የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ከሀገራችን ሕግ አንጻር ሲታይ የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ከሚያገኛቸው አያሌ የተፈጥሮ መብቶች ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል:: የሰው ልጆችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነትን ከሐይማኖት፣ ከባሕል እና ከሌሎች የተፈጥሮ ሕጎች አኳያ ስንመለከተው ፅኑ መሠረት ያለው ነው።
ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ሰው ለተለያዩ ዓላማዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይንቀሳቀሳል:: ይህ እንቅስቃሴው ለራሱ ለተፈጥሯዊ ሰውም ሆነ ለሌሎች ነፃነት ወይም ለሀገር ደኅንነት እና ጥቅም ሲባል የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል:: የዚህ የሰው ልጅ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ተፈጥሮአዊ ባህርይ እና ውስብስብ ፍላጎቶች፣ እንዲሁም እንቅስቃሴው ከድንበር አልፎ በሀገሮች መካከል ከሚፈጥረው ጫና የተነሳ የሚደረገው የሕግ ጥበቃ ከሀገሮች አልፎ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው አድርጎታል::
ይሁን እንጂ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተከሰቱ እጅግ አስከፊ የመብት ጥሰቶች መካከል አንዱ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት መገደቡ ነበር::
አንድ ችግር ሲፈጠር ለችግሩ መፍትሔ መስጠት ወይም መንገድ ማበጀት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪው እንደመሆኑ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተፈጠሩ የመብት ጥሰቶችን በማስመልከት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል:: ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከልም ዓለም አቀፍ የሰበዓዊ መብት ተቋማት መመሥረት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችን ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ:: በዚህም መሠረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲቋቋም በሰብዓዊ መብት ሰነድ ደረጃ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ እና ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት መካተታቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ::
የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13 ንኡስ ቁጥር አንድ ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት ዕውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል:: በተለይ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት በአንቀፅ 12 ላይ በመርህ ደረጃ ይህ መብት ገደቦች የሌሉበት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በሕግ በተደነገጉ ቅድመ ሁኔታዎች አማካኝነት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታዎች እንዳሉ ያሳያል::
እነዚህ ሁኔታዎች ከብሔራዊ ደኅንነት፣ ከሕዝብ ሞራል እና ከጤና ጋር የሚያያዙ ናቸው፤ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች መሠረት አድርጎ የሚወጣ ሕግ ከአድሎ ነፃ የሆነ እና የትኛውንም ሕዝብ በተለዬ የሚጎዳበት አግባብ ሊኖር እንደማይገባው ይደነግጋል::
በአጠቃላይ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ለሰው ልጅ ከተሰጡ መሠረታዊ መብቶች ውስጥ ቀዳሚው ነው:: በመሆኑም ማንኛውም ሀገር፣ በሀገር ውስጥ ያለ አስተዳደራዊ ክልል እንዲሁም ማንኛውም ተቋም እና ግለሰብ ይህንን መብት የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለበት::
የመዘዋወር ነፃነት ከሀገራችን የሕግ አንድምታ አንጻር የሀገራችንን ታሪክ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ከሕግ አልፎ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ነው። የሀገራችን ሕዝብ ባሕሉን አክባሪና እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ከሌሎች ሀገራት በተሻለ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ሲከበር ቆይቷል:: ይህ ታሪካዊ እና ማሕበረሰባዊ እውነታ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ነፍስ ዘርቶ እንዲሄድና ተፈፃሚ እንዲሆን የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ድንጋጌዎችን በማካተት እና የመዘዋወር ነፃነት የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረም የመጀመሪያውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ተችሏል::
በ1995 ዓ.ም በወጣው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከት ድንጋጌ አካቷል:: በሕገ መንግሠቱ አንቀፅ 32 ንኡስ ቁጥር አንድ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ሀገር ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው::
በዚህ አንቀፅ መሠረት አንድ ኢትዮጵያዊ በመረጠው በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር ነፃነት ሲኖረው ከዚህም በላይ ይህ ግለሰብ በተዘዋወርበት አካባቢ በተመቸው ቦታ ላይ መኖሪያውን መሥርቶ የመኖር ነፃነትም እንዳለው ይደነግጋል:: ከዚህ አንቀፅ ጋር በተያያዘ የሕገ መንግሥቱ ሌላው ድንጋጌ አንቀፅ 41 ንኡስ ቁጥር አንድ እንደሚገልፀው ማነኛውም ሰው በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው::
በመሆኑም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 32 እና 41 መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፈቃድ በመረጠው የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በመሄድ መኖሪያውን የመመሥረት እና በፈለገው ሙያ ላይ የመሰማራት መብት አለው::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም