አካንማሹ ብሔራዊ ፓርክ

0
124

በጃፓን ከሆካይዶ ደሴት በስተምስራቅ፣ በሰሜን አብሺሪ በደቡብ ኩሺሮ ከተሞች መካከል ነው የሚገኘው – አካን ማሹ ብሔራዊ ፓርክ:: ሰፊው የፓርኩ ክልል ጫፋቸው የሾጠጠ ወይም የሾሉ ዛፎችን የለበሰ ነው::

ለፓርኩ መመስረት በቀጣናው በተከሰተ እሳተገሞራ የተፈጠሩት አካን፣ ኩሺሮ እና ማሹ የተሰኙ ውኃ የያዙ ኩሬዎች ተጠቃሾች ናቸው::

ከብሔራዊ ፓርኩ ዋና ዋና ተጠቃሽ እውነታዎች መካከል በአካን ሀይቅ ድቡልቡል ቅርፅ ያለው አልጌ የተሞላ መሆኑ፣ ኩሺሮ በጃፓን ትልቁን በእሳተ ገሞራ የተፈጠረ ሐይቅ መያዙ፣ የማሹ ሐይቅ ደግሞ በዓለም  ጥርት ብሎ የሚታይ ውኃ መሆኑ ጥቂቶቹ ናቸው::

በእሳተገሞራ በተፈጠሩ ተራራዎች ቀጣና በእግር በመዘዋወር ሐይቆቹን  መጐብኘት መቻሉ  ተመራጭ አድርጐታል:: በተጨማሪም ከፓርኩ መግቢያ በስተምእራብ የምትገኘው ትንሿ ኦንኔቶ ሀይቅ እንደ ዓየር ሁኔታው የሚለያይ ቀለማትን በማንፀባረቅ ትታወቃለች::

በአካን ኃይቅ ላይ በጀልባ የሚደረግ ጉዞም የጐብኚዎችን ቀልብ የሚስብ የፓርኩ ተጠቃሽ መስህብ ነው::

የኩሺሮ ሐይቅ

በአካን ማሹ ብሔራዊ ፓርክ እሳተገሞራ በፈጠረው አዘቅት የተፈጠረ ሀይቅ ሲሆን በክረምት በሚፈጠረው ቅዝቃዜ ወደ ግግር በረዶነት ይቀይረዋል:: በፓርኩ ቀጣና በርካታ ፍል ውኃዎች ይንፎለፎላሉ:: ከውስጣቸው እንፋሎት ሲትጐለጐል መመልከትም ለጐብኚዎች ሀሴትን ያጐናፅፋል::

በፓርኩ ክልል በሚገኙ ሀይቆች አልጌ ንጣፍ በቅሎባቸዋል:: በቀጣናው የሚገኙ ተራሮች እና ከፍታ ቦታዎች  በሌሎች ቦታዎች ተዘውትሮ የማይታይ በአበባ የተንቆጠቆጡ አጫጭር ቁጥቋጦን ለብሰዋል::

የዱር እንስሳት

በአካን ማሹ ብሔራዊ ፓርክ ቀይ ቀበሮ በብዛት የሚገኝ ሲሆን በሆካይዶ ያሉት በሌሎች ቀጣናዎች ከሚገኙት አካላቸው ከፍ ያለ ወይም ትልልቅ ናቸው::

በአካን ማሹ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘው ደን ለጃፓን አጋዘን ምቹ መኖሪያ ሆኖም ያገለግላል:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ጃፓን ትራቭል፣ ኢኤንቪ እና ትሪኘ አድቫይዘር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here