የተማሪ ምገባዉ ለትውልድ ግንባታ

0
156

የህዳር  16 ቀን 2017 ዓ.ም

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ቀድሞውንም በጥራት እና በተደራሽነት ከፍተኛ ትችትን የሚያስተናግደው ትምህርት በተለይ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ እጅጉን እየተፈተነ ይገኛል። በወቅቱ የተፈጠረው እና አሁንም ድረስ መልኩን እየቀያየረ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የቀጠለው ግጭት ከተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተደምሮ ትምህርት ክፉኛ እየተፈተነ እንዲመጣ አድርጎታል::

በሌላ በኩል መፍትሄ አጥተው ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቁት ግጭቶች በሚፈጥሩት አሉታዊ ተዕጽኖ እና ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ዘጠኝ ዞኖች እና 43 ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ ሚሊዮኖች ተማሪዎችን ከትምህርት እንዳያርቅ በመስጋት የክልሉ መንግሥት የተማሪ ምገባ ማስጀመሩ ይታወሳል:: የተማሪ ምገባ የተጀመረው የክልሉ መንግሥት በመደበው 75 ሚሊዮን ብር ሲሆን በዋናነት የምገባ ፕሮግራሙ ተደራሽ የሚሆነው በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ነው:: የገምገባ ፕሮግራሙ  ተማሪዎች በሰዓቱ በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ፣ ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ፣ ያቋረጡት እንዲመለሱ፣  አዘውትረው ትምህርት ቤት እንዲገኙ እና ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማስቻሉን ተማሪዎች ተናግረዋል::

የተማሪ ምገባው ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የተረዱት ዛሬ ተሞክሮውን አስፍተው አስቀጥለዋል:: በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በአርዓያነት ይነሳል:: ከተማ አስተዳደሩ የተማሪ ምገባን በይፋ ያስጀመረው በ2015 ዓ.ም ለ500 ተማሪዎች ነበር። ቁጥሩ በ2016 ዓ.ም ወደ አምስት ሺህ አድጓል:: በ2017 ዓ.ም 12 ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል::

አሚኮ ያነጋገራቸው ተማሪዎች እና ወላጆች  የተማሪ ምገባ መጀመሩ በተለይ ከእጅ ወደ አፍ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ እፎይታን እንደሚሠጥ ገልጸዋል። ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ሳያቋርጡ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ትምህርታቸውን በንቃት ተከታትለው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል::

የኮምቦልቻ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ብርሐኑ ድንቁ የተማሪ ምገባ ፕሮግራሙ በተለይ በጣም ለችግረኛ ተማሪዎች ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል:: ከዚህ ባለፈ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ፣ ተማሪዎች ትምህርት ቤቱን ወደው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ እና የውጤት መሻሻል እንዲመጣ ማድረጉን ጠቁመዋል:: ወላጆችም ትምህርት ቤቱ የኔ ነው ብለው ለልጆቻቸው የነገ መዳረሻ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሠሩ መሆኑን ርእሰ መምህሩ ገልጸል::

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግሥቱ አበበ እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ የምገባ ተጠቃሚ የሚሆኑ ተማሪዎች መሠረታዊ የሆነ የምግብ አቅርቦት ውስንነት ያለባቸው ናቸው:: ምገባ በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች የአቋራጭ ተማሪዎች ቁጥር ሙሉ ለሙሉ መቆሙንም አረጋግጠዋል:: ተማሪዎች አዘውትረው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ፣ የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት እንዲከታተሉ፣ በውጤትም መሻሻል እንዲያሳዩ ማስቻሉን የምገባው አወንታዊ ተፅዕኖ ማሳያ አድርገው አንስተዋል::

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ መሀሙድ አሚን የሱፍ የ2017 ዓ.ም የምገባ ፕሮግራምን ባስጀመሩበት ወቅት ለምገባ ፕሮግራሙ 75 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል:: ለፕሮግራሙ እውን መሆን ከተማ አስተዳደሩ 50 ሚሊዮን ብር መመደቡን እና ቀሪው 25 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከከተማዋ ነዋሪዎች እና ከባለሐብቶች እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል::

“ከልማቶች ሁሉ የላቀው ልማት የተማሪ ምገባ ነው” ያሉት ከንቲባዉ፣ ነገን ለመገንባት የዛሬው ትውልድ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል:: “ተማሪዎችን መመገብ ትውልድን መገንባት ነው” ያሉት ከንቲባው ሕዝቡ ለጅምሩ መስፋት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል:: ለዚህ ማረጋገጫቸው የምገባ ፕሮግራሙን ባስጀመሩበት ወቅት ከነዋሪዉ 10 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ነው::

በአጠቃላይ የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎች የትምህርት ተነሳሽነት እንዲጨምር፣ የማቋረጥ ምጣኔ እንዲቀንስ እና የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል እንዲሻሻል የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ሜድርክሲቭ (medrxiv.org) ድረ ገጽ ላይ የተጋራው ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል:: በረሀብ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች እንዲቀንሱ፣ የድብርት ስሜቶች ጠፍተው በንቃት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከማስቻሉም ባሻገር በወላጆች ከትምህርት እንዲቀሩ የሚደረገውን ጫና የመቋቋም አቅማቸው እንዲዳብርም ያደርጋል::

በትምህርት ቤቶች የሚተገበር የምገባ ፕሮግራም የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ እንዲቀንስ ማድረጉን ጥናቱ አረጋግጧል:: ጥናቱ እንዳብራራው በትምህርት ቤቶች የምገባ ሥርዓት ባልተጀመረበት ወቅት ቤተሰብ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ይሰማሩ ነበር። ይህም ለጉልበት ብዝበዛ እና ያልተገባ ቦታ እንዲውሉ በማድረግ የሱስ ተጋላጭነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን አንስቷል::

የምርት አቅርቦት ውስንነት፣ የምርቶች ዋጋ መጨመር፣ ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ ለምገባ ዓላማ ተብሎ የተገነባ መሠረተ ልማት አለመኖር የምገባ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ዋና ተግዳሮት ሊሆን ስለሚችል በጥናት ላይ የተመሠረተ የምግባ ፕሮግራም መጀመር ተገቢነቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል:: የምገባ ፕሮግራም መጀመር ታዲያ ከላይ የተነሱትን ችግሮች እንደሚያስቀር ነው ጥናቱ ያስገነዘበው::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here