“ወደዚች ዓለም የመጣኸዉ ለመስጠት ነው፤ በመጀመሪያ ግን ተቀብለሀል”

0
132

ቤቱ የኖህ መርከብ በሚል ቅጽል ወጥቶለታል:: የቸገረውም ሆነ የፈለገ እየበላ እየጠጣ የምኖርበት ስለሆነ::“የሚያስፈልግህን ብቻ ውሰድ፤ አታትርፍ፤ አንተም አትትረፍ (ከአቅም በላይ አትሁን)” የሚል ፍልስፍናም አለው:: “የሚተርፍ ይጣላል እና” ይላል:: ተግባቢ እና ጨዋታ አዋቂ መሆኑም ይመሰከርለታል::ባልተስማማበት እና ልክ ባልሆነ ነገር ላይ ፊት ለፊት ሀሳቡን ከመግለጽ ወደ ኋላ  አይልም:: በዚህም ሞገደኛ ነው ይሉታል፤ ከአርቲስት ስዩም ተፈራ ጋር የነበረን የመጨረሻ ክፍል ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል:: መልካም ንባብ!

ስዩም ተፈራ ሞገደኛ ነው?

አዎ ሞገደኛ ነኝ:: ሞገደኛነቴ የመጣው ከቤተሰቦቼ ነው:: ቤተሰቦቼ ሲበዛ ነጻ አድርገው ነው ያሳደጉኝ:: ሞገደኛነቴ ከድሮው አቅም ያንሰዋል እንጂ አሁንም አለ:: በእርግጥ ከህሊና ጋር ነው እንጂ አካላዊ ሞገደኝነት የለብኝም:: ላመንኩበት ነገር ግትር የመሆን እንጂ የመደባደብ አጋጣሚም ታሪክም የለኝም:: ሞገደኛነቴ ከመዘጋጃ አስወጥቶ ወደ ራስ ቲያትር አስገብቶኛል:: አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ያበሽቁኛል:: ሙሉ ነገር ለሰው አትስጡ ብየ ልመክር ነው:: ለሰው ሙሉ ነገር ስትሰጠው ሌላ ተጨማሪ አለው ብሎ ይጠብቅብሀል:: ከዚያ ይሄ ሙሉ ነው ብሎ መቀበል ይከብደዋል::

እኔ የታዘዝኩትን ለማድረግ ችግር የለብኝም ፈቃደኛ ነኝ::ከመታዘዝ ውጪ አንድን ሰው እንድትፈራው እና እንድታጎበድድለት ሲፈልግ ያኔ ችግር ይፈጠራል::ያኔ አምጻለሁ::ከመዘጋጃ አስወጥቶ ራስ ቲያትር ያስገባኝም ይህ ቀጥተኛ ባሕሪዬ ነው::

የቅርብ ቤተሰቦችህ ወንድም ጌታ እያሉ ይጠሩሃል፤ ይህ ስያሜ እንዴት መጣ?

ወንድም ጌታ ማለት ማዕረግ ነው:: ልጆች ሆነን እናታችንን በሰሙ እያልን ነበር የምንጠራት፤ የሆነ ጊዜ ላይ አንዲት መነኩሴ ቤታችን መጥተው ይሰሙናል:: “እንዲህ ያለ ስርዓት የለም፤ እናታችሁን እትዬ ወይም ሌላ ማዕረግ ሰጥታችሁ ጥሩ” ብለው ተቆጡን:: ከዚህ ተነስተን እናታችንን እትዬ፣ ታላቅ እህታችንን እቴቴ ብለን መጥራት ጀመርን፤ ለእኔ ደግሞ ወንድም ጌታ የሚል ስም ተሰጠኝ:: ወንድም እህቶቼ ሲጠሩኝ የሰማ  በሙሉ ወንድም ጌታ ነው የሚለኝ:: ጎረቤቶቼ ሁሉ ወንድም ጌታ ነው የሚሉኝ (ሳቅ):: ዋናውን ስሜን የሚያስታውሱት አይመስለኝም::

የስጋ ወንድሜ ማንያዘዋል እንደሻው አስተምሬ ያሳደኩት ልጅ ነው:: ያደገውም ወንድም ጌታ እያለኝ ነው:: በኋላ ላይ እሱ አስተማሪዬ ሆነ:: አንድ ቀን “ስዩም” ብሎ ጠርቶኝ ደንግጬ መመለስ አቃተኝ::  ምንድን ነው የጎደለው? ብየ ሳሰላስል ወንድም ጌታ ብሎ አልጠራኝም፤ ስዩም ነው ያለኝ፤ ከእሱ ወንድም ጌታ የሚለውን ነው እየሰማሁ የኖርኩት:: እኔ ተማሪ፣ እሱ አስተማሪ ነበርን:: ያስተማርኩት ልጄ መልሶ አስተምሮኛል፤ ይህ እድለኝነቴ ነው::

ስዩም ቤቱን አይቆልፍም ይባላል፤ ለምንድን ነው?

ከቤተሰቦቼ የመጣ ነገር ነው፤ የሴት አያቴ ቤት አይቆለፍም ነበር:: እማሆይ አዛለች ማስረሻ ይባላሉ፤ “ልጆቼ ርቧቸው መጥተው አያታቸው ስለሌለች እንዳይቸገሩ” በሚል ሁሌም ቤቱ ክፍት ነው:: በተለይ እሳቸው ናቸው ደግነቱንም፣ መቻልንም፣ መስጠትንም ያስተማሩኝ::

ነገሮችን በጥበብ እንዴት ማየት እንዳለብኝ እና ነጻነትን ከእናቴ ወስጃለሁ:: ስለዚህ ልጅ ስታሳድግ ተጠንቀቅ፤ ወደዚች ዓለም የመጣኸው ለመስጠት ነው:: በመጀመሪያ ግን ተቀብለሀል::  አቅም ባልነበረህ በልጅነት ዘመንህ ተቀብለሀል:: አቅም ባለህ ጊዜ አለመስጠት ልክ አይደለም:: በሁለት እድሜህ ተቀባይ መሆን የለብህም:: ደግሞም የማትችልበት ጊዜ ይመጣል::

ስለዚህ ሁለተኛውን የማትችልበት ጊዜ የምታልፈው በምትችልበት ጊዜ በሰጠኸው ነው:: የሰጠኋቸውን ነገሮች አሁን እየተቀበልኩ ነው ብየ አስባለሁ:: ግን ከሰጠሁት በላይ ኖሮኝ ብሰጥ እንዴት ቆንጆ ነበር::

አባት ተወደደም ተጠላም፣ ይማር አይማር የደረስክበት ቦታ የአባትህ እውቀት ነው::እሱ ያሳወቀህ ነው:: አባት ልጁን አሽኮኮ የሚለው ልጁ ከእሱ በላይ እንዲያይ ነው:: ያ ማለት አባትህ ትከሻ ላይ ነው ያለኸው:: ማንም ሰው ትከሻውን ለሚያድጉ ሰዎች መፍቀድ አለበት::እሱ ላይ እንዲያድጉ፣ ከእሱ በላይ እንዲያዩ መፍቀድ አለበት::

ከአምስት ልጆችህ መካከል ሐሙስ የሚባል ልጅ አለህ:: ስሙ እንዴት ወጣ?

ሐሙስ የሚል ቲያትር ጽፌ ሐሙስ ዕለት ብሔራዊ ቲያትር  አሟላ የተባልኩትን ሁሉ ጨርሼ ሰጠኋቸው:: “እንኳን ለእኛም ደረስክልን” ብለው ደስ አላቸው:: በብሔራዊ ቲያትር ሊታይልኝ ነው ብየ ደስ ብሎኝ እያለ “ልጅ ተወልዶልሀል” ብለው ደውለው ነገሩኝ:: ሐሙስ በሉት አልኳቸው:: የሐሙስ ቲያትሬ ለመታየት ዝግጁ መሆኑ አስደስቶኝ እያለ ልጁ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ ደስታ ሆነልኝ:: ለዚያ ነው ልጄን ሐሙስ ያልኩት::

ጋሽ ስዩም ኳስ ጨዋታ ማየት ይወዳል?

ድሮ እንዳውም ከማየት መጫወት እወድ ነበር:: በኋላ ደጋፊ መሆን ጀመርኩ:: አሁን አሁን ደጋፊ ሳልሆን ተመልካች ነኝ:: ደጋፊ (ቲፎዞ) መሆን መታወር እንደሆነ ገባኝ:: በዚህ ምክንያት ተመልካች እንጂ ደጋፊ አይደለሁም::

አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ከሞሮኮ እየተጫወቱ ነው:: አንዱ ሞሮኳዊ ተጫዋች በሚገርም ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ግብ አስቆጠረ:: በጣም ደስ የምትል ግብ ነበር የተቆጠረችው:: እንዴ! ብየ በአግራሞት ጮሁኩ:: ተመልካቹ ሁሉ ዞሮ በንዴት አየኝ (ሳቅ):: ምነው  ጥሩ ጎል አይደለም እንዴ? ነው ያልኳቸው ሀገሬ እየተጫወተች መሆኑን ረስቼዋለሁ:: እኔ በአደኩበት አካባቢ ተቃራኒ ባለጋራም ቢሆን ጥሩ ነገር ካለ እናደንቃለን::

በግጥም ሥራዎችህ በብዙ ትደነቃለህ፤ ነገር ግን ብዙ ያልታተሙ ሥራዎች አሉህ፤ ልምን ይሆን?

ችግር ነው! በጉርምስናህ ወራት የምትወደውን በጉልምስናህ ጊዜ ብዙም ላትፈልገው ትችላለህ:: በጉልምስናህ ጊዜ ምትሻውን በሽምግልናህ ወቅት አትፈልገውም:: አትወደውም ማለት ግን ፈጽሞ ትጠላዋለህ ሳይሆን ሙሉ ጊዜህን አትሰጠውም፤ ለእሱ አይደለም የምትኖረው ማለት ነው:: ሌላ ነገር ትወዳለህ፤ ሌላ ነገር ታደንቃለህ፤ ዓላማየ ብለህ የትይዘው ነገር ይኖራል፤ እንደየ እድሜህ ትኖራለህ:: አሁን ላይ የምጽፋቸው ግጥሞቼ ሕይወት እንደዚህ ነው፤ እንደዚህስ አይተነዋል? የሚሉ ናቸው እንጂ በግጥም ሰውን ላስደንቅ አልፈልግም:: በጉርምስናየ እንደዛ ነበር የሚያስደስተኝ፤ በግጥም ሰውን ማስደመም:: ስለዚህ ብዙም ለማሳተም ተነሳሽ አይደለሁም::

ስለ መጽሐፎችህ ንገረን?

አራት ያሳተምኳቸው መጻሕፍት አሉኝ::“አንዱ አብሬህ አለሁ” የሚል መንፈሳዊ መጽሐፍ ነው:: ብዙ ሰው ቢያነብልኝ እወዳለሁ:: ምክንያቱም ሞገደኛው ስዩም በሌላ ገጽታ ደግሞ እዛኛው ላይ ስላለ ይሄኛውም መልኬ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ::

ፍልስፍናውስ እንዴት ነው?

እይታዎቼ ይለያሉ መሰል፤ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ከጀርባየ ላይ አልቅሷል:: እሱ እንዳውም የሚለኝ ፈላስፋ አይደለም:: የሚለው ምንድን ነው ስዩም የምታይባቸው መስመሮች ከብዙሀኑ በጣም ይለያሉ፤ በዚህ ነገር አትፈርበት፤ ስዩም በሆንከው አትፈር፤ በሆንከው አትኩራ፤ ሁለቱም አንተ አይደለህም ተሰጥቶህ ነው ይለኝ ነበር:: ይሄን ካልኩ በቂ ነው::

ለወጣቱ ምን ትመክራለህ?

እድሜ መልካም ነው፤ ነገር ግን እድሜ ብቻ ሲቆጠርብህ ጥሩ አይደለም::እድሜ ማስቆጠር አይደለም መኖር ማለት፤ ሥራን ማስቆጠር ነው መኖር፤ በእድሜህ ሥራን አስቆጥርበት:: ነገ ለወጣቶች እንዳይቆጫቸው የምለው በመኖር ውስጥ መልካም ነገር መሥራት ትክክለኛ መኖር ነው:: በመኖር ውስጥ በጎ ነገር ለማድረግ ደግሞ ትርፍ ፈላጊ መሆን የለብንም:: የተቀበልነውን መስጠት ነው ያለብን:: ያልተቀበልነውን ከየት እናመጣዋለን:: የተቀበልነውን ጓጉተን ለመስጠት እንጣደፍ:: የተቀበልነውን አለመስጠት ባለ እዳ እንደመሆን ነው የምቆጥረው::

ለመስጠት ትርፍ የምትጠብቁ ከሆነ፣ ወይም ወደ ገንዘብ ለመቀየር የምትፈልጉ ከሆነ የተሰጣችሁትን ይዛችሁት ትሞታላችሁ:: ወይም ደግሞ ታበላሹታላችሁ አሊያም ተራ ነገር ታደርጉታላችሁ:: እናቶቻችን ያንዱን ልጅ አንዳቸው ጡት ሲያጠቡ ዋጋ እየተነጋገሩ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነጋዴ ይሆኑ ነበር:: ግን በፍቅር አቅፈው ሰጥተውናል:: ያ በነጻ የተቀበልነው ነው ፍቅር የሆነልን::

ሌላው ደግሞ ዋጋ የማያስከፍል ነገርን አትምረጡ:: ቀላል መንገድ ወደ ፈተና ያስገባል:: ዋጋ ያስከፈለ ነገር ቋሚ ስኬት ይዞ ይመጣል:: ወጣቱ ፈተናን አይጥላ:: ፈተና ለስኬት ዋናው መንገድ ነው:: ወርቅ በእሳት ይፈተናል እንዲሉ አበው::

ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!::

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here