ኅብረተሰቡ ከአጭበርባሪዎች ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ ተሰጠ

0
121

ከባንክ እንደተደወለ አስመስለው የተለያዩ ስልኮችን በመጠቀም የግለሰቦችን የባንክ የምስጢር ቁጥር በመቀበል በማጭበርበር ከግለሰቦች የሂሳብ ቁጥር ብር ከሚመዘብሩ ወንጀለኞች ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ የባንክ ስሞችን ተጠቅመው ለግለሰቦች በመደወል የሚያጭበረብሩ ሰዎች መበራከታቸው ተገልጿል።

አጭበርባሪ ግለሰቦቹ ሲስተም እያስተካከልን ነው፤ የባንካችን ተሸላሚ ደንበኛ ሆነዋል እና የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም የሞባይል ባንኪንግ የምስጢር ቁጥር እንዲያስገቡ በማግባባት ማጭበርበሩን እንደሚፈጽሙ ነው የተብራራው።

በግለሰቦች የሂሳብ ቁጥር የተቀመጠ ገንዘብን ወደ ራሳቸው የሚወስዱ አጭበርባሪዎች መበራከታቸውንም ደርሸበታለሁ ብሏል ፌዴራል ፖሊስ።

ኅብረተሰቡም የእንዲህ አይነት የመጭበርበር ወንጀል ሰላባ እንዳይሆን ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል።

ኅብረተሰቡ ተጠርጣሪዎችን ሲመለከት ተቋሙ ያበለፀገውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) በመጠቀም ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመደወል በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ እና ደኅንነት አካላት በአካል በማድረስ የድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

 (መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here