በንግግር ሰላማችንን እናስፍን!

0
136

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ከወሰንና ከማንነት ጋር በተገናኘ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሚፈለገው ጊዜ አለመመለስ፣ ፍትሐዊ የመልማት እንዲሁም የልማት ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄዎች በሚፈለገው ልክ ምላሽ አለማግኘት  ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ግጭት እና ጦርነት ዳርገዋታል::

በአገራችን ያለው ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ ፉክክር እና የሥልጣን ሽኩቻም ከመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሁም ሀሰተኛ ትርክት ጋር ተደማምሮ የተከሰቱትን የእርስ በርስ ግጭቶች እያባባሰ፣ የልማት ውጥኖቻችንን እያደናቀፈ ይገኛል፤  ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴውን አዳክሟል፤ የዜጐችን ደኅንነትም አደጋ ላይ ጥሏል::

ይኽው ግጭት በተለይ በአማራ ክልል ከተከሰተበት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ አናጥቧል፤ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን አውድሟል፤ የዜጐችን የመንቀሳቀስ እና ሰርቶ የመብላት መብት ገድቧል፤ የአያሌ ንጹሃንን ህይወትም ቀጥፏል::

ይህ የሰላም እጦት ችግር እልባት ካልተበጀለት በስተቀር ከዚህ የከፋ ችግር ማስከተሉና አገራችንንም ወደ ባሰ ምስቅልቅል ውስጥ መክተቱ አይቀርም::

ስለሆነም ቆም ብሎ የችግሩን ምንጭ በጋራ መመርመርና በጋራ መፍትሄ መሻት ግድ ይላል::  በተለይም የችግሩ ዋነኛ ምንጭ እንዲሁም አባባሽ ምክንያት ሲነዛ የኖረው ሀሰተኛ ትርክት መሆኑን ተገንዝቦ ከዚህ ችግር የምንወጣበትንና በንግግር ሰላማችንን የምናሰፍንበትን መንገድ  መሻት ያስፈልጋል::

ወደ ግጭት ያስገቡንን ምክንያቶች በውል ለይቶ  መፍትሄ ለመሻት  ከምንም በላይ መቀራረብና ልባዊ ውይይት ማካሄድ ግድ ይላል:: ይህ ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ የመሻት ጉዳይ ለነገ የማይባል፣ ላንድ ወገን የማይተው አሳሳቢና የጋራ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብም ያሻል::

መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት  ከተለያዩ ወገኖች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ምክክር አድርጓል:: ይህ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም መፍትሄ በማስቀመጥ እና በቁርጠኝነት በማስፈፀም ረገድ ግን አሁንም ችግሩ በሚጠይቀው ልክ ለውጥ አልታየም:: በዚህ የተነሳም ዛሬም የአማራ ክልል ህዝብ በሰላም እጦት እየተቸገረ እና ለድህነት እየተዳረገ ይገኛል:: በዚህ ጉዳይ ላይ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘጋቢ ያነጋገራቸው ምሁራን እንደሚሉት አገራችን ከተከሰተባት የእርስ በርስ ግጭት ወጥታ ወደ ተሻለ ከፍታ እንድትሸጋገር፣ ህዝብ ሳይሞት፣ ሳይዘረፍ፣ ሳይፈናቀል እና የደህንነት ችግር ሳይሰማው በፈለገበት ቦታ ተንቀሳቅሶ በመሥራት የኢኮኖሚ ተጠቀሚነቱን እንዲያረጋግጥ፣ ሕዝባዊ መስተጋብሩ እንዲጠናከር፣ የልማት እንዲሁም የዕድገትና ሥልጣኔ ጉዟችን እንዲፋጠን ንግግር፣ ውይይት እና ድርድር ቀዳሚው የትግል ስልት ሊሆን ይገባል::

ግጭቶች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ አግኝተው ሕዝብ ያለ ስጋት የሚንቀሳቀስባትን ሀገር ለመገንባት  ሕዝቡ ታጣቂ ኃይሎች  ወደ ድርድር እንዲመጡ በሚያደርጉ ጉዳዩች ላይ ጫና መፍጠር ይጠበቅበታል::

መንግሥትም ሕዝብ የሚያነሳቸውን የፍትህ፣ የዴሞክራሲ እና የልማት፣ ጥያቄዎችን ለመፍታት በቁርጠኝነት መሥራትና የጀማመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ችግሩን ለመፍታት  የመሪነቱን ሚና መወጣት ከመንግሥት የሚጠበቅ ቢሆንም ያገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ፣ በመደማመጥ መሥራትና ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄ መሻት ይጠበቅባቸዋል::

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here