በተሽከርካሪ ላይ ድብ ጉዳት አድርሶብናል በሚል ለመድን ኩባንያ የክፍያ ጥያቄ በአስረጂነት ተያይዞ የቀረበ ተንቀሳቃሽ ምስል አልባሳት በለበሰ ሰው መፈፀሙን ኩባንያው አጣርቶ በማጭበርበር ወንጀል መክሰሱን አሶሼትድ ኘሬስ ድረገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በአሜሪካ የካሊፎርኒያ መድን መምሪያ ክፍያ ጠያቂዎቹን በተነቀነባበረ የሀሰት ማስረጃ 142,000 ዶላር የማጭበርበር ወንጀል ከሷቸዋል፡፡
አራቱ የሎስአንጀለስ ኗሪ ተከሳሾች ባለፈው ዓመት ጥር ወር ከሳንበርናዲኖ ተራራ የወጣ ድብ በሮልስ ሮይስ እና በማርቸዲስ ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል የተጫጫሩ ወንበሮች እና በሮች እንዲሁም የውጪውን ክፍል አሳይተዋል፡፡
የኩባንያው ባለሙያዎች የተቀረፀውን ምስል ተመልክተዋል- በባለሙያም አስገምግመዋል፡፡ በመርማሪው ማጠቃለያ መሰረት አራቱ ተከሳሾች ለሁለት የመድን ኩባንያዎች በተመሳሳይ ቀንና ቦታ የተቀረፀን ምስል ለመድን ካሳ ጥያቄ ማቅረባቸውን አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ለካሊፎርኒያ የዱር አራዊት ባለሙያ የተቀረፀው ምስል ተሰጥቶት ሙያዊ ትንተና እንዲሰጥበት መደረጉን ነው ጽሁፉ ያሰፈረው፡፡
ባለሙያውም ወንበሮቹ አና በሮቹን “ድቡ” በጥፍሩ ሲጫጫር የካሜራው አቅጣጫ እና ርቀቱን አገናዝቧል፡፡ “ድቡ” በተሽከርካሪው መስኮት ቆሞ እንደሚታይ እና ካሜራው ተሽከርካሪ ውስጥ ሆኖ መቀረጹን ነው የጠቆመው- ባለሙያው፡፡
ባለሙያው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተቀረፀውን ምስል አጢኖ እና ገምግሞ የቀረበው የተቀረፀ ምስል “ድቡ” ሰው ሰራሽ የ “ድብ” ልብስ በለበሰ ሰው የተፈፀመ መሆኑን አረጋግጧል፡
በመጨረሻም የመድን ኩባንያው የመድን ጠያቂዎቹ ቤት እንዲፈተሽ ማዘዣ አስቆርጦ ባደረገው ብርበራ መድን ጠያቂዎቹ የተገለገሉበት ሰውሰራሽ የድብ ልብስ መገኘቱን ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም