ሂደትም ከ156 ሺህ ሜትር ኩብ በላይ መደበኛ ኮምፖስት ተዘጋጅቷል:: ሥራውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው መምሪያው ያስታወቀው::

በተያዘው በጀት ዓመት ለሚከናወነው የመስኖ፣ የበልግ እና የመኸር እርሻ ሥራ የሚውል ከ66 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ መደበኛ ኮምፖስት (የተፈጥሮ ማዳበሪያ) ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ከመደበኛ ኮምፖስት በተጨማሪም ቨርሚ እና ባዮሳላሪ ኮምፖስት እየተዘጋጀ መሆኑን የቢሮው መረጃ ይጠቁማል። በዚህ ዓመት የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት የሚያስችል እንደሆነ መረጃው ያሳያል።

በክልሉ በተያዘው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 254 ሽህ 100 ሄክታር መሬት በማልማት ከ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል። በአንደኛው ዙር መስኖ በአብዛኛው በበጋ መስኖ ስንዴ የሚሸፈን ይሆናል ተብሏል።

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት ለማዘጋጀት ከታቀደው 66,659,991 ሜትር ኪብ መደበኛ ኮምፖስት ውስጥ 60,082,808 ሜትር  ኪዩብ (90 በመቶ አፈጻጸም) ተዘጋጅቷል::::

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here