የበኲር ጉዞ

0
143

ዘመኑ 1985 ዓ.ም ነበር፣ ወቅቱ እንደ ሀገር ማስታወቂያ ሚኒስቴር በሚል በተቋቋመው መሥሪያ ቤት ሥር በክልሎች በቢሮ ደረጃ ሥራውን ይከውን የነበረበት ነው። በዚህ ጊዜ ታዲያ ክልላዊ ዜናዎች በእነዚህ ቢሮዎች እየተዘጋጁ በሀገራዊው ሬዲዮ ጣቢያ (የኢትዮጵያ ሬዲዮ) ለአድማጭ ይደርሱ ነበር።

በአማራ ክልል በኩል እንዲህ ክልላዊ መረጃዎችን ከአርሶ አደሩ ቀዬ ድረስ በመዝለቅ ለአድማጮች ያደርሱ ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጋዜጠኞች መካከል ጉምቱው ጋዜጠኛ ጌታቸው ፈንቴ አንዱ ነው። ጋዜጠኛዉ ትውስታውን እንዳጋራን በወቅቱ ሁሉም ነገር ያልዘመነበት በመሆኑ ከአርሶ አደሩ ቀዬ ለመዝለቅ ቀናትን የሚፈጅ የእግር ጉዞ በማድረግ ጭምር ዜናዎች ተሠርተው፣ ተቀናብረው ከዚያም ለብሔራዊዉ ሬዲዮ ጣቢያ (የኢትዮጵያ ሬዲዮ) ተልከው ለአድማጮች ይስተጋቡ ነበር። ሙያዊ ፍቅር እና ቁርጠኝነት ደግሞ ዋናው ስንቃቸው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በማስታወቂያ ቢሮ በኩል ይዘጋጁ የነበሩ ዜናዎች ከሁለት ዓመታት በኋላ (1987 ዓ.ም) በሌላ መልክ ተከሰቱ። ይህ ዓመት ታዲያ በኢትዮጵያ ክልሎች ታሪክ የመጀመሪያው የሕትመት የብዙኃን መገናኛ ወደ ሥራ የገባበት ነበር። ይህ ቀዳሚነት ደግሞ በኲር የሚለውን ስያሜ አስከትሏል።

ታህሣሥ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ክልላዊ እና ሀገራዊ መረጃዎችን ለአንባቢያን ማድረስን እንዲሁም አንባቢ ትውልድን ማፍራትን ዋና ዓላማዋ አድርጋ በተመሠረተችው በኲር ጋዜጣ መሠረቱ የተጣለው አሚኮ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ነገሩ ዘምኖ፣ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ 12 የስርጭት ቋንቋዎች ያሉት ከመሆኑም በላይ የሁለት የቴሌቪዥን እና ስድስት የኤፍ ኤም ጣቢያዎች እንዲሁም አንድ ክልላዊ ሬዲዮ ባለቤት ወደ መሆን በመሸጋገር ግዙፍ የሚዲያ ተቋም ሆኗል። በሀገራችን የብዙኃን መገናኛ ታሪክ አሚኮ ሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች (የሕትመት፣ ዲጂታል፣ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ እና ኤፍ ኤም ) ያሉት ብቸኛው ተቋም መሆኑንም ልብ ይሏል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሀገራችን በርካታ የሕትመት የብዙኃን መገናኛዎች ቢቋቋሙም ብዙ ሳይጓዙ ነው የከሰሙት። ለዚህ ደግሞ የ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ ዓመታት ተጠቃሽ  ናቸው። ከዚህ በተቃራኒው ታዲያ ምሥረታዋን በ1987 ዓ.ም ያደረገችው በኲር ጋዜጣ ለአንድም ጊዜ ሳትቆራረጥ ቀጥላ 30 ዓመትን አስቆጥራለች። ከዚህ ጋር በተያያዘ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ጋዜጣዋን አሳትሞ አንባቢያን ካሉበት ድረስ ማድረስ ባይቻልም የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዜናዎችን፣ ትንታኔዎችን ፣ መጣጥፎችን ፣ ልዩ ልዩ ማስታወቂያወችን እንዲሁም የጨረታና የእወጃ መልዕክቶችን ለተጠቃሚወችና ለአንባቢዎች በማድረስ ላይ ትገኛለች።

ከበኲር ጋዜጣ መሥራቾች አንዱ የሆነው እና በአሁኑ ወቅትም በጋዜጣዋ በከፍተኛ አዘጋጅነት በመሥራት ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ጌታቸው ፈንቴ እንዳለን ከአርሶ አደሩ ቀዬ ድረስ ዘልቆ በመግባት አዳዲስ የግብርና አሠራሮች እንዲለመዱ እና እንዲተገበሩ (ለአብነት የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር መጠቀም) የበኲር አበርክቶ ከፍተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የክልሉን የመስህብ ሀብቶች በማስተዋወቅ ለዘርፉ ዕድገት ባደረገችው አስተዋጽኦ በኲር ተመስጋኝ ናት።

“ይህ ብቻ አይደለም፣ ብልሹ አሠራርን በመዋጋት በኲር ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች። በብልሹ አሠራር የተዘፈቁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማጋለጥ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አድርጋለች” ነው ያለን ጋዜጠኛ ጌታቸው።

በኲር ጋዜጣ በተለያዩ አምዶች መረጃዎችን ከማቅረብ ባሻገር የሥራ ማስታወቂያዎች፣ ጨረታ፣ እወጃ እና መሰል ማሕበራዊ ጉዳዮችንም ለንባብ ታቀርባለች፤ በዚህም ሕዝቡ አገልግሎቶችን በቅርብ እንዲያገኝ በማድረግ ከወጪ እና ከጊዜ ብክነት እየታደገች ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡

ታህሣሥ 7 ቀን 1987 ዓ.ም በጥቂት ሠራተኞች በበኲር ጋዜጣ የተጀመረው የብዙኃን መገናኛ ተቋም እያደገ ሄዶ በአሁኑ ወቅት 859 ሠራተኞች ያሉትን ግዙፍ የሚዲያ ተቋም አሚኮን ለመመሥረት  ተችሏል፡፡ ከሰሞኑ ታዲያ አሚኮ የ30 ዓመት የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡ በወቅቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ ከበኲር ምሥረታ ጀምሮ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች በማንሳት በዚህ ሂደት ውስጥ በማለፍ ለአሁኑ ግዙፍ ተቋም መመሥረት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ የሠሩ መሥራቾች እና በሥራው ሂደት አሻራቸውን ያሳረፉ ባለሙያዎች “በፈተና ውስጥ ሆኖ ሥራን ማስቀጠል እና ማሳደግ እንደሚቻል አሳይተውናልና ክብር ይገባቸዋል” በማለት ነው ያመሰገኑት።

ይህን ታሳቢ በማድረግም “የአሁን ሠራተኞች ያለፉትን 30 ዓመታት ጉዞ እንደ ስንቅ በመውሰድ ወደ ፊት 30 ዓመት በመመልከት የበለጠ ግዙፍ ተቋምን መፍጠር፣ የአሁን ባላደራዎች ሆነን መሠረት የምንጥል ልንሆን ይገባል” ብለዋል።  ከዚህ በተጨማሪም በፈተና ውስጥ ጸንቶ ለውጤት መትጋትን፣ መሥራትን፣ ችግርን የመፍታት አቅምን ማሳደግ፣ ይዘትን ማሻሻል፣ ተመራጭ ሚዲየም ማድረግ እና ከሰው ልቦና ውስጥ በመግባት በጎ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ አሳስበዋል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here