ምሶሶውን የማጽናት ጉዞ

0
139

እንደ መንደርደሪያ

ኢትዮጵያ ግብርናን የምጣኔ ሐብቷ ሁሉ ምሶሶ አድርጋ ትወስዳለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ከ85 በመቶ በላይ ለሚሆነው ሕዝቧ መተዳደሪያው፣ ሀገራዊ ምጣኔ ሐብታዊ ድርሻው ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ፣ ሰፊ እና ምቹ የእርሻ መሬት መኖሩ፣ በገጸ ምድር እና ከርሰ ምድር ውኃ የታደለች መሆኗ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ/ር) ከአሚኮ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ግብርና 33 በመቶ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ ይህ ወደ አማራ ክልል ሲመጣ ከአጠቃላይ ክልላዊ የምርት ድርሻ ከ51 በመቶ በላይ ይወስዳል፡፡ ወደ ውጭ ከሚላኩ /የኤክስፖርት/ ምርቶች የግብርና ውጤቶች  እስከ 70 በመቶ፤ የሥራ ዕድል በመፍጠር ደግሞ እስከ 73 በመቶ ድርሻ በመያዙ ለግብርናው ምሶሶነት ሌላው ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ  የዝናብ መጠን እና የውኃማ አካላት በስፋት የሚገኝባት ሀገርም ናት፡፡  ዓመታዊ የዝናብ መጠኗ 980 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እንዲሁም  የገጸ ምድር ውኃ ድርሻዋ 123 ቢሊዮን ሜትር ኩብ መሆኑን ኢንጅነር ዳኝነት (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ለእርሻ ምቹ የሆነ ከ13 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ያላት ሀገር መሆኗም ግብርናን የሕልውናዋ ሁሉ መሠረት አድርጋ እንድትጓዝ ያደርጋታል፡፡ ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂ መር የአስተራረስ ዘዴን አለመከተሏ፣ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃዋን በጸጋነት ከማየት ባለፈ ለመስኖ ልማት አለመጠቀሟ ዜጎቿ ዘመናትን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ እንዲገፉ ሆነዋል፤ አሁንም ድረስ የእርዳታ ድርጅቶች መሽቀዳደሚያ ሆና እንድትቀጥል አድርጓታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ ጸጋዋን ዐይታ ከማደር ወደ መጠቀም፣ ከተረጂነት ወደ ረጂነት፣ ከሸማችነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራትን ምርት የማምረት ትልምን በመስኖ ለማሳካት እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡

 

አስታራቂው ጅማሮ

ኢትዮጵያ ከመኸር እርሻ በተጨማሪ በመስኖ ልማት ምርታማነትን ለማረጋገጥ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ መስኖ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እስከ አራት በመቶ እንዲሁም ከአጠቃላይ የግብርና ምርቶች ደግሞ ከ9 እስከ 12 በመቶ ድርሻ እንዳለው ኢንጅነር ዳኝነት (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ በመሆን ባደረጉት ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ በመስኖ መልማት የሚችለው አጠቃላይ የማሳ መጠኗ 10 ሚሊዮን ሄክታር መሆኑ ደግሞ በእርግጥም ምርታማነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡ መስኖ ልማት በተፈጥሮ ከሚከሰቱ እንደ ድርቅ፣ ተባይ፣ ተምች እና ሌሎች በመሳሰሉ የሰብል ምርቶች የመጠቃት ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑ መስኖ ልማት ላይ ለማተኮር ገፊ ምክንያት መሆኑንም ኢንጅነር ዳኝነት ጠቁመዋል፡፡

እነዚህም ምክንያቶች ኢትዮጵያን በተለይም ለዘመናት ለከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ሲዳርጋት የቆየውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመቻል፣ ለውጪ ገበያ ከማቅረብም ያለፈ የተረጂነት መጥፎ ስሟን ለማደስ ብሎም የውጪ ምንዛሪ ችግሯን ለመፍታት የስንዴ ልማት ላይ በስፋት እየሠራች ትገኛለች፡፡

 

ስንዴ እና የኢትዮጵያ ጉዞ

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተጠናው እና በአፍሪካ ጆርናልስ ኦንላይን ላይ ሰፍሮ የሚገኘው ጽሑፍ እ.አ.አ በ2050 የዓለም የምግብ ፍላጎት አሁን ካለበት በ70 በመቶ ሊጨምር እንደሚቻል አመላክቷል፡፡ የሕዝብ ቁጥርን ታሳቢ ያደረገ የግብርና ምርትን ማሳደግ እንደሚገባ፣ ለዚህም በዓለም በምርታማነቱ ከበቆሎ ቀጥሎ የሚገኘውን የስንዴ ልማት እንደ ዋና መውጫ መንገድ መውሰድ እንደሚገባ ጥናቱ በማከል ጠቁሟል፡፡

በተለይ ስንዴ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚፈለግ፣ በዋጋ ውድ መሆን ምክንያት እና በዝቅተኛ ምርታማነቱ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ያላረጋገጠ ሆኖ ውስንነቱ ይነሳበታል፡፡

ኢትዮጵያ ግን የመጪው ዘመንን የምግብ ፍላጎት ቀድማ የተረዳች እስክትመስል የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ እና ከተረጂነት አዙሪት ወጥታ ስንዴን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ያለፈ የተረጂነት መጥፎ ስሟን ከታሪክ ማኅደር ፍቆ የውጭ ምንዛሪ ችግሯን ለመፍታት ዋና ዓላማዋ አድርጋ እየሠራች ትገኛለች፡፡ የጥናት ውጤቱ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ላይ በስፋት መሥራት የጀመረችው ከባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ጥናቱ የ2014 የምርት ዘመንን በዋቢነት ሲያነሳ በወቅቱ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን አርሶ አደሮች የተሳተፉበት አንድ ነጥብ 89 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ተሸፍኗል፡፡ አምስት ነጥብ 78 ሚሊዮን ቶን ስንዴ መመረቱንም አስታውቋል፡፡ በሄክታር 30 ነጥብ 46 ኩንታል መመረቱም ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳያ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ለውጭ ገበያ በ2015 ዓ.ም ማቅረቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም ወርሀ የካቲት ማስታወቃቸው ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እና ውጤት አበረታች ለመሆኑ ማሳያ ተደርጎም ይነሳል፡፡ ስንዴን በበጋ መስኖ የማልማት ጥረቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮዎች እና የተጠሪ ተቋማት የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማን ባካሄዱበት ወቅት ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዓመቱ በበጋ መስኖ ስንዴ ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ተሸፍኖ 118 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

 

የአማራ ክልል ጸጋ እና የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ

ኢንጅነር ዳኝነት (ዶ/ር) አማራ ክልል 177 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዓመታዊ የዝናብ መጠን እንደሚያገኝ፤ ከ48 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የገጸ ምድር ውኃ ባለቤት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ክልሉ በሚታረስ መሬት እና በአምራች የሰው ኅይል በከፍተኛ ደረጃ የታደለም ነው፡፡ ክልሉ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በመስኖ የሚለማ መሬት እንዳለው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዓመታዊ የመስኖ ልማት ሽፋኑ ከ250 ሺህ አልዘለለም፡፡ ከዚህ ውስጥ በዘመናዊ መንገድ እየለማ የሚገኘው 110 ሺህ ሄክታር መሆኑ ደግሞ አሁንም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቋሚ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

በክልሉ ትላልቅ ወንዞች፣  ለመስኖ ልማት ምቹ እና ሰፊ የእርሻ መሬት አላቸው ተብለው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል አንዱ የሰሜን ጎጃም ዞን ነው፡፡ በዞኑ የሚገኘው የቆጋ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ደግሞ በበጋ መስኖ ልማት ይበልጥ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አጋዥ ሆኖ ይነሳል፡፡

የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ንቅናቄ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሰባታሚት ቀበሌ በተጀመረበት ወቅት ወቅት 19 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር እንደ ሚሸፈን እና ከዚህም 780 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ለልማቱም 58 ግድቦች፣ 6 ሺህ 518 የውኃ መሳቢያ ሞተር፣ ሦስት ሺህ 31 ባሕላዊ የወንዝ እና ምንጭ ጠለፋ፣ በዚህ ዓመት ለአርሶ አደሮች የተከፋፈሉ 13 ትራክተሮችን ጨምሮ በድምሩ 21 ትራክተሮች በዞኑ መገኘታቸው በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን አስቻይ ሁኔታዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው በ2017 የበጋ እርሻ 343 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ይሸፈናል፡፡ ክልሉ ባለው ጸጋ ልክ ምርታማነትን በማረጋገጥ በምግብ ራስን የመቻል ግብን ለማሳካት ሁሉም የመስኖ ልማት ሥራዎች በሦስት ዙር እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል፡፡

ዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ማሳካትን ታላሚ ያደረገ 230 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል እንደሚሸፈን አቶ ቃል ኪዳን አስታውቀዋል፡፡ አማካይ ምርታማነቱንም በሄክታር 37 ኩንታል ማድረስ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡ ለዚህም ልማቱ በተለይ ባለፉት ዓመታት የተሻለ ልምድ በታየባቸው አካባቢዎች፣ ለተመሳሳይ ምርቶች አንድ አካባቢ /ለክላስተር/ ትግበራ እና ለሜካናይዜሽን ምቹ እና ምርታማ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚተገበር አቶ ቃልኪዳን አረጋግጠዋል፡፡

 

ትኩረት የሚያሻቸው ስጋቶች

ምርታማነትን ለማረጋገጥ በወቅቱ  መዝራት ዋናው መፍሔሄ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ፣ እስካሁን 34 ሺህ 53 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ክልል በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የእርሻ ሥራን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደ መንግሥት በአሁኑ ወቅት እየተሠራጩ ካሉ ትራክተሮች በተጨማሪ በማኅበራት፣ በግለሰብ እና በባለሐብቶች እጅ ያሉ ትራክተሮች በሙሉ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ የመስኖ ስንዴ ልማት በሰሜን ጎጃም ዞን ባስጀመሩበት ወቅት ምርትን ከጥራት ጋር ለማሳደግ እስካሁን ሁለት ሺህ ትራክተር መሰራጨቱን እና 56 ኮምባይነር ወደ ክልሉ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

የመኸር ሰብሉ የመስኖ ልማት ሥራውን እንዳያዘገየው የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር ታግዞ በፍጥነት የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው ጠቅሰዋል፡፡ የዘር ሥራን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ሌላው በትኩረት እየተሠራበት ያለው በአንድ ቀን ዘርን በዘመቻ ማስጀመር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ለመስኖ ልማት የሚሆን መሬት ያላቸው እና መሬት ተከራይተው የሚያርሱ ባለሐብቶች በስንዴ ልማት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ ውይይት መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ለመስኖ ልማቱ በቂ የአፈር ማዳበሪያ መኖሩን ምክትል ቢሮ ኃላፊው  አረጋግጠዋል፡፡ እጥረት ያጋጥማቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን ቀድሞ በመለየት የተሻለ ክምችት ካለባቸው አካባቢዎች በማዟዟር ችግሩን ለመፍታት ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

የምርት ጭማሬ ከ30 እስከ 50 በመቶ እንደሚያበረክት የሚታመንበት ምርጥ ዘርም ሌላው እንደ ክልል በዓመቱ የበጋ ወቅት ለማሳካት የታሰበውን የስንዴ ምርት ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ አበርክቶ አለው፡፡ ከዚህ አኳያ የከረመ የስንዴ ምርጥ ዘር መኖሩን ያስታወቁት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ነገር ግን ሁሉንም በምርጥ ዘር ለመሸፈን እጥረት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን ሳይጠብቅ ቀድሞ ባመረተው እና እጁ ላይ በሚገኝ ዘር ማሳውን እንዲሸፍን ጠይቀዋል፡፡

መስኖ የውኃ አማራጭ ባለባቸው ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተለመደ እንዲሆን የውኃ መሳቢያ ሞተር በስፋት እየተሠራጨ መሆኑን አቶ ቃልኪዳን አስታውሰዋል፤ ነገር ግን የነዳጅ አቅርቦት ፈተና ሆኖ መስተዋሉን ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ችግር በመፍታት የመስኖ ልማቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል እያንዳንዱ ወረዳ የልማቱ ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮችን ስም ዝርዝር ለይቶ ለንግድ እና ገበያ ልማት እንዲያሳውቅ በማድረግ ነዳጅ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በስንዴም ሆነ በሌሎች የሰብል፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍ ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ አሁንም ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች አሉ፡፡ ያለን የውኃ ሐብት በመስኖ ሊለማ ከሚችል መሬት ጋር አቆራኝቶ ነባር ግን ያልተጠናቀቁ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና ፍጥነት ማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ግድቦችንም መገንባት ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ በአማራ ክልል ከፍተኛ የመልማት ዕድልን ያጎናጽፋሉ ተብሎ ከበርካታ ዓመታት በፊት የተጀመሩ የመገጭ እና የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች አሁንም ልማትን ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን እየፈጠሩ ቀጥለዋል፡፡ እንደ አቶ ቃልኪዳን ፕሮጀክቶቹ እያለሙ የሚሠሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከክልሉ መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው፡፡

የክልሉ የሰላም ችግር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ፈተና እንዳይሆን ልዩነቶችን ፈጥኖ በሰላማዊ መንገድ መቋጨት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡ በሰሜን ጎጃም ዞን የመስኖ እርሻ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር፣ ግብዓትን ለኢንዱስትሪዎች በጥራት እና በብዛት ለማቅረብ መንግሥት ማዳበሪያ እና ትራክተር ማቅረብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ የግብርና ሥራ ሰላም እና ነጻነት ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ሰላምን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጎን ሊሰለፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ያለው ታጣቂ ኅይልም የክልሉ መንግሥት ለሰጠው የሰላም ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የሕዝብ አሳቢነቱን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here