የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የአንድ መስኮት አገልግሎት በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናት እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፤ የተቋቋሙት የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ከሰሞኑ በነበረ ምክክር የተገኙ የማዕከላቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
ከቢሮው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሴቶች እና ህጻናት የሕክምና፣ የስነ ልቦና፣ የፍትሕ፣ የምግብና የመጠለያ አገልግሎት በተቀናጀ እና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በአንድ ቦታ የሚሰጥባቸው ማዕከላት ናቸው፡፡
በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራትን ጨምሮ በሴቶችና ህጻናት ላይ ጥቃቶችና ሌሎች የመብት ጥሰቶች ሲፈጸሙም ተጠቂዎች ተገቢውን የሕክምና እና የስነ ልቦና እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን እንዲያገኙ ጥቃት አድራሾችም ተገቢና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው /አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ/ ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት ይሠራሉ፡፡
በምክክሩ የተሳተፉት የተቋማቱ አስተባባሪዎች ማዕከላቱ የተቀናጀ እና ሁሉን አቀፍ እንዲሁም ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአብክመ ሴቶች ህፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ ስለ ምክክሩ እንደገለጹት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት ዋናው ተግባር ነው፤ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥበት የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አሁናዊ ሁኔታን በአግባቡ በመዳሰስ ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ምክክሩ መካሄዱን አንስተዋል፡፡
በምክክሩ የጥምረቱ አባል ተቋማት ትኩረት እና ቅንጅት በሚፈለገው ልክ አለመሆን፣ ሳምንቱን ሙሉ የ24 ሰዓት አገልግሎት አለመስጠት፣ የምግብ አቅርቦት እና ማሕበረሰቡ ስለ ማዕከላቱ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን አበይት ችግሮች እንደሆኑ ተነስቷል፡፡
የተሟላ እና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት በክልሉ ያሉ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ኃላፊዎች ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር እና በማስተባበር በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያሉ ችግሮችን ፈጥነው መፍታት እንዳለባቸው ነው የተመላከተው፡፡
በምክክሩ የፍትሕ፣ የጤና፣ የፍርድ ቤት፣ የፖሊስ ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተገኝተዋል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም