የበጋ መስኖ መዝራት ተጀመረ

0
143

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት አቅዶ እየሠራ መሆኑን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ከመኸር ሰብል ስብሰባው እና ጥበቃው ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ልማት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ነው የተመላከተው።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት፣ በምርት ዘመኑ በአዲስ እና በነባር 39 ሺህ 552 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 27 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማ ነው፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ያሉ የመስኖ ውኃ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም የበጋ መስኖ ስንዴን በስፋት ለማልማት የማሳ ዝግጅት እና የግብዓት አቅርቦት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 24 ሺህ 258 ሄክታር መሬት ማሳ ታርሷል። ስድስት ሺህ 500 ሄክታሩ ማሳ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል። በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታሰበው 27 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 11 ሺህ 871 ሄክታር የታረሰ ሲሆን ስድስት መቶ 35 ሄክታር በዘር መሸፈኑን ምክትል ኃላፊው ገልፀዋል።
ለመስኖ ልማቱ የወንዝ ጠለፋ፣ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን የመጠገን እና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል። ዕቅዱን ለማሳካትም የግብዓት እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለበጋ መስኖ ልማቱ ጥቅም የሚውል 84 ሺህ 514 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል። እስካሁንም ከሦስት ሺህ 400 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። አንድ ሺህ 250 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ ከ50 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።
አርሶ አደሩም በእጁ ያለውን ዘር በጥራት እንዲጠቀም እየተሠራ ነው ብለዋል። ሥስት መቶ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን ማሰራጨት ተችሏል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በምርት ዘመኑ 918 ሺህ ኩንታል ምርት በበጋ መስኖ ስንዴ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here