አራት ዐይናዉ ዳኛ

0
150

የእግር ኳስ ዳኝነት አጀማመር ዛሬ እንደምንረዳው አልነበረም። ያኔ ስዓትን ወይም ጊዜን ከመቆጣጠር ያለፈ ሚናም አልነበረውም። በዘመናዊ እግር ኳስ ግን የዳኞች ሚና በአስደናቂ ሁኔታ ተቀይሯል። ዛሬ ላይ ጨዋታዎችን ያስጀምራሉ፤ ሕጎችን ያስከብራሉ፤ የጨዋታውን ፍሰትም ይመራሉ፤ የጨዋታውን ፍትሐዊነት እና ደህንነትም ያስጠብቃሉ።

ሙያው ጥሩ ዐይን፣ ፈጣን ውሳኔ አሰጣጥ፣ የጨዋታን አጠቃላይ ግንዛቤም ይፈልጋል። አሁን ላይ በዳኝነት ሙያ የተደራጀ እና ጠንካራ ስልጠና ቢኖርም ሙያው ግን ሁሌም ከውዝግብ የጸዳ አይደለም። ይህም በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በየጊዜው የምንመለከተው ጉዳይ ነው። በርካታ ዳኞች አወዛጋቢ እና የተሳሳቱ ውሳኔዎችን በማስተላለፋቸው የገንዘብ ቅጣት አለፍ ሲልም ጨዋታዎችን እንዳይመሩ ዕገዳ ሲጣልባቸው ማየት የተለመደ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ዳኞች በላቀ ቴክኖሎጂ እየታገዙ ጨዋታዎችን እየመሩ ነው። ዳኞችን የሚያግዙ በየጊዜው የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ቢደረጉም አሁንም ግን ብዙ ስህተቶች ሊታረሙ አለመቻላቸውን ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። እነዚህ ሁሉ ቴክኖሎጂዎች ሳይመጡ ጣሊያናዊው የቀድሞ ዳኛ ፒየርሉጂ ኮሊና  ታላላቅ የሊግ እና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በአስደናቂ ብቃት መርቷል።

በሙያው ለፍጹምነት የተቃረበ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል፤ በሰማያዊ ቀለም ዐይኖቹ ውስጥ ቫር (VAR) የተገጠመለት ሲሉም ያሞካሹታል። በታላላቅ ጨዋታዎች መሀል የማይጠፋ፤ ሜዳ ላይ በአራት ቋንቋዎች (በፈረንሳይኛ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛ እና በእንግሊዘኛ) መግባባት ይችላል። ተጫዋቾችም በእርሱ በመዳኘታቸው ብቻ ትልቅ ደስታ ይፈጥርባቸዋል፤ ያልተገባ ድርጊት ለመፈጸምም አይደፍሩም ነበር።

እ.አ.አ በ2002 ጃፓን ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ በፍጻሜው ጨዋታ ሮናልዶ ናዛሪዮ ዴሊማ መለያውን እና የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ የተሸለመውን የወርቅ ኳስ ለጣሊያናዊው ዳኛ አብርክቶለታል። የፍጻሜ ተፋላሚ የነበሩት ጀርመናውያንም ምንም እንኳ በብራዚል ተሸንፈው ዋንጫውን ቢያጡም ጨዋታውን የመራበት መንገድ አስደስቷቸው አድናቆታቸውን ገልጸውለታል።

ፒየርሉጂ ኮሊና ወይም በቅጽል ስሙ ዘ ሸሪፍ እ.አ.አ በ1960 በጣሊያን ቦሎኛ ከተማ ነው የተወለደው። ተጫዋች የመሆን ፍላጎት የነበረው ኮሊና በታዳጊነት ዕድሜው በመሀል ተከላካይነት ተጫውቷል። ታዳጊው በተጫዋችነት ግን ስኬታማ እንደማይሆን ቀድሞ በመረዳት በ17 ዓመቱ ሀሳቡን ቀይሮ ፊቱን ወደ ዳኝነት ሙያ አዙሯል። እናም የዳኝነት ስልጠና በመውሰድ የዳኝነት ሙያን ተቀላቅሏል። ጎን ለጎን ደግሞ ከቦሎኛ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ1984 እ.አ.አ አግኝቷል።

እ.አ.አ በ1988 በጣሊያን ሦስተኛ ዲቪዚዮን የዳኝነት ሥራውን ጀምሯል። ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላ ደግሞ በሴሪ ሲ አንድ እና ሴሪ ሲ ሁለት ተሸጋግሯል። የዳኝነት እድገቱ ፈጣን እንደነበር የሚነገርለት ኮሊና ከሦስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ወደ ሴሪ ቢ እና ሴሪ ኤ ተሸጋግሯል።

በ1995 በፈረንጆችም 43 የሴሪ ኤ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት አከናውኗል። በፊፋ ምርጥ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ መካተት የጀመረውም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው። ከዚያ በኋላ ያለው የኮሊና የዳኝነት ህይወት እንደ አፈ ታሪክ የሚነገር መሆኑን የፕሮፌሽናል ዳኞች ማህበር ዘገባ ያመለክታል። ፒየርሉጂ ኮሊና ከአዕምሮ የማይጠፉ በርካታ ጨዋታዎችን መርቷልና ነው።

ከፈረንጆች ሚሊኒየም ማግስት በ2002 እ.አ.አ ጃፓን ባስተናገደችው እና ብራዚል ሻምፒዮን በሆነችበት የዓለም ዋንጫ ኮሊና በሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር። ያላቸውን ክብር ከሜዳ ሳይወጡ ገልጸውለታል።

ጀርመናዊው የቀድሞው ግብ ጠባቂ ኦሊቨር ካህን በወቅቱ “ኮሊና የዓለማችን ምርጡ ዳኛ ነው” ሲል አሞካሽቶታል። ኮሊና ብዙ ታላላቅ የሊግ እና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ጥበብ በተሞላበት ድንቅ ብቃት በዋና ዳኝነት አከናውኗል። ኮሊና ለመጨረሻ ጊዜ ጨዋታዎችን የመራው በ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፓርቹጋል ከስሎቫኪያ ያደረጉት ጨዋታ ነበር።

ስመ ጥሩ ዳኛ ፒየርሉጂ ኮሊና ምንም እንኳ እድሜው 46 ቢሆንም ከሚወደው የዳኝነት ሙያ ግን በጊዜ ነበር የተሰናበተው። ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የበጎ አድራጎት ጨዋታዎችን በመዳኘት ተሳትፏል። ከ2010 እ.አ.አ ጀምሮ የዩክሬን ዳኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል። ኮሊና በ2018 የሩሲያው የዓለም ዋንጫ የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኝነት (ቫር) ተግባራዊ እንዲሆን ካደረጉ ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

በእግር ኳስ ዳኝነት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኘው ጣሊያናዊው የቀድሞ ዳኛ አሁን ላይ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የዳኞች ፕሬዝዳንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በ17 ዓመታት የእግር ኳስ ዳኝነት ህይወቱ በርካታ ስኬቶችን ተጎናጽፏል። ኮሊና በንግድ ውስጥ ተሰማርቶም እየሠራ ሲሆን በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩትን ሌሎች ሰዎችንም ያማክራል።

የቀድሞው ዳኛ የምንጊዜም ምርጥ ዳኞች ሽልማትን ከ1987 እስከ 1920 እአአ በተከታታይ አሸንፏል። በስፖርቱ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ በ2004 እ.አ.አ የእንግሊዙ ሀል ዩንቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክቶለታል። በፈረንጆች 2011  በጣሊያን እግር ኳስ ከታላላቅ ስፖርተኞች መካከል አንዱ በመሆን በክብረ መዝገብ ስሙ ሰፍሯል።

በ2009 እ.አ.አ በእግር ኳስ የተንቀሳቃሽ ምስል ክለሳ ንባብ ተግባራዊ መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ አንስቶ በሥራ ላይ ውሏል። ይሁን እንጂ በቪዲዮ ክለሳ ንባብ ብቻ ውሳኔ መስጠትን ይቃወም እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። የቪዲዮ ክለሳ ንባቡ ዳኞች ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ለመስጠት ብቻ መጠቀም እንዳለባቸውም ያስረዳል። የቀድሞው ዓለም አቀፍ ዳኛ በ2022 ኳታር ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ተጽዕኖው ከፍ ያለ እንደነበር አይዘነጋም።

የተጨማሪ ሰዓት (Extra time) ተግባራዊ የሆነው በእርሱ ነው። በዚህ የዓለም ዋንጫ በየጨዋታው የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ባልተለመደ መልኩ ከዐስር ደቂቃ በላይ ተሰጥቶ ተመልክተናል። ይህም የእርሱ ውጤት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ስመ ጥሩ ዳኛ በአሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኖ የተመሰገነ ብቸኛው ዳኛ ጭምር ነው። በ2005 እ.አ.አ ቸልሲ ከባርሴሎና ጋር ሲጫወት ድሮግባ በሁለት ቢጫ ካርዶች ከሜዳ ይሰናበታል። ሞሪንሆም በወቅቱ ይህን ጨዋታ መምራት የነበረበት ኮሊና ነው ሲል በይፋ ተናግሯል።

የመልሱን ጨዋታ እውቁ ዳኛ በዋና ዳኝነት በመምራት ቸልሲ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፈረንጆች 1998 እስከ 2003 በተከታታይ ለስድስት ዓመታት የዓለማችን ምርጡ ዳኛ የሚል ማዕረግ ሰጥቶታል። የግብ መስመር ቴክኖሎጂ፣ ቫር እና የቪዲዮ ክለሳ ንባቦች ባልነበሩበት ዘመን የሜዳ ላይ ስህተቶች ከእርሱ እይታ አያመልጡም።

ጨዋታዎችን ለመምራት ወደ ሜዳ ከመግባቱ በፊት ጨዋታውን እና የተጫዋቾችን ባህሪ ከእነስማቸው በማጥናት ነበር ወደ ሜዳ የሚገባው። በቪዲዮ ጨዋታዎች (Video Games) ላይ የሚታይ ብቸኛው ዳኛ ነው። ከዳኝነት ህይወቱ ከተገለለ በኋላ እስከ 2010 እአአ በዩክሬን እግር ኳስ ፊዴሬሽን የዳኞች ሊቀመንበር ሆኖ ሠርቷል። የአውሮፓ እግር ኳስ ዳኞች ኮሚቴ አባል እና የፊፋ ዳኞች ኮሚቴ አባል እንደነበረም ይታወሳል።

ጨዋታዎችን በፍትሐዊነት የመምራት ብቃቱ፣ ጨዋታን የመቆጣጠር ክህሎቱ፣ የእግር ኳስ ሕግ እና ደንቦችን የመረዳት እውቀቱ፣ ጫናዎችን የመቋቋም ብቃቱ እና ውሳኔ አሰጣጡ አስደናቂ እንደነበር የእግር ኳስ ቤተሰቡ ይመሰክርለታል። ይህም ለስፖርቱ ትቶት ያለፈው ትልቅ ሀብት እንደሆነ ይጠቀሳል። የፒየርሉጂ ኮሊና ስም ሲነሳ የጥሩ እና የከፍተኛ ደረጃ ዳኝነት መለኪያም ሆኖ ይነሳል። ደጋፊዎች የሚደሰቱበት ጥሩ ጨዋታ ከሆነ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የሚመራው ኮሊና ስለመሆኑ ደጋፊዎች ለአፍታም አይጠራጠሩም።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here