ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል

0
134

በአማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤቶች ሰባት ሚሊዮን 71 ሺህ 933 ተማሪዎቸን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ እንደ ነበር የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ የተመዘገቡት ሁለት ሚሊዮን 543 ሺህ 128 መሆናቸውን ቢሮው አሳውቋል። ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል ነው ያለው።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የ2017 ዓ.ም የትምህርት ቢሮን የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም የግምገማ ሪፖርት አቅርበዋል። በግምገማው በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት እና ግጭት በትምህርት ዘርፉ ላይ በትሩን አሳርፏል ብለዋል።

ቢሮ ኃላፊዋ እንዳሉት በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መጻሕፍት ለዘረፋ እና ውድመት ተጋልጠዋል። በ17 ወረዳዎች ደግሞ አንድም ትምህርት ቤት አልተከፈተም። እንደ ክልልም 40 በመቶ ምዝገባ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ዶ/ር ሙሉነሽ እንዳብራሩት የትምህርት ሥርዓቱ በተለይም ከ2013 ዓ.ም ወዲህ በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች በእጅጉ እየተፈተነ ነው። በሰሜኑ ጦርነት ከወደሙ አራት ሺህ ትምህርት ቤቶች መካከል የተጠገኑት ከ10 በመቶ የማይበልጡ ሲሆን ይህም በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በ2016 ዓ.ም በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም እጦት ደግሞ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ አድርጓል። ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችም እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል።

በፀጥታ ችግሩ አሁንም የቅድመ አንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑ፤ መጻሕፍት በበቂ መጠን አለመቅረብ የቀጠለ ችግር እንደሆነ ቢሮ ኃላፊዋ አመላክተዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here