ሙስና እና ብልሹ አሠራሮች የሚያደርሱትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማስቀረት መታገል ይገባል ተባለ፤ ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን በየዓመቱ ኅዳር 30 ይከበራል፡፡
በዓሉን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ሙስና የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ውደመት በመረዳት በተለይ ወጣቱ ትውልድ ሊታገለው እንደሚገባ አሳስበዋል፤ “ሙስና እና ብልሹ አሠራሮች በሀገራችን ብሎም በክልላችን ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ኢኮኖሚዊ፣ ማሕበራዊ እና ፓለቲካዊ ቀውሶች ለመከላከል፣ የምዝበራ እና የዘረፋ ችግሮችን ለማስቆም ከወጣቱ ትውልድ ጋር በአንድነት ለመታገል በማሰብ ቃላችንን የምናድስበት በዓል ነው” ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን እና በክልላችን ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል፤ የነገን ሰብዕና ይገነባል!” በሚል መሪ መልክት ተከብሮ ውሏል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ወጣቱ ትውልድ እራሱን በሥነ ምግባር ገንብቶ ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን ከሕዝቡ ጋር ሆኖ በትኩረት ሊታገል ይገባል።
ባለፉት ጊዚያት በክልሉ ውስጥ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ምክንያት በማድረግ በየአካባቢው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ፣ የብልሹ አሠራር እና የሙስና ችግሮች መታገል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፤ ለዚህም ሲቪክ ማሕበራት፣ የብዙኃን መገናኛ አካላት፣ የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የፀጥታ መዋቅሩ በጋራ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት እና ማስረጃ በመሆን የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ የጸረ ሙስና ቀን በዓልን ከማክበር ባለፈ በቁርጠኝነት ሙስናን መከላከል እንደሚገባ የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን አሳስቧል።
የጸረ ሙስና ቀንን በማስመልከት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ውይይት አካሂደዋል፤ በውይይቱ ጽሑፍ ያቀረቡት የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ የዝና ደስታ ለውጤታማ አሥተዳደር እንቅፋት ከሚኾኑ ጉዳዮች መካከል ሙስና እና ብልሹ አሠራር ግንባር ቀደሙ ነው ብለዋል።
የሕዝብ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከኢፍትሐዊ አሠራር እና ከብልሹ አሠራር መውጣት እንደሚገባ ያነሱት ምክትል ኃላፊዋ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ከሙስና የጸዳ አገልግሎት መሥጠት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሙስና እና ብልሹ አሠራር የመንግሥትን ታማኝነት እንደሚቀንስ በማንሳት የመንግሥት ሠራተኞች የአገልግሎት አሠጣጥን የተሻለ በማድረግ ሙስናን መታገል እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሙስና ለሰላም እጦት፣ ለሕግ መጣስ እና ለሌሎች ችግሮች ስለሚዳርግ ሥራን በሕግ እና በሥርዓት ብቻ መከወን እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ኃላፊዋ ማብራሪያ ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ ያቀጭጫል፤ በሀገር ደኅንነት ላይም አደጋ ያሳድራል። ሙስና እየተስፋፋ ሲሄድም በሥነ ምግባር ብልሹ የሆነ ትውልድ እንዲፈጠርም ያደርጋል።
በመሆኑም ሙስናን ለመታገል መንግሥት የህዝብ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ አስተማማኝ፣ ተገልጋዮችን የሚያረካ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይገባዋል በማለት ያሳሳቡ ሲሆን ተጠያቂነትን ማረጋገጥም አስፈላጊ እና ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም


