ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ የተንጣለለውን አትላንቲክ ውቂያኖስን እየቀዘፍን ወደ ካሪቢያን ክልል ለአፍታ እናቅና፤ የ23 ትንንሽ ደሴቶች ስብስብ ውጤት ወደ ሆነችው አንድ ሉዓላዊት ሀገር። የምናብ መርከባችንን እንቅዘፍ፤ የደስታ መፍለቂያ ከካሪቢያን ሁለተኛዋ ሀብታም ሀገር ናት ይሏታል። በካሪቢያን ካሉት ሀገራት በሕዝብ ብዛቷ 6ኛ ነች። 5 ሺህ 128 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አላት። የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ምድር፣ ትሪንዳድ እና ቶቤጎ ላይ መልህቃችንን እንሰር።
ትሪንዳድ እና ቶቤጎ የተባሉ ሁለት እህትማማች ደሴቶች አንድ ሉዓላዊት ሀገርን –ትሪንዳድ እና ቶቤጎ ሪፐብሊክን ፈጥረዋል። ምንም እንኳን የ21 ትናንሽ ደሴቶች ስብስብ ብትሆንም ሀገሪቱ ስያሜዋ ከሁለቱ ትልልቅ ደሴቶች መሀል የተወሰደ ነው። ትሪንዳድ ትልቋ ደሴት ስትሆን አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ ይኖርባታል፤ ቶቤጎ ትንሽ ደሴት ናት። የሀገሪቱን መሬት ስድስት በመቶውን ትሸፍናለች። አራት በመቶው ሕዝብ የሚኖርባት ደሴት ናት። በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ከደቡብ አሜሪካዊቷ ቬንዝዌላ እና ከግሪናዳ በስተደቡብ ትገኛለች። በሰሜን ምሥራቅ ከባርባዶስ እና በደቡብ ምሥራቅ ከጉዌና ጋር የባህር ድንበር ትዋሰናለች።
ፖርት ኦፍ ስፔን ዋና መናገሻ ከተማዋ ትሪንዳድ ውስጥ ትገኛለች። የዓለም ምርጡ ካካዋ የሚበቅልበት፣ ልብን የሚሰውር በዓለም ተለባላቢው በርበሬ የሚመረትባት፣ የባህል መናኸሪያ፣ የአብሮነት፣ የብርታት መገለጫ ምድር ናት።
ትሪንዳድ እና ቶቤጎ የካሪቢያን ካርኒቫል መገኛው ናት። ይህ ብቻ አይደለም፤ የካርኒቫሉ ድምቀት የሆነው የካሊፕሶ ሙዚቃ መገኛ ቤቱም ናት። አልፎም በ1920ዎቹ ከፖርት ኦፍ ስፔን ለተገኘው የሳህን ድራም (steelpan) የትውልድ ሀገሩ ናት።
ክርስቶፈር ኮሎምበስ በ1490 ዓ.ም ትሪንዳድን ከረገጠበት ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ በስፔን ቅኝ ገዥ ሰፋሪዎች መወረሯን ታሪክ ያስታውሳል። አእዋክ እና ካሪብ ሕንዳውያን የደሴቷ ቀዳሚ ኗሪዎች የነበሩ ቀደምት ተወላጆች ቢሆኑም በከፍተኛ ሁኔታ በስፔን ቅኝ ገዥዎች ተገፍተዋል። የተረፉት ቀስ በቀስ ከሌሎች ጋር ተዋህደዋል። ቶቤጎ ደግሞ የተለየ ታሪክ ያሳለፈች ሌላዋ ደሴት ናት። በቅኝ ግዛቱ ወቅት ፈረንሳይ፣ ደች እና እንግሊዝ ቶቤጎን ለመቆጣጠር ተፋልመዋል። ለሀያ ሁለት ጊዜ ያህል የተለያዩ እጆች ተፈራርቀውባታል።
ከሰባት ሺህ ዓመታት በፊት ከደቡብ አሜሪካ መነሻቸውን ባደረጉ አራዋካን በተባሉ ሰዎች እና ካሪባን ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች በደሴቶቹ ላይ መስፈራቸው ይነገራል። አሁን ያለው ሕዝብ የአፍሪካ፣ የሕንድ ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓ እና የቻይና ቅልቅል ነው። በደሴቷ የሰፈሩት በባርነት የመጡ እና በጉልበት ሰራተኝነት ወደ ስፍራው የመጡ ናቸው። ይህ አይነቱ የአሰፋፈር ሁኔታ በካሪቢያን ታሪክ ውስጥ የተለመደ ነው። ይህ የሕዝብ ስብጥር በብሔራዊ ባህሏ ላይ ከፍተኛ የዘር ቅልቅል ያላቸው ሰዎች እንዲኖሩ አሻራውን ትቷል።
ትሪንዳድ እና ቶቤጎ በ1954 ዓ.ም ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተዋል። በ1968 ዓ.ም ደግሞ ሪፐብሊክ ሆነዋል።
የባህል መናኸሪያ የሚሏትም ከዓለም የተለያዩ አቅጣጫዎች የመጡ ባህል እና ማንነቶች አብረው የተዋሃዱባት በመሆኗ ነው። የሀገሪቱ ባህል የአፍሪካውያን፣ የሕንዳውያን፣ የፈረንሳይ፣ አሜርኢንዲያኖች፣ የቻይና፣ የእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ቬንዝዌላ፣ ካሪቢያን እና የአሜሪካ ተፅእኖ የሚንፀባረቅበት ነው።
ትሪንዳድ እና ቶቤጎ ጎራ ከተባለ መታየት የሚገባቸው ብዙ ውብ ነገሮች አሉ። ዋና ዋና የሚባሉትን ብቻ ለእናንተ እንካችሁ ስንል የካሪቢያን ድምቀት በሆነው እውቁ የመንገድ ላይ ካርኒቫል እንጀምር። ብሔራዊ መነቃቃትን እና ደስታን የሚያላብሰው ይህ ትዕይንት ታሪካዊ መሰረት ያለው እና የካሪቢያንን ቀለማማ ባህል በማሳየት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ይጀምራል። ዋናው ካርኒቫል ሰኞ እና ሀሙስ በትሪንዳድ ትላልቅ ከተሞች ይካሄዳል። በጭቃ መቀባባት፣ ቀለማማ ፓውደር የመርጨት፣ ፊት የመቀባት ፓርቲ ሰኞ ይጀምራል። የሁለት ቀናት የጎዳና ትርኢቱ በካሊፕሶ ጭፈራ ይደምቃል።
ማራኪ የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች ሁለቱንም ደሴቶች ለመዝናናት ተመራጭ ያደርጋቸዋል። የተራራ ሰንሰለቶች ማራኪ ዕይታን ይፈጥራሉ። በርካታ ወንዞች እና ምንጮች በትሪንዳድ ደሴት ውስጥ ይገኛሉ። ትልቅ የሚባለው ወደ አትላንቲክ የሚፈሰው ኦርቶሪዮ ወንዝ ተጠቃሽ ነው። ትንሹ ቶቤጎ ደሴት ከዋናው ቶቤጎ በቅርብ ርቀት ያለ ሲሆን ቶቤጎ ካሏት በርካታ ትንንሽ ደሴቶች ትልቁ ነው። ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሞላ ነው።
ማራከስ የባህር ዳርቻ ትሪንዳድ ያላት ምርጡ እና ታዋቂው የመዝናኛ ስፍራ ነው። ከባህሩ ዳር ሆኖ የሚፈጥረው እይታ፣ ፀአዳ አሸዋው በአረንጓዴ የተሸፈኑ ተራሮች ተዳምረው በእጅጉ ቀንዎን ያስውቡልዎታል። በአጭሩ የካሪቢያኗ ውብ ሀገር የደሴቶች ስብስብ ትሪንዳድ እና ቶቤጎ የብዙ ባህሎች ቅይጥ ማህበረሰብ በፍቅር በህብር የሚኖሩባት ድንቅ ምድር፤ ተነግሮ በማያልቅ ውበት የተሞላች የደስታ የፌሽታ ሀገርን እንዲህ በአጭሩ አስጎበኘናችሁ።
ምንጭ፦ ፕላኔትዌር፣ ብሪታኒካ፣ ቲኤንቲኤርፖርት፣ ናሽናል ጆግራፊክ
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም