ከ18 ዓመታት በፊት በእንግሊዝ ማንቸስተር ሲቲ የሚባል ክለብ ቢኖርም በፕሪሚየር ሊጉ ግን ያን ያህል ተጽዕኖው የጎላ አልነበረም። የማንቸስተር ከተማ ክለብም ደማቅ ቀይ እንደነበር አይዘነጋም። እ.አ.አ በ2008 የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ከገባ በኋላ በክለቡ አዲስ የእግር ኳስ ለውጥ፣ አዲስ አቢዮት ተፈጥሯል። ባለፉት 16 ዓመታት ቢሊየነሩ ሼክ መንሱር ቤን ዛይድ ረብጣ ቢሊዮን ፓውንድ ገንዘብ በማፍሰስ ከአውሮፓ ኃያላን ክለቦች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል።
ለወትሮ የበይ ተመልካች የነበረው ክለብ የፕሪሚየር ሊግ፣ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ እና ሌሎችም የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በተለይ ደግሞ ስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በ2016 እ.አ.አ ኢትሀድ ከደረሰ በኋላ የማንቸስተር ከተማ ቀለም ከቀይ ወደ ውኃ ሰማያዊ ቀለም ተለውጧል። ጓርዲዮላ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የኢትሀድ ቆይታው ስድስት የፕሪሚየር ሊግ፣ አንድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ አንድ የፊፋ ክለቦች፣ ሁለት የኤፍ ኤ ፣አራት የካራባዎ እና ሁለት የኮሚዩኒቲ ሽልድ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በፕሪሚየር ሊጉ በተከታታይ አራት ዋንጫዎችን ያሳካ የመጀመሪያው ክለብም መሆን ችሏል- ማንቸስተር ሲቲ። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም አስፈሪ የነበረው ክለብ ዘንድሮ ግን ሞገሱ ተገፎ አስቸጋሪ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። ከማራኪ አጨዋወት ጋር የአውሮፓ ክለቦች ቁንጮ የነበሩት ውኃ ሰማያዊ ለባሾች በትናንሽ ክለቦች ሳይቀር ተደቁሰዋል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በሁሉም ውድድሮች በተከታታይ ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። ከተከታታይ አስከፊ ውጤት በኋላ በ14ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ኖቲንግህም ፎረስትን ሦስት ለባዶ አሸንፏል::
አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እና ማንቸስተር ሲቲ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን ባለማሸነፋቸው አዲስ ክብረ ወሰንም መስበራቸው አይዘነጋም። በሰባት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 19 ግቦችም ተቆጥሮባቸዋል። በ13ኛ ሳምንት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ወደ አንፊልድ ሮድ አቅንቶ ከሊጉ መሪው ሊቨርፑል ጋር ያደረገውን መርሀ ግብር ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሁለት ለባዶ መሸነፉ የሚታወስ ነው። ውኃ ሰማያዊ ለባሾች በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ በበርንማውዝ፣ በብራይተን እና ቶተንሀም ሆትስፐርስ ጭምር መሸነፉ ይታወሳል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ በስፖርቲንግ ሌዝበን ተሸንፏል፤ ከፌይኖርድ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ደግሞ እስከ 75 ኛው ደቂቃ ሦስት ለባዶ ቢመራም በ15 ደቂቃ ሦስት ግቦች ተቆጥሮበት ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል። ዘንድሮ በየጨዋታው ያልተጠበቀ አስከፊ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኝው የማንቸስተሩ ከተማ ክለብ ከሊቨርፑል ጋር ከነበረው መርሀ ግብር በኋላ ብዙዎች የማንቸስተር ሲቲ ዘመን እያበቃ መሆኑን እየተናገሩ ነው።
በኢትሀድ የፔፕ ጓርዱዮላ ፀሐይ እየጠለቀች ስለመሆኗ ኤስፒኤን የተባለው የስፔን ጋዜጣ አስነብቧል። ጋዜጣው አብነት አድርጎ ያነሳውን የአንፊልዱን ጨዋታ የጓርዲዮላው ቡድን ዘጠና ደቂቃ በቀዮች መቀጥቀጡን ያትታል። ለወትሮ የማይደፈረው የኋላ ክፍል ሳስቶ ሁለተኛው የሜዳ ክፍል ተጫዋቾች የግብ እድሎችን የመፍጠር እና የፊት መስመሩ የማጥቃት አቅም አንሶት ታይቷል። ኳስን በመቆጣጠር እና ተጭኖ በመጫዎት የሚታወቀው የማንቸስተሩ ከተማ ክለብ ኳሱን ለሊቨርፑል ኮከቦች አስረክቦ 90 ደቂቃ ሲቅበዘበዝ ማሳለፉን ኤስፒኤን ያስታውሳል። ከዚህ ጨዎታ ቀደም ብሎ በነበረው 12ኛ ሳምንት መረሀ ግብርም ቶተህናም በሜዳው አስተናግዶ አራት ለባዶ የተሸነፈበት ጨዋታም ብዙዎችን ያስገረመ ነበር።
ከዚህ አስከፊ ሽንፈት ሳያገግም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውጤቱን አስጠብቆ ከሜዳ መውጣት ባለመቻሉ ከፌይኖርድ ጋር አቻ ተለያይቷል። የወቅቱ የፕላኔታችን ምርጡ አሰልጣኝ እስከ 75ኛው ደቂቃ ሦስት ለባዶ እየመራ በመጨረሻ ነጥብ ተጋቶ ሲወጣ በአሰልጣኝነት ህይወቱ የመጀመሪያው ነው። ማንቸስተር ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ እስከ ታላቁ የአውርፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ እያስመዘገበ ያለው ደካማ ውጤት የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆን? ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ።
በፕሪሚየር ሊጉ ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነትም ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የ14ኛ ሳምንት ጨዋታን ጨምሮ ልዩነቱ ዘጠኝ ደርሷል። በዚህ ደረጃ ማንቸስተር ሲቲ የውጤት ቀውስ ከገጠመው 18 ዓመታትን አስቆጥሯል። በርካታ ጋዜጦች የክለቡን ወቅታዊ ችግር መንስኤ ምንድነው? ለሚለው ብዙ መላምቶችን አስቀምጠዋል። ዘ አትሌቲክ እንዳስነበበው የማንቸስተር ሲቲ ቀውስ የጀመረው የሮድሪን መጎዳት ተከትሎ ነው።
የሮድሪ በቦታው አለመኖር ማንቸስተር ሲቲን ይበልጥ የኋላ ክፍሉ እንዲጋለጥ እና በርካታ ግቦች እንዲቆጠሩ አድርጓል። ቡድኑ ሚዛኑን በመሳት በተጋጣሚ የበላይነት እንዲወሰድበትም በር ከፍቷል። ባሳለፍነው ዓመት ማንቸስተር ሲቲ የተሸነፈባቸውን ብዙዎች ጨዋታዎች ያለ ሮድሪ ያድረጋቸውን እንደነበር የሚታወስ ነው። ዘ አትሌቲክ ቁጥራዊ መረጃዎችን ጠቅሶ እንዳስነበበው ሮድሪ ካልተሰለፈ ውኃ ሰማያዊ ለባሾች የማሽነፍ ምጣኔያቸው 57 ነጥብ አንድ በመቶ ነው። ሮድሪ ከተሰለፈ ደግሞ 75 ነጥብ በመቶ የማሽነፍ ዕድል እንዳላቸው መረጃው ያሳያል።
ታዲያ የቡድኑ የልብ ምት የሆነው የባሎንዶሩ አሸናፊ መጎዳት ክለቡ በውጤት ማጣት እንዲንገዳገድ አድርጎታል። የ34 ዓመቱ እንግሊዛዊው የቀኝ ተመላላሽ ካይል ዎከር እና የ33 ዓመቱ የጨዋታ አቀጣጣይ ኬቨን ዲብሮይነ ባለፉት ዓመታት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች እንደነበሩ አያጠያይቅም። የእግር ኳስ የእድሜ ማምሻ ላይ የሚገኙት እነዚህ ኮከቦች አሁን ላይ ከጉዳት እና ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ አቋማቸው እየወረደ ይገኛል።
ሁለቱ ተጫዋቾች በኢትሀድ ያላቸው ተጽዕኖም እየቀነሰ መጥቷል። ጓርዲዮላ የእነዚህን ትክክለኛ ተተኪ አለማግኝቱ የቡድኑ ጥንካሬ እንዲቀንስ ሌላኛው ምክንያት ተደረጎ ተነስቷል። ሌላው ማንቸስተር ሲቲ ወጣት ኮከቦችን በቋሚ ዝውውር እና በውስተ ውል ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ መስጠቱ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች በወጣቶች ለመተካት የሚያደርገውን ሽግግር እንዳዘገየው ተዘግቧል። ኮል ፓልመርን ለቸልሲ፣ ጁሊያን አልቫሬዝን ለአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቴይለር ሀርውድ ቤሊሰንን ለሳውዝአምፕተን፣ ሌያም ዴላፕን ለአይፕስዊች ታውን ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር ወቅት አሳልፎ መስጠቱ የሚታወስ ነው።
ከኢትሀድ ለቀው በወጡ ኮከቦች ምትክም ብራዚላዊውን ሳቪኖን፣ ማቲያስ ኑኔስን እና ኤካይ ጉንዶጋን ናቸው ኤትሀድ የደረሱት። ከ18 ወራት በኋላ ድጋሚ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ቤት የተመለሰው ኤካይ ጉንዶጋን እንደበፊቱ ተጽዕኖ መፍጠር አልቻለም። ከወልቨር አምፕተን 50 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበት ውኃ ሳማያዊ ለባሾች ቤት የደረሰው ማቲያስ ኑኔስም የተጠበቀውን ያህል መሆን አልቻለም። የሁለቱ ጥምረት ሜዳ ላይ ክለቡን ወደ ፊት አንድ እርምጃ እንዲራመድ ባለማድረጉ የውጤት ቀውስ ተፈጥሯል።
ጓርዲዮላ በተደጋጋሚ የጉንዶጋን እና የኮቫቺችን በማጣመር እየተጠቀመ ቢሆንም ሁለቱም የሮድሪን ያህል ተጽዕኖ መፍጠር ለቻሉም። ከእነዚህ በተጨማሪ የናታን አኬ፣ እና የኢማኑኤል አካንጂ ጥሩ አቋም ላይ አለመገኝት ቡድኑን ውጤት አሳጥቶታል።ሌላው ማንቸስተር ሲቲ ምንም እንኳ በመጨረሻ አሸናፊ ቢሆንም በእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር 115 ክሶች ቀርቦበት እንደነበር አይዘነጋም።
ፍትሐዊ የገንዘብ አጠቃቀም ደንብን ጥሷል በሚል የተከሰሰው ማንቸስተር ሲቲ በዝውውር ገበያው በፈለገው ልክ እንዳይሳተፍ ታግዶ ቆይቷል:: ውጤት የራቀውን ማንቸስተር ሲቲን ለመታደግ የመፍትሄ ሀሳብ ያቀረበው ኤስፒኤን የመሀል ተከላካዩን አካንጂን የሮድሪን ሚና ሰጥቶ በማጫወት ጓርዲዮላ የሚፈልገውን የኳስ ቁጥጥር እና ተጋጣሚን ትንፋሽ የማሳጣት ቁልፉን ድጋሚ ማግኘት የችላል ነው የሚለው መረጃው::
ማንቸስተር ሲቲ በተለይ ከቶተንሀም እና ከሊቨርፑል ጋረ በነበረው ጨዋታ ለወትሮ የነበራቸው የመከላከል አቅም እና በመልሶ ማጥቃት በተጋጣሚ ላይ አደጋ የመፍጠር ብቃት በእጅጉ ተዳክሞ ታይቷል:: ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በእነዚህ ጨዋታዎች ከተጠሟቀቸው 14 ጨዋታዎች ዘጠኙ ከ29 ዓመት እደሜ በላይ የሆኑ ናቸው:: እናም ቡድኑ ሮጠው በማይደክሙ ወጣቶች መተካት እንደሚኖርበት መረጃው ይጠቁማል::
ቡድኑ ወደ ቀድሞው ጥንካሬው እና ቅረጽ እንዲመለስ አጥቂው እርሊንግ ብራውት ሀላንድን ማሳርፍ እንደሚገባም መረጃው ያትታል:: ምንም እንኳ ሀላንድ የተዋጣለት ግብ አምራች ቢሆንም አጨዋውቱ ለቡድኑ ምቾት የሚሰጥ አይደልም:: ምክንቱም ሀላንድ በየጨዋታው ከኳስ ጋር ያለው ንክኪ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው::
አጥቂው በአንድ ጨዋታ በአማካይ 19 ብቻ ንክኪ እንደሚያደረግ ቁጥሮች ይናገራሉ:: ታዲያ እንደ መፍትሄ ተደረጎ በኤስፒኤን የተቀመጠው በሀላንድ ቦታ ፊል ፎደን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ቢጫወት ማንቸስተር ሲቲ ወደ ቀድሞው ጥንካሬው እና አጨዋወቱ ሊመለስ ይችላል ነው የተባለው:: ያም ሆነ ይህ ግን ሀዲዱን ለሳተው ቡድን ቶሎ መፍትሔ ካልተበጀለት ችግሩ ሊጸና እንደሚችል የእግረ ኳስ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው:: ችግሩ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ አሰልጣኙ ራሱን ከኃላፊነት እንደሚያነሳ ተናግሯል:: ማንቸስተር ሲቲ በሊቨርፑል ሁለት ለባዶ ከተሸነፈ በኋላ የሊቨርፑል ደጋፊዎች “ትባረራልህ!” የሚል ጭሆት በአንፊልድ አሰምተዋል::
ይሄንን ድምጽ የሰማው ሰፔናዊው አሰልጣኝ እ.አ.አ በ2018 አሰልጣጣኝ ሆዜ ሞሪህኖ በኦልተራፎርድ ለገጠማቸው ተመሳሳይ ቸግር በቸልሲ ቤት ያሳኩትን ዋንጫዋች በጣቶቻቸው ምልክት ያሳዩበትን አጋጣሚ ደግሞታል:: ጓርዲዮላ በስድስት ጣቶቹን በማንሳት ስድስት የፐሪሚየር ሊግ ዋንጫዋችን ማሳካቱን ለሊቨረፑል ደጋፊዎች አስታውሷል:: ማንቸስተር ሲቲ ከገባበት የውጤት ቀውስ አገግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ታምር ይሠራ ይሆን ወይስ ችግሩ ቀጥሎ የጓርዲዮላ እና የሀብታሙ ክለብ ጋብቻ ያበቃል? አብረን የምናየው የሆናል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም