ልማት ያለ ግብር…

0
159

በኢትዮጵያ የግብር እና የቀረጥ አጀማመር ከመንግሥታት አመሠራርት ጋር  የተቆራኘ ነው። ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማዕከላዊ መንግሥት እየተጠናከረ እስከመጣበት ጊዜ የነበረው የግብር አሰባሰብ የተበታተነ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ። ይህን ለማስተካከል አፄ ቴዎድሮስ በወቅቱ ያደረጉት ጥረትም ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል።

በሀገራችን የግብር ሥርዓት በአፄ ዘርዕያቆብ ተጀምሮ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አዋጅ ወጥቶለት  ማሻሻያዎች እየተደረጉበት አሁን እስከደረስንበት ዘመን ዘልቋል። በወቅቱ ግብር የሚከፈለውም በጉልበት/አገልግሎት በመስጠት/፣ በዓይነት እና  አልፎ አልፍ ደግሞ በገንዘብ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በመሆኑም ግብር ለሀገር ልማት የሚውል የሀብት ምንጭ ተደርጎ ይወሰዳል። መንግሥት በሕግ እና ደንብ ተመስርቶ ከሕዝብ እና ከድርጅት ገቢ የሚያገኝበት ዋነኛ መንገድ ነው። ይህም ለሀገር ልማት፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ እና ለመልካም አስተዳድር ችግሮች መፍቻ እንዲሁም ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በመሆን ያገለግላል።

በሀገራችን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና በታክስ ሕግጋት መሠረት መንግሥት የተለያዩ የግብር ዓይነቶችን በመጣል ገቢ ይሰበስባል። እነዚህም የገቢ ግብር፣ የተርን ኦቨር ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ታክስ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

ዜጎች ዕውቀታቸውን በመሸጥ፣ ቤታቸውን በማከራየት፣ በሥራ እና በሌላ መንገድ ከሚያገኙት ገቢ በሕግ በተቀመጠው አሠራር እና ሕግ መሠረት ግብር ይከፍላሉ። የተሰበሰበው ግብር ደግሞ ለደመወዝ፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ (ለትምህርት ቤት፣ ለመንገድ፣ ለጤና ጣቢያ፣ ለሆስፒታል፣ ለንፁህ መጠጥ ወኃ፣ ለድልድይ፣ ለኃይል አቅርቦት) እና ለሌሎች አገልግሎቶች ይውላል። በመሆኑም በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ግብር መሰብሰብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ግብር በመሰብሰብ ላይ ይገኛል። ለአብነትም የአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር በበጀት ዓመቱ የፀጥታ ችግሩን ተቋቁሞ ግብር እየሰበሰበ መሆኑን አስታውቋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈጠነ ጥላሁን በስልክ ለበኵር እንደተናገሩት “እኛ ኢትዮጵያዊያን ‘የመንግሥት የሆነውን ለመንግሥት፤ የቄሳር የሆነውን ለቄሳር’ የሚል ግብር የመክፈል ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን ተረድተን ስንተገብር ስለመቆየታችን አባባሎቻችንም ምስክሮቻችን ናቸው” በማለት ግብር መክፈል የቆየ ሀገራዊ ግዴታ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል::

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በገቢ አሰባስቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል። ይሁን እንጂ በግጭት ውስጥ ሆኖም ግብር ለመሰብሰብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብር መቼም ቢሆን መቼም፤ የትኛውም መንግሥት ይምጣ  አይቀሬ እና በጊዜው እንኳን ባይከፈል እዳ ሆኖ እንደሚቀጥል ማኅበረሰቡ እንደሚገነዘብም መምሪያ ኃላፊው አንስተዋል:: በመሆኑም ግብር ከፋዩ አንፃራዊ ሰላም ያለባቸውን ጨምሮ የፀጥታ ችግሩ ሙሉ በሙሉ በሌለባቸው አካባቢዎች የሚጠበቅበትን ግብር እየከፈለ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ፈጠነ ማብራሪያ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ከመደበኛ ገቢ እና ከከተማ አገልግሎት 3 ቢሊዮን 148 ሚሊዮን 643 ሺህ 594 ብር ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ከዚህ ውስጥ  እስካሁን 527 ሚሊዮን 819 ሺህ 144  ብር መሰብሰብ ተችሏል:: የተገኘው ገቢም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የተሻለ  ነው ብለዋል።

በቀጣይም ከደረጃ “ሀ” እና “ለ”፣ ከአከራይ ተከራይ፣ ከውዝፍ  እና ከእርሻ ሥራ ግብር በመሰብሰብ ገቢውን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም መምሪያ ኃላፊው አረጋግጠዋል::

ዳንግላ ከተማ፣ ጃዊ፣ ፈንድቃ እና አዲስ ቅዳም  በብሔረሰብ አስተዳደሩ በዋናነት ገቢ የሚሰበሰብባቸው ከተሞች ናቸው። ሆኖም የተፈጠረው የፀጥታ ችግር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ቻግኒ፣ ጓንጓ፣ አንከሻ እና አየሁ ጓጉሳ በግብር አሰባሰቡ የተሻለ አፈፃፀም ያሳዩ አካባቢዎች ናቸው። በአንፃሩ ቲሊሊ፣ ፈንድቃ፣ ፋግታ፣ ዳንግላ እና ጓጉሳ አካባቢዎች በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በሰፊው ግብር ያልተሰበሰበባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ በቀጣይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ወቅታዊ የፀጥታ ችግሩ በሠራተኞች ላይ ጫና ቢያሳድርም ፈተናውን  ተቋቁሞ መሥራት መቻላቸውን አስረድተዋል።

ነጋዴዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ ንግድ ፈቃዳቸውን ማሳደስ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ መክፈል እንዳለባቸው አቶ ፈጠነ አስገንዝበዋል::

የግብር አሰባስብ ሒደቱ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ደግሞ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት መምሪያ ኃላፊው፤ በአሠራሩ ቅሬታ ያለው ግብር ከፋይ ቅሬታውን የሚያቀርብበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል። የፀጥታ ችግር የገጠማቸው ከተሞች እና ወረዳዎች ደግሞ ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መምሪያ ኃላፊው እንደሚሉት ግብር በወቅቱ አለመክፈል ለቅጣት እና ለወለድ ይዳርጋል። በመሆኑም ግብር ከፋዩ በወቅቱ በመክፈል ራሱን ከእዳ ነፃ ማውጣት ብሎም ሀገሩንም ማልማት ይጠበቅበታል ።

የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ቀለም ተስፋዬ በበኩላቸው እንደተናገሩት የግብር ከፋዩ ግንዛቤ እንዲያድግ አስፈላጊ የሚባሉ ሥራዎች እና የቅስቀሳ ተግባራት ተከናውነዋል። ለአብነትም በተለያዩ አካባቢዎች መድረኮች ተዘጋጅተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፣ በራሪ ወረቀቶችን በማሰራጨት  ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል። እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም እውቅና እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በዞኑ ባለፉት ጊዜያት ተከስቶ በነበረው የሰላም እጦት የግብር አሰባሰቡ ችግር ገጥሞት እንደነበርም ወይዘሮ ቀለም አንስተዋል። በዚህም ግብር ከፋዩ የራሱን ሀብት አንቀሳቅሶ ለመሥራት ከባድ ችግር ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን ተከትሎ ግብር ሰብስቦ ለልማት ለማዋል ፈተና ሆኖ መቆየቱን ነው ለበኵር በስልክ የተናገሩት:: አሁን ላይ ግን አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ ግብር እየተሰበሰበ   መሆኑን ነዉ ያረጋገጡት ።

በበጀት ዓመቱ ዞኑ 3 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ  እስካሁን  1 ቢሊዮን 59 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል:: ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ332 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ እንዳሳየ ገልፀዋል። በዞኑ ከ410 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራ ገቢ (ከአርሶ አደሩ የመሬት መጠቀሚያ) የሚሰበሰብ ግብር በመኖሩ አርሶ አደሮችም በወቅቱ እንዲከፍሉ አሳስበዋል።

ከገቢ አኳያ እንደ ዞን የተሻለ አፈፃፀም ያመጡ እንሳሮ፣ ቡልጋ ከተማ አስተዳድር፣ ሲያ ደብርና ዋዩ፣ አንጎለላና ጠራ፣ መርሐቤቴ እና አረርቲ ወረዳዎች የበለጠ እንዲበረታቱ እና የበለጠ ገቢ እንዲሰበስቡ እውቅና እና ሽልማት ስለመሰጠታቸውም አንስተዋል::  በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጣርማ በር፣ መንዝ ማማ እና ባሶ እና ወራ ወረዳዎች ደግሞ  በዝቅተኛ አፈፃፀም የሚገኙ ናቸው።

ባለ ድርሻ አካላት ደረሰኝ መስጠት እና ግብር ከፋዩም ደረሰኝ መቀበል እንዳለበትም መምሪያ ኃላፊዋ አስገንዝበዋል:: ግብር በአግባቡ እና በወቅቱ ካልተሰበሰበ በዞኑ እየተገነቡ ያሉ የልማት ሥራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንቅፋት መሆኑን በመገንዘብ ከባለሙያ እስከ መሪዎች ተቀናጅቶ ግብር መሰብሰብ እንደሚገባም  ጥሪ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ እንደገለፁት ግብር ለአንድ ሀገር እድገት እስትንፋስ እና የህልውና ጉዳይ ነው። ግብር አግባብነት ባላቸው ሕጎች በመንግሥት የሚጣል የግዴታ ክፍያ ነው:: ይህም ማለት ግብር አግባብነት ባላቸው ሕጎች በሕግ ሳይፈቀድ ማናቸውም አይነት ግብር የማይሰበስብ ሲሆን እነዚህ ሕጎች የተፈፃሚነታቸው ወሰን ግብር ከፋይ ማን እንደሆነ? መቼ እና እንዴት መከፈል እንዳለበት፣ የግብር መሠረት ምን እንደሆነ፣ ግብሩ በምን ምጣኔ እንደሚከፈል እና ሌሎችም የግብርን አስተዳደር የተመለከቱ ጉዳዮችን ያካትታል። ግብር ከፋዮቹ  የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የከተማ አገልግሎት ግብር እና ሌሎች የግብር ዓይነቶች እንደሚከፍሉም ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት::

ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ  አቅዶ እየሠራ ይገኛል።   ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት የህዳር ወር መገባደጃ ድረስ   16 ቢሊዮን 922 ሚሊዮን 341 ሺህ 515 ብር መሰብሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል:: ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት አሥር ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር እንደተሰበሰበ አስታውሰዋል። የተሰበሰበው ገቢም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል::

ለግብር አሰባስቡ መሻሻል ምክንያቶችንም አስቀምጠዋል፤ ዘንድሮ ካለፈው ዓመት የተሻለ አንፃራዊ ሰላም መኖሩ፣ ጠንካራ የየዕለት የመረጃ ልውውጥ መደረጉ፣ ሁሉም የሥራ ሂደቱ ለገቢ ሥራው ልዩ ትኩረት መስጠቱ፣ በትብብር መሥራት መቻሉ እንዲሁም በክልሉ የግብር ሕጉን አክብረው የሚከፍሉ ምስጉን ግብር ከፋዮች በወቅቱ መክፈላቸው ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው።

ግብር በተገቢው መንገድ መክፈል  የዜጎችን ደህንነት፣ ማህበራዊ ጤንነት ለመጠበቅ እና  መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት አይነተኛ መሳሪያ መሆኑንም አመላክተዋል:: ግብር   ወሳኝ የልማት ማነቆዎችን ለመፍታት እና የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል  ትልቅ መሳሪ  መሆኑንም ገልጸዋል::

በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ያለባቸው አካባቢዎች የተሻለ የገቢ አፈጻጸም እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል:: አሁንም ድረስ ዝቅተኛ የገቢ አሰባሰብ ላይ ያሉ አካባቢዎች መኖራቸውንም አክለዋል:: ወቅታዊ የክልሉ የሰላም እጦት በግብር አሰባስቡ ላይ መሠረታዊ ችግር ነበር ብለዋል። ለዳይሬክተሩ በግብር ከፋዩ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንዴት መፈታት እንዳለባቸው  ጥያቄዎችን አንስተንላቸዋል::

በምላሻቸውም ቢሮው ፍትሐዊ የግብር አጣጣልን መሠረት አድርጎ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚታዩ ጉድለቶች እንዳሉም  አመላክተዋል። አላግባብ ግብር ከፍ እና ዝቅ የሚሆንበት ሁኔታ ሲከሰት ችግሩ የሚታይበት መንገድ መኖሩን አንስተዋል። በግብር አጠጣል እና አሰባስብ ላይ በግብር ከፋዩ ዘንድ ቅሬታ ካለ ቅሬታቸውን አቅርበው በድጋሜ የሚታይበት መንገድ መኖሩንም ጠቁመዋል። በቅሬታ አፈታቱ ዙሪያም አልተስተካከለም ብሎ የሚያምን ከሆነ በይግባኝ የሚታይበት አሠራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ እምነት በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ለህሊናቸው፣ ለሙያቸው እና ለኃላፊነታቸው በመታመን ሊሠሩ ይገባል። ከዚህ ባለፈ ግብር ከፋዮችን በተገቢው መንገድ ማገልገል እና ከሙስና የፀዳ አሠራርን መከተል ይኖርባቸዋል። ግብር ከፋዩም የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ለሀገር ልማት እና መሠረተ ልማት ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ሃገራዊ ግዴታዉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here