ከሰው ቀድማ ዓይኗን የገለጠችው፣ ለዓለም የስልጣኔ ቀንዲሏ፣ የባህል ቤተ መዘክር፣ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሀብት የታደለችው የአፍሪካ ምድር እጅግ የአሁኑን አያድርገውና የገነነ ታሪክ ነበራት። የዓለምን የስልጣኔ በር የከፈቱ ምጡቅ አእምሮዎችን ያፈለቀች፣ በራሷ ማንነት የምትኮራ የአስተዋይ፣ ጥበበኛ፣ ትሁት፣ ታታሪ፣ አፍቃሪ፣ አክባሪ እና ቆፍጣና የጀግኖች መፍለቂያ ነበረች። ድሮ ድሮ ጥቁርነት ውበት እና ክብር እንጂ መሰደቢያ አልነበረም። ጥቁር ሕዝብ አስተዋይ፣ ባለፀጋ፣ አዋቂ እና ስልጡን ጌታ ሕዝብ ነበር እንጂ የተናቀ አልነበረም።
አሁን አሁን ግን ያ ጌታ የነበረ ማንነት፣ ሸማ ሰርቶ መልበስን ያስተማረ ሕዝብ፣ ከድንጋይ ዘመን ወደ ብረት ዘመን ዓለምን ከድቅድቅ ጨለማ መሀል መርቶ ያወጣ ስልጣኔ አመንጭ፣ ኩሩ አፍሪካዊ ማንነቱ ከከፍታው ወርዷል። አንድ ጊዜ ባርነት፣ ሌላ ጊዜ ቅኝ አገዛዝ በታሪኳ ውስጥ እየተፈራረቁ አህጉሪቷን አደቀቋት። ልጆቿ እንደ እንስሳ ከቀያቸው እየታነቁ ለባርነት ተቸበቸቡ። ከስምንት መቶ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ በሀይል ወደ ባእዳን ምድር ተጋዙ፤ ለዘመናት ጉልበት እውቀታቸው ተሰርቆ የዘራፊዎቻቸውን ሀገር ገነባ፤ ካዝናዎቻቸውን በሀብት አጨናነቁት፤ በአፍሪካ ውርደት አውሮፓ ከበረች። የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ድንቅ ከተሞች የጥቁር እፁብ ድንቅ እጆች ውጤት መሆናቸውን አይክዱም። ነገር ግን ለ400 ዓመታት ያህል በመከራ በስቃይ የጎበጠው አፍሪካዊ የማታ ማታ ነፃነቱ በይፋ ሲታወጅለት መልካም ዘመን የመጣለት መሰለ።
ነገር ግን አሳዳሪዎቹ የተስማሙላት አይመስልም። ጥቅማቸው የቀረ ያህል የተሰማቸው የቀድሞ የባሪያ አሳዳሪዎቹ በጀርመኗ በርሊን ከተማ የአስራ አራት ሀገራት ተወካዮች ተገናኝተው፣ “በዝግ” ስብሰባ የአፍሪካን አህጉር ለአውሮፓውያኑ ኃያላን ለመሸንሸን አንዳች ነገር መዶለት ይዘዋል፣ ከኅዳር 6 እስከ የካቲት 19 ቀን 1877 ዓ.ም አፍሪካን ለመቀራመት፤ የበርሊኑ ጉባኤ ግን አፍሪካን ቅኝ ለመግዛት መንገድ ጠርጎላቸዋል።
አውሮፓውያኑ የጫኑት የቅኝ አገዛዝ ስርዓት አፍሪካውያን በራሳቸው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ችሎታቸውን ቀምቷል። አውሮፓውያኑ ኃያላን ለአፍሪካውያን ቅድስናን እና የኢኮኖሚ እድገትን እንዳመጡ እየሞገቱ፣ በሌላ በኩል ለራሳቸው የኢኮኖሚ ጥቅም የአፍሪካን የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት በዝብዘዋል። በበርሊኑ ጉባኤ ላይ፣ የአውሮፓ መሪዎች ያለነርሱ የአፍሪካ “ስልጣኔ” ሕልም እንደሆነ ተዘባብተው ነበር።
አውሮፓውያኑ ኃያላን በሦስት ወራት የበርሊኑ ዱለታ የአፍሪካን የዘመናት ቅርፅ አፈራርሰው አዲስ ካርታ ሳሉ። ከጉባኤው በኋላ አፍሪካ የራሷ መሆን እንዳትችል የሚያደርግ የቅኝ ግዛት ቀንበር ተዘጋጅቶላት ነበር። “ሆድ ሲያወቅ…”እንዲሉ አፍሪካን ካለችበት ኃላ ቀርነት፣ ከድህነት እና ከመሃይምነት አረንቋ የማውጣት፣ የሕዝቧን ሕይወት የመቀየር ኃላፊነት አለብን ተባብለው አፍሪካን በኃይል ወረሩ። ወረራቸውን ከ1883-1893 ዓ.ም ድረስ ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ አፍሪካ ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር ሙሉ ለሙሉ በአውሮፓውያን እጅ ወደቀች። የቅኝ አገዛዝ ዘመን ጀመረ። አፍሪካን በዝብዞና እና አቆርቁዞ የመክበር አጀንዳ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ተተገበረባት።
የቅኝ ግዛት አበሳ
አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ዘመን ምንም መልካም ትዝታ የላትም፤ ከብዝበዛ እና ከጭቆና ውጭ ምንም አላተረፈችም። ሕዝቧ በገዛ ሀገሩ ሁለተኛ ዜጋ፣ በገዛ መሬቱ ጭሰኛ፣ በገዛ ቀየው ባይተዋር፣ በገዛ ሐብቱ ለማኝ የሆነበት ነው። ጥቁርነት… የማይረባ፣ የማይለወጥ፣ ከሰው ዘሮች ሁሉ ያነሰ ተደርጎ የኮሰሰበት፣ የተሰደበበት፣ የተናቀበት፣ የተገለለበት ነው። ለአፍሪካዊ…ያ ዘመን ሁሌም ከአእምሮው የማይጠፋ መጥፎ ትዝታ ነው። የአፍሪካውያን ቱባ ባህል ተንቋሽሾ እና ተበርዟል፣ መሬታቸው ተነጥቋል። ስራ አጥ አውሮፓውያንን ወደ አፍሪካ እንዲፈልሱ በማበረታታት ልክ እንደ ነባር ገበሬዎች የሰፋፊ መሬት ባለቤት አድርጓቸዋል፤ አፍሪካውያን መሬታቸው መነጠቁ ሳይበቃ ርካሽ ጉልበት እንዲሰጡ ይገደዳሉ፣ በዚህም የአፍሪካውያን ሕይወት በአደገኛ ሁኔታ ተመሰቃቀለ።
በርግጥ በቅኝ ግዛት ወረራው መጀመሪያ አካባቢ አፍሪካውያን ነፍጥ አንግበው የተፋለሙ እና አስገዳጅ የጉልበት ሥራን የተቃወሙ ቢሆንም፣ ትግሉ አካባቢያዊ እና የድንገቴ ስለነበር በአሰቃቂ ሁኔታ በወራሪዎቹ የበላይነት ተቀልብሰዋል። አንድ ቦታ ላይ ግን ቅኝ ግዛትን አንገት ያስደፋ አንፀባራቂ የጥቁሮች ድል ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከአድዋ ተራሮች ስር የተፈፀመ አፍሪካዊ ገድል። የማታ ማታ ይህ ድል ለመላው ጭቁን አፍሪካውያን እና ለመላው ጥቁር አሜሪካውያን እና ኤዥያውያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የመውጣት ትልቅ የትግል ስንቅ መሆን ችሏል።
የቅኝ አገዛዝ ስርዓቱ እያደር የብዙሃኑን አፍሪካውያን መብት በመደፍጠጥ የሕዝቡን ምሬት ስለጨመረው አፍሪካውያንን ለነፃነታቸው ቆርጠው እንዲነሱ አስገድዷቸዋል። በመሆኑም በአፍሪካ የብሔርተኝነት እና የነፃነት ትግል መቀጣጠል ያዘ። በሁሉም አካባቢዎች አፍሪካውያን የየራሳቸውን የትግል አቅጣጫ ቀይሰው ቅኝ አገዛዝን ተፋለሙ። አፍሪካዊ ብሔርተኝነት እስከ ትጥቅ ትግል ወደ መረረ ደረጃ በመሸጋገር የቅኝ አገዛዝን ስርዓት በማፍረክረክ ወደ ነፃነት ጎዳና ግስጋሴውን አጠናክሯል። በተለይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ ሁለት አሥርት ዓመት ውስጥ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ተቀዳጅተዋል።
አፍሪካዊ ብሔርተኝነት
በገዛ ሀገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የቆጠረውን እና ያዋረደውን የቅኝ ግዛት ስርዓት አፍሪካዊው ትውልድ በተደራጀ መልኩ መታገል አስፈላጊ መሆኑን የተረዳበት ጊዜ መጥቷል። በተለይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አዲስ እይታን እና አመለካከትን ወልዷል። አፍሪካዊ ማንነቱ መጉደሉ የሚቆጨው ትውልድ መነሳት እየጀመረ መጣ። በእርሱ መሬት ሌሎች ሲከብሩ እርሱ በድህነት እየደቀቀ የመቀጠሉን እዳ ቁጭ ብሎ ማየት፣ ለአፍታ መታገስ የማይችል በቃ የሚል ቁጡ ትውልድ ከየአቅጣጫው ተጠራርቶ በአዲስ የአፍሪካዊ የብሔርተኝነት ትግል መሰባሰብ ያዙ። አፍሪካን ከጨቋኙ የባእዳን አገዛዝ የሚያላቅቅ አፍሪካዊ ትግል፣ አፍሪካዊ ድርጅት እና አፍሪካዊ ታጋይ አታጋይ የሚያሻት አፍሪካ ለራሷ ችግር ለራሷ ማበር ነበረባት።
ታዲያ በቅኝ ግዛቱ ዘመን በአውሮፓ እና በአፍሪካ የመማር እድል የነበራቸው አፍሪካውያን አንዳንድ ምሁራን መነሳት ጀመሩ። አዳዲስ አስተሳሰቦች አዳዲስ ምልከታዎችን የያዙ ጠያቂ አእምሮዎች ነፃነትን መጠየቅ የጀመሩበት ወቅት ብቅ አለ።
“አፍሪካን ለአፍሪካ” ከሚለው፣ ቅኝ ግዛትን ከአድዋ ተራሮች ስር ካዋረደው ብቸኛው አፍሪካዊ ድል ላይ ተንተርሶ በእነ ማርከስ ጋርቬይ ከባህር ማዶ ትውልድ ተቆጥሮ ብቅ ሲል፣ እውቁ ጥቁር አሜሪካዊ ፀሀፊና ፖለቲከኛ ዲቦይዝ ፓን አፍሪካኒዝምን ማራመድ ሲጀምር፣ ተከትሎም ለጭቁን ሕዝቦች ነፃነት፣ ተስፋ፣ እኩልነትን፣ አብዮትን የሚሰብከው የሶሺያሊዝም ኮሙኒዝም ፍልስፍናዎች መስረጽ እና መስፋፋት እንዲሁም ሌሎችም ክስተቶች ለአፍሪካ የብሔርተኝነት ትግል መሰረት ከጣሉ ዐበይት ክስተቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በወቅቱም ከአፍሪካ የመማር እድል አግኝተው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ለተማሩ ወጣት አፍሪካውያን ምሁራን አፍሪካዊ ብሔርተኝነቱ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል።
የጋናው ክዋሜ ንክሩማህ በአሜሪካ ለትምህርት በቆየበት እና ባስተማረበት ወቅት የአፍሪካን የነፃነት ትግል ጉዞ ካስጀመሩት ዲያስፖራ አፍሪካውያን መካከል አንዱ ነው። በአሜሪካ ከትምህርቱ በተጓዳኝ በተለያዩ መድረኮች በመገኘት በፖለቲካው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ከአሜሪካም ወደ ለንደን ለሦስተኛ ድግሪ ትምህርቱ በተዛወረበት አጋጣሚ ጸረ ቅኝ ግዛት እና የጥቁር ብሔርተኝነትን አስተባብሯል፡፡ አሜሪካ ውስጥ በሚታተሙ ጋዜጦችም አፍሪካን አስመልክቶ አወዛጋቢ ጽሑፎችን ያዘጋጅ ነበር፡፡ ክዋሜ ንክሩማህ የመላው አፍሪካ አንድነት መንግሥት የመመስረት ርዕዩን ዕውን ለማድረግ ቅስቀሳ የጀመረውም በዚሁ ወቅት ነው፡፡
በተለይ በ1945 ዓ.ም ላይ በማንችስተር እንግሊዝ የተካሄደውን 5ኛውን የፓን አፍሪካን ጉባኤ በማደራጀት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ቀደም ሲል ሲካሄዱ የነበሩ የመላው አፍሪካ ጉባኤዎች በዘር እኩልነት ጥያቄዎች ላይ ብቻ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ ይህ 5ኛው ጉባኤ ግን ከዘር እኩልነት ከፍ ያለ፣ የአፍሪካን ነፃነት አጥብቆ የሚጠይቅ አጀንዳ ያነገበ ነበር፡፡ ወሳኙ አምስተኛው የፓን አፍሪካኒዝም ጉባኤም የተጠናቀቀው፦
‘’ነፃ መውጣት ቆርጠናል። ትምህርት እንፈልጋለን። የተሻለ ሕይወት የመኖር መብት ማግኘት፣ ሀሳባችንን እና ስሜታችንን የመግለፅ መብት፣ የእኛነታችንን መብት የማሳደግ እና የመፍጠር መብት እንፈልጋለን። የጥቁር አፍሪካ ራስ ገዝነትን እና ነፃነትን እንፈልጋለን። ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲ እና ለተሻለ ማህበራዊ ሕይወት በምንችለው በማንኛውም አይነት መንገድ እንታገላለን።’’
በሚል በቅኝ ግዛት ላይ በተስተጋቡ ጠንከር ያሉ ቃላት በያዘ የአቋም መግለጫ ነበር።
ጉባኤውን ዲ ቦይዝ ቢያዘጋጀውም ንክሩማህ በጉባኤው ባቀረባቸው የተለያዩ ጽሁፎቹ ከአፍሪካ እና ከዓለማችን የተለያዩ ማእዘናት መጥተው በጉባኤው ለታደሙት ወጣት አብዮተኞች በማነሳሳት እና ተፅእኖ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶ ነበር። ከዚህ ጉባኤ በኋላ ንክሩማህ ለአፍሪካ ነፃነት ሙሉ ጊዜውን በማዋል መታገል እና ማታገል ጀምሯል። የአፍሪካ ሶሺያሊስት ሪፐብሊክ ውህደትን በመፍጠር አፍሪካን በማዋሀድ የምዕራባውያንን ተጽዕኖ መግታት እንደሚቻልም አስረድቷል፡፡
ይህ የብሔርተኝነት መንፈስ በመላው አፍሪካ አህጉር ውስጥ እና ውጭ ሌሎች ታጋዮችን ማስነሳት ችሏል። ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ በውጭ ሀገራት የቆየው የኬንያው ጀሞ ኬንያታ የአፍሪካን አብዮት በኮሙኒዝም ፍልስፍና አስተሳብ አስተሳስሮ ለመታገል በገባው ቃል መሰረት ትግል በኬንያ አስጀምሯል።
የአፍሪካውያኑን ሀብት፣ ጉልበት ፣ ማንነት የሚበዘብዘውን ቅኝ ግዛት ለማስቆም የጋራ አላማ ያነገቡ በርካታ አፍሪካውያን ብሔርተኞች ትግሎቻቸውን በተለያየ መንገድ አጧጥፈው ቀጠሉ። አብዛኞቹ የትጥቅ ትግልን ተከትለዋል። ለአብነትም አልጀሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ጊኒ ቢሳው፣ እና በተወሰነ ደረጃ ኬንያ፣ ናሚቢያ፣ ዛየር እና ዚምባቡዌን እጅግ ከባድ የነፃነት ትግል አድርገዋል። በአንፃሩ ደግሞ ኮት ዲቮር፣ ቦርኪናፋሶ፣ ታንዛኒያ የመሳሰሉት የካሄዱት የትጥቅ ትግል መጠነኛ የሚባል ነበር።
…..ይቀጥላል
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም