ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ በቀጠለው በትጥቅ የታገዘ ግጭት የአማራ ክልል የትምህርት እንቅስቃሴ ክፉኛ ተጎድቷል:: በሰሜኑ ጦርነት ጫና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ እና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ዝቅተኛ መሆንን ተከትሎ “ለምን?” በሚል ተፈጥሮ የነበረውን ቁጭት ዛሬ ለምን መድገም አቃተን?
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ አሁንም ድረስ የቀጠለው ግጭት በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ትናንት ካጋጠመው ቢገዝፍ እንጂ ያነሰ ሊሆን አይችልም:: ለዚህ ማሳያው ደግሞ ባለፈው ዓመት ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው ከርመዋል:: ይባስ ብሎ ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሰኔ ላይ እንደተዘጉ ሳይከፈቱ ዓመቱን ስለመሻገራቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል::
ችግሩ ወደ 2017 ዓ.ም ተሸጋግሮ የአንደኛው ወሰነ ትምህርት ሊጠናቀቅ ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ በቀረበት ነባራዊ ሁኔታ በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ከታቀደው ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ማሳካት የተቻለው ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ ነው:: አሁንም ድረስ የቀጠለው የጸጥታ መደፍረስ ክልሉ በትምህርት ዘርፍ የነበረውን ውክልና እንዳያሳጣው አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች መማር ማስተማርን ከማስቀጠል ጎን ለጎን የትምህርት ግብዓትን በበቂ ሁኔታ ማሟላት ተገቢ ነው::
ባለፈው ዓመት አንድም ተማሪ አስተምሮ ለፈተና ካላደረሱ አካባቢዎች መካከል አንዱ የምዕራብ ጎጃም ዞን ነው:: ባለፈው ዓመት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት በ2017 ዓ.ም ዳግም በማስጀመር ለማስቀጠል እንደ ዞን 396 ሺህ 547 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ አስቀምጧል:: የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መኩሪያው ገረመው ለበኵር በስልክ እንደነገሩን እንደ ክልል ትምህርት በተጀመረበት ወቅት ዞኑ አንጻራዊ ሰላም በነበረባቸው ስድስት ወረዳዎች 17 ሺህ 235 ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደ መማር ማስተማር ገብቷል::
የዞኑ የጸጥታ ችግር ከመስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ማገርሸቱን ተከትሎ የመማር ማስተማር ሥራው ለአንድ ወር ተቋርጦ መቆየቱ፣ ከወርሀ ሕዳር ጀምሮ ደግሞ እንደ ገና መጀመሩን አቶ መኩሪያው ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥርም 8 ሺህ 500 ብቻ ናቸው:: ይህም በወርሀ መስከረም ተመዝግበው በትምህርት ላይ ይገኙ ከነበሩት ውስጥ 8 ሺህ 735 ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት ቤቶች አልተመለሱም ማለት ነው:: አሁን በትምህርት ላይ የሚገኙት ከዞኑ ዕቅድ አኳያ ሲመዘን በ388 ሺህ 47 ተማሪዎች ዝቅ ያለ ነው:: እንደ ምክትል መምሪያ ኃላፊው በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ወረዳዎች ስድስቱ ከመማር ማስተማር ሥራ ውጪ ሆነው ዘልቀዋል:: ቡሬ፣ ፍኖተ ሰላም እና ደምበጫ ከተሞች ደግሞ ትምህርት የተጀመረባቸው አካባቢዎች ናቸው::
በአጠቃላይ ግጭቱ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ፣ የትምህርት ተቋማት ነገ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን እንዳያፈሩ ዝርፊያ እና ጉዳት እንደደረሰባቸው ምክትል መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል:: በዞኑ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በአብዛኛው ከደረጃ በታች በመሆናቸው ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት በግጭቱ ከመቶ በላይ ትምህርት ተቋማት ለጉዳት መዳረጋቸው ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ሊያደርገው እንደሚችልም አቶ መኩሪያው ስጋታቸውን ገልጸዋል::
ትምህርት በተጀመረባቸው አካባቢዎች ትምህርቱ በተሳካ ሁኔታ ሊቀጥል ይገባል የሚሉት አቶ መኩሪያ፤ ለዚህም ግብዓት ለማሟላት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: የመማር ማስተማር ሥራውን በቀዳሚነት ከሚደግፉ ግብዓቶች መካከል ዋናው በተማሪዎች፣ በወላጆች እና በመምህራን ዘንድ በስፋት የሚጠየቀውን መጻሕፍት ለማሟላት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አቶ መኩሪያዉ ጠቁመዋል:: እስከ ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚውል 490 ሺህ 598 መጻሕፍት ወደ ዞኑ መግባቱን፣ ይህም በአጠቃላይ መጓጓዝ ከነበረበት ከ75 በመቶ በላይ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል:: ከዚህ ውስጥ 143 ሺህ 974 መጻሕፍት አንጻራዊ ሰላም ወደሰፈነባቸው ወረዳዎች መሠራጨቱን አረጋግጠዋል::
ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚያገለግሉ መጻሕፍትም ለዞኑ ደርሰዋል:: በአጠቃላይ ወደ ዞኑ መግባት ከነበረበት 270 ሺህ 634 መጻሕፍት ውስጥ እስካሁን 203 ሺህ 728ቱ መድረሱም ተመላክቷል:: 155 ሺህ 474 የሚሆነው ወደ ወረዳዎች ማሰራጨት መቻሉን ጠቁመዋል::
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተማሪ መጻሕፍት እና ሌሎች መማር ማስተማሩን ሊያግዙ የሚችሉ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ከማድረግ ጎን ለጎን ከ188 ሺህ በላይ ደብተር ድጋፍ ማድረጉን አቶ መኩሪያው አስታውሰዋል::
“ትምህርት ማኅበራዊ ተቋም ነው” ያሉት አቶ መኩሪያው፤ በመሆኑም የትኛውንም ፖለቲካ፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ጎሳ… ሳይለይ በአንድ የሚያስተሳስረውን ትምህርት ሁሉም ያለምንም ጫና እንዲያገኝ ሁሉም አካል ጥብቅ ከለላ እና ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል:: ሕዝቡም ትምህርት በተጀመረባቸው አካባቢዎች ዳግም የትምህርት መስተጓጎል እንዳይፈጠር የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዘብ ሆኖ እንዲሠራ ጠይቀዋል::
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የክልሉ ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም መዝግቤ አስተምራለሁ ያለው የሰባት ሚሊዮን ተማሪ ቁጥር እንዳያሳካ ማድረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቱ አስታውቀዋል:: እስካሁን ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ያልበለጠ ተማሪ በትምህርት ላይ እንደሚገኝ ለግጭቱ ተጽእኖ ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: አሁንም የተማሪ ምዝገባ እንደሚቀጥል የገለጹት ወይዘሮ እየሩስ ጎን ለጎን መማር ማስተማሩን ሊያግዝ የሚችል ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል::
እንደ ምክትል ኃላፊዋ ገለጻ የመጻሕፍት አቅርቦትን ለማሟላት በሁለት መንገድ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው:: የመጀመሪያው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው ያሉት ባለፈው ዓመት ታትመው በጸጥታ ችግር ሳይሰራጩ በክዘና ማዕከላት የቆዩ መጻሕፍትን ማሰራጨት ነው:: በዚህም ባለፈው ዓመት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን መጻሕፍት ከትምህርት ሚኒስቴር ለክልሉ መድረሱን አስታውቀዋል:: ከዚህ ውስጥ አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮኑ ባለፈው ዓመት መሰራጨቱን አስታውሰዋል:: ቀሪውም በአሁኑ ወቅት እየተሠራጨ ነው::
በክልል ደረጃ ከቅደመ መደበኛ እስከ አንደኛ ደረጃ ያሉ መጻሕፍት ሕትመታቸው በክልል ደረጃ እንደሚከናወን ወይዘሮ እየሩስ አስታውቀዋል:: ባለፉት ዓመታት ሕትመታቸው የተጠናቀቀ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን መጻሕፍት እንደነበሩ አስታውሰው:: ከዚህ ውስጥ 12 ነጥብ 1 የሚሆነው 2017 ዓ.ም ከመግባቱ በፊት መሰራጨቱን ጠቁመዋል:: ቀሪው አሁንም ወደየዞኖቹ በመሠራጨት ላይ ነው::
ሁለተኛው የመጽሐፍት ስርጭት ደግሞ ሕትመታቸው በዚህ ዓመት የተጠናቀቁ ናቸው:: በዚህም ሕትመቱ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሆነው እና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚውል ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን መጻሕፍት መመደቡን ወይዘሮ እየሩስ ነግረውናል:: ከዚህም ውስጥ ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ወደ ክልሉ መግባቱን እና አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮኑ ገብቶ ወደየዞኖቹ በመሰራጨት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል::
ለአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የሚውሉ መጻሐፍት ሕትመት እና ስርጭት ጎን ለጎን እየተከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል:: በአሁኑ ወቅት አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን መጻሕፍት በስርጭት ላይ መሆኑ ተመላክቷል:: ከዚህ ውስጥ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን መጽሓፍት ሕትመቱ ተጠናቆ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ምክትል ኃላፊዋ ገልጸዋል:: መጽሓፍቱ ለተማሪዎች መድረሳቸውን ለማረጋግጥ ጠንካራ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ይገኛልም ተብሏል::
የክልሉ ትምህርት በርካታ ፈተናዎች ያሉበት ነው ያሉት ወይዘሮ እየሩስ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሙ የመጡ የጸጥታ ችግሮች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ደግሞ ተጨማሪ ፈተና ሆነው ብቅ ማለታቸውን ጠቁመዋል:: በመሆኑም ክልሉ ይታወቅበት ወደነበረው የትምህርት እንቅስቃሴ እንዲመለስ በትብብር መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::
ለ2017 የትምህርት ዓመት ራሱን የቻለ የጊዜ መቁጠሪያ/ካላንደር/ መዘጋጀቱን ወይዘሮ እየሩስ አስታውቀዋል:: ይህም ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታውን መሠረት ያደረገ የተማሪ ምዝገባ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው:: ክልላዊም ሆነ ሀገር አቀፍ ፈተናውም በትምህርት አጀማመሩ መሠረት የሚፈጸም በመሆኑ ተማሪዎች በማንኛውም ጊዜ ትምህርት ሲጀመር ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ ወላጆችም ጊዜው አልቋል ሳይሉ ትምህርት ቤቶች እንደተከፈቱ ልጆቻቸውን እንዲልኩ መልዕክት አስተላልፈዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም