የዲሞክራሲ እናት

0
147

ከተንጣለለው አትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ በአሳሾች ጠቋሚነት አስቀድመው ግዛት መስርተው የነበሩትን የስፔን ቅኝ ገዥዎች እግር ተከትለው ወደ አዲሱ ምድር ያቀኑት እንግሊዛውያን 13 ቅኝ ግዛቶችን ገንብተው ቀስ በቀስ  እግራቸውን ሰድደው ለዘመናት ቆይተዋል።

እነዚህ ግዛቶች በእንግሊዝ አስተዳደር ስር ሆነው ከፍተኛ የራስገዝነት ስልጣን ነበራቸው። ለእያንዳንዱ ግዛት እንግሊዝ የምትመርጥላቸው መሪ ያስተዳድራቸዋል። የእንግሊዝ ፓርላማ በሚያወጣላቸው ሕግ የግድ ይገዛሉ። ነገር ግን በራሳቸው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ያሉበት የየራሳቸው ምክር ቤቶች ነበሯቸው። የግብር አከፋፈሉ በአውሮፓ መለኪያ ስለነበር ብዙም ጉዳት አይሰማቸውም።  ይህ በመሆኑ ምክንያትም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ችግር አልነበረባቸውም። ሆኖም ከነፃነት ትግሉ በፊት ለየብቻቸው ይንቀሳቀሱ ነበር። ርስ በርስም ፉክክር እና መቀናናት ይስተዋልባቸው ነበር።

የአሜሪካዊነት ስሜት በሁሉም ቅኝ ግዛቶች ዘንድ መታየት የጀመረው ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲሆን ከነፃነት ትግሉ በፊት ግን እንዲህ አይነቱ ስሜት እምብዛም ነበር። ነገር ግን የእንግሊዝ መንግሥት የቅኝ ግዛቶቹን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር ያወጣው አዲስ መርሃ ግብር ከቅኝ ግዛቶቹ ጋር እያላተሙ መጣ። ከእንግሊዝ ግዛት ነፃ በመሆን ራሷን የቻለች ሀገር የመመስረት ፍላጎት ማቀንቀን መጀመሩን አንዲሁም የአሜሪካ አብዮት ዳዴ ማለት መጀመሩን በሁለተኛው ክፍል ጀምረን ነበር ያቆምነው፤ የመጨረሻውን ክፍልም እነሆ።

እንደ ጀምስ ኦቲስ፣ ፓትሪክ ሔንሪ እና ሳሙኤል አዳምስ አይነት አርበኛ መሪዎች የሚያደርጓቸው ንግግሮች እና ተግባራት በእንግሊዝ ላይ የሕዝቡን ቁጣ ማነሳሳት ቻሉ። አንዳንድ አመፆች እንዲሁም የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴዎች መታየትም ጀመሩ። ይህ በእንዲህ እያለ ቶማስ ፓይን የተባለ አንድ አሜሪካዊ አብዮተኛ እና አርበኛ ያዘጋጀው፣ “ኮመን ሴንስ፣ ዘ ራይት ኦፍ ሜን ኤንድ ዘ ኤጅ ኦፍ ሪዝን” የተሰኘ ባለ 50 ገፅ በራሪ ወረቀት የነፃነት ትግሉን ወደ ሌላ ምእራፍ ወሰደው። ከ100 ሺህ በላይ ቅጅዎች በሶስት ወራት ውስጥ በየግዛቶቹ ተሰራጭቶ አለቀ። በራሪ ወረቀቱ በዘር ሀረግ የሚተላለፍን የንጉሣዊ ስርዓት እሳቤን ጎንጦታል። አንድ ትንሽዬ ደሴት ለምን አንድ ትልቅ አህጉርን ትገዛለች? አይነት ጥያቄ በሰዎች ሀሳብ ውስጥ ጭሯል። ቶማስ ፓይን ለሕዝቡ ምርጫ አቅርቧል፤ “…ለአምባገነኑ እና ላረጀ ያፈጀ ለእንግሊዝ ንጉሥ መገዛትን መቀጠል ወይስ ራሱ ለራሱ በቂ በሆነ ነፃ ሀገር ላይ ነፃነት እና ደስታን መጎናፀፍ…” ይህ አስተሳሰብ በሁሉም ቅኝ ግዛቶች ዘንድ ተስፋፋ እና በሕዝቡ ዘንድ ከእንግሊዝ የመነጠል ውሳኔን አጠነከረው።

ሆኖም አሁንም አንድ የቅኝ ግዛቶች የጋራ ቅቡልነት ያለው መደበኛ አዋጅ የማግኘት ሥራ ይቀር ነበር። ግንቦት 27 ቀን 1768 ዓ.ም ላይ የቨርጂኒያ ተወካይ የነበረው ሪቻርድ ሔንሪ ሊ በሁለተኛው ኮንቲኔንታል ኮንግረስ ላይ “እነዚህ የተባበሩት ቅኝ ግዛቶች  ነፃ እና ራሳቸውን የቻሉ ሀገር ናቸው” የሚል ሀሳብ በማስተጋባት ለኮንግረሱ አቀረበ። ወዲያውኑ አምስት አባላት ያሉት በቶማስ ጃፈርሰን የሚመራ ኮሚቴ የነፃነት አዋጅ የተሰኘውን ሰነድ እንዲያዘጋጅ እና ለድምፅ እንዲያቀርብ ሀላፊነት ተሰጠው።

የቶማስ ጃፈርሰን አስተዋፅኦ የጎላ የሆነበት የነፃነት አዋጅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ካለቀ በኋላ ሰኔ 27 ቀን 1768 ዓ.ም ላይ ለኮንግረሱ ቀርቦ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ። ሰነዱ የአንድን አዲስ ሀገር  መመስረት ያበሰረ ብቻ ሳይሆን፤ በመላው ዓለም አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን የሰው ልጅ የነፃነት ፍልስፍናን ወደፊት ያስቀደመ ታላቅ ሰነድ ነበር።

ቶማስ ጃፈርሰን አዋጁን ሲያስተዋውቅ እንዳሳወቀው መንግሥታት ሕዝብን ለማገልገል እንደሚመሰርቱ እና ተግባራቸውም በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አውጇል። ቶማስ ጃፈርሰን በማከልም ዲሞክራሲያዊ መንግሥታት የሚመሰረቱባቸውን መሰረታዊ መርሆዎች ዘርዝሯል። “ሁሉም የሰው ልጆች እኩል ተፈጥረዋል፣ ስለዚህ ማንም ሊቀማቸው የማይችል መብቶች በፈጣሪያቸው ተሰጥቷቸዋል። እነዚህም መብቶች የሕይወት፣ የነፃነት፣ እና ደስታን የመሻት መብቶችን ያካትታሉ” ብሎ ነበር። እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ ታዲያ መንግሥታት ከሚገዙት ሕዝብ ፈቃድ ትክክለኛ ስልጣኖቻቸውን በመቅዳት ከሰዎች መካከል ይቋቋማሉ፤ እነዚህን መብቶች የሚያበላሽ ወይም የሚጥስ መንግሥት ከሆነ ደግሞ መንግሥቱን የመለወጥ ወይም የማስወገድ እና አዲስ የማቋቋም መብቱ የሕዝቡ መሆኑን ያስገነዝባል። ታላቋ ብሪታኒያ ግን ይህን አዋጅ በፍፁም አልተቀበለችም። ይልቁንም የቅኝ ግዛቶቿን አመፅ በሀይል ለማስወገድ ወደ ወታደራዊ እርምጃ ተንቀሳቀሰች። የነፃነት አርበኞቹም ጠቅልለው ወደ መራር የነፃነት ትግል ውስጥ ገቡ። ቅኝ ግዛቶች ያደራጁት የነፃነት አርበኞችን ኃይል ይመራ ዘንድ ኮሎኔል ጆርጅ ዋሽንግተን ዋና አዛዥ በመሆን ተሹሟል። ቆራጥ ተጋድሎ ውስጥ የገቡት አርበኞቹ ትግላቸውን የሚያኮላሽ ተግዳሮቶችን በአመራር ብቃት ተቋቁመው ባይጋፈጡ ኖሮ ድል አይታሰብም ነበር። አርበኞቹ የእንግሊዝን ጦር ብቻ አልነበረም የገጠሙት፣ በሀገሬው ባንዳዎች ከሚቃጡባቸው ጥቃቶች ጋር ጭምር እንጂ። በዚህ ላይ የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ እና የምግብ አቅርቦት እጥረት ፈትኗቸው ነበር። ነገር ግን ከእነዚህ ተግዳሮቶች በላይ የነበረው የጆርጅ ዋሽንግተን ቁርጠኝነት እና ብልህነት የተሞላ  የአመራር ማብቃት እና ፅኑ መንፈስ የመኮንኖቹን እና የወታደሮቹን የተዳከመ ተስፋ ዳግም ነፍስ ዘርቶበት ወደ ድል ይዟቸው ገሰገሰ።

የውጭ ሀገራት ድጋፍ በሌላ በኩል የነፃነት ትግሉን የመደገፍ ፍላጎት ማሳየታቸው የትግሉን ጉልበት አበረታታው። በተለይ ፈረንሳይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክታለች። ፈረንሳይ የዘመናት ባላንጣዋን የእንግሊዝን አንገት ለማስደፋት ይህ አጋጣሚ መልካም እድል ሆኖ ስለተሰማት አርበኞችን መደገፍ ያዘች። የአጋርነት ስምምነት በመፈረምም ከአሜሪካውያኑ ጎን ቆመች። ወጣቷን አሜሪካ በማገዝ ፈረንሳይ የተቀናቃኟን የታላቋን እንግሊዝ ጉልበት መስበር አልማ ተንቀሳቀሰች። በመሆኑም ለአሜሪካውያኑ አርበኞች የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ፣ የወታደሮች እና የምግብ ድጋፍ አደረገች። የፈረንሳይን እግር ተከትለውም ስፔን እና ሆላንድ የራሳቸውን ድጋፍ አበረከቱ። ከዚህም የተነሳ አብዮታዊ ትግሉ የነፃነት ትግል ከመሆን በበለጠ የዓለም ጦርነት እስከመባል ደርሷል።

ኮሎኔል ጆርጅ ዋሽንግተን በላቀ ወታደራዊ የአመራር ብቃት ሰራዊቱን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ  በአግባቡ እያበረታ በማስተባበር መርቶ የእንግሊዝን ጦር አንበርክኳል። ለዓመታት የተደረገው ጦርነት በመጨረሻ በአሜሪካውያኑ የነፃነት አርበኞች አሸናፊነት በ1773 ዓ.ም ላይ በድል ተደመደመ።

ነፃነታቸውን ከእንግሊዝ እጅ ማግኘት ብቻውን ለአዲሷ ሀገር ለአሜሪካ ሁሉም ችግሮቿ መፍትሄ አልሆነም። አሜሪካውያኑ ለበርካታ ዓመታት በከሰረ ንግድ እና በኢኮኖሚ ድቀት አሳራቸውን ሲያዩ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያትም ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት አለመኖሩ ነበር። ታዲያ ይህን እና ሌሎች የአሜሪካን ችግሮች የሚቀርፈው ጠንካራ ዲሞክራሲታዊ መንግሥት በመመሥረት መሆኑ የአሜሪካ መስራች አባቶች ፅኑ እምነት ነበር። እናም ከትግሉ በፊት በነፃነት አዋጁ ላይ በተቀመጡት መሰረታዊ መርሆዎች ላይ የቆመ በሕዝብ፣ ከሕዝብ፣ ለሕዝብ የሆነ መንግሥት ለማቋቋም ጉዙው ቀጠለ።

በ1779 ዓ.ም በፊላደልፊያ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች በአንዳች ወሳኝ ስብሰባ ላይ ተገናኝተው ነበር። የወደፊቷን አሜሪካን እጣ ፋንታ የሚወስኑ  አሜሪካውያንን የወከሉ እነዚህ ሰዎች ለሳምንታት በመወያየት፣ በመከራከር በመጨረሻም በመግባባት ወሳኙን ስብሰባ ቋጩ። ውጤቱ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ነበር፤ አሜሪካ እስከዛሬ የምትተዳደርበትን የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገመንግሥት ተደነገገ። በሕገ መንግሥቱ  ጥላ ስር የአዲሧ ሀገረ መንግሥት የአሜሪካ ጠንካራ ፌዴራላዊ መንግሥት ተመሰረተ። ጆርጅ ዋሽንግተን የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚደንት በማድረግ  በመሆን ተሰየሙ።

በዓለማችን አዲስ ዲሞክራሲያዊት ሀገር እውን ሆነች። ዛሬ የምድራችን ኃያል ሀገር የሆነችው ታላቋ አሜሪካ በአንፃራዊነት የዲሞክራሲ እድገት ማሳያ በመሆን ዘመናዊ የመንግሥት ስርዓት የገነባች ሆናለች። የዜጎቿን ጥቅም፣ መብት፣ ነፃነት እና እኩልነትን ለማረጋገጥ  አባቶቻቸው በጣሉት ጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተች ታላቅ፣ ሁሉ የሚቀናባት ሀገር እስክትሆን በሚገባ ታንፃለች።

ከዓለም ሁሉም አቅጣጫ የመጡ የተለያየ ዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ ባህል እና ቋንቋ ያላቸው ሕዝቦች በአንድነት፣ በነፃነት እና በእኩልነት የሚኖሩባት ምቹ ምድር እንድትሆን ቀደምት የአሜሪካ አባቶቻቸው የከፈሉት ውድ መስዋእትነት ትልቅ ነበር። የእነርሱ ፅናት እነሆ ዛሬ ያለችውን ዘመናዊት፣ ብልፁግ እና ዲሞክራሲያዊት ሀገር ለልጅ ልጆቻቸው አውርሷል። እኛም የማይናጋ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት በመገንባት ዜጎቿ የሚኮሩባት፣ የሚሰውላት ድንቅ ሀገር ሆና ተሰርታ ለዛሬ ክብር የበቃ የዓለም ሀያሏን የአሜሪካን ታሪክ በዚሁ ቋጨን።

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here