የላቀ ጥረት ለተወዳዳሪነት እና ተመራጭነት!

0
155

በኩር ሳምንታዊ ጋዜጣ ሆና የተመሠረተችው የዛሬ 30 ዓመት ታህሣሥ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. ነበር፡፡ ያኔ ዜና ገጽን ጨምሮ ስድስት አምዶች ነበሯት፤ የገጿ ብዛት ስምንት፣ ቀለሟም ጥቁርና ነጭ ነበር፡፡

በኩር ስትመሠረት በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ የተሟላ የሥራ መሣሪያም ሆነ መሥሪያ ቦታ አልነበረም፡፡ ያኔ የነበሩት አሥር እንኳን የማይሞሉ ጋዜጠኞች በኩርን የማዘጋጀቱን ሥራ ያከናውኑ የነበረው እጅግ ኋላ ቀር፣ አድካሚ እና ለአደጋ አጋላጭ በሆነ መንገድ ነበር፡፡

ጽሑፎች በወቅቱ በነበረችው ብቸኛ ታይፕ ራይተር ከተጻፉ በኋላ በመቁረጫ (ከተር) እየተቆራረጡ ወረቀት (ዳሚ) ላይ በተሽከርካሪ ሙጫ እየተለጠፉ ነበር የዝግጅት ሥራው ይከናወን የነበረው፡፡ ወረቀቱ በመቁረጫዉ ሲቆረጥ ብዙ ጊዜ ጽሑፉ ይበላሽ፣ ከዚህም በላይ ጋዜጣዋን ለማድረስ በሚደረግ ሩጫ አዘጋጆቹ በምላጩ ይቆረጡ፣ በብዙ መከራ ያዘጋጁት ጋዜጣም ደም በደም ሆኖ ይወድቅ፣ የለበሱት ኮትም ሆነ ጃኬት በሙጫ እየተበላሸ ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት አጋጣሚም ይከሰት እንደነበር መሥራቾቿ  ያወሳሉ፡፡

በወቅቱ በኩርን የማዘጋጀቱ ሂደት እጅግ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም መሥራቾቿ  ችግርን ተቋቁመው በጽናት በመሥራታቸው በእድገት ጎዳና እየተራመደች ሠላሳኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን ለማክበር ችላለች፡፡ አምዶቿ ከስድስት ወደ ሀያ፣ ገጾቿም ባማካኝ ወደ አርባ  አድገዋል፡፡  ባለቀለም ጋዜጣም ሆናለች፡፡ ያ ሁሉ ፈተና ታልፎ ዛሬ በኩርን የማዘጋጀት ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በኮምፒዩተር ተጀምሮ በኮምፒዩተር ከሚጠናቀቅበት ደረጃ መድረስ ተችሏል፡፡

የጋዜጣ ህትመት ቁጥር አናሳ መሆን እንዲሁም የሥርጭት ተደራሽነቱ ተሽከርካሪ በሚገባባቸው አካባቢዎች ብቻ መወሰኑ በኵር በምስረታዋ ወቅት የተስተዋለ ውስንነት ቢሆንም አሁን ላይ በበይነ መረብ እንዲሁም በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በዓለም ላይ ተደራሽ ለመሆን ችላለች፡፡

በኩር በዚሀ የዕድገት ጎዳና እየተራመደች ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት እና ሥልጣኔ መፋጠን የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡ ከምሥረታዋ ጀምሮ ሙስናን፣ ብልሹ አሠራርን… እየተከታተለች በድፍረት በማጋለጥ የሰው እጅ ከማየት ይልቅ  ሁሉም በላቡ በወዙ ጥሮ ግሮ እንዲያድር፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ግልጽነት እንዲሁም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ስትሞግት ኖራለች፡፡

ምርትን እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ  የሚችሉ አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በአርሶ አደሩ ዘንድ ለማስረጽ ረድታለች፤ የክልሉን የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አስተዳደር እንከኖች እየነቀሰች በማስነበብ ችግሮች እንዲፈቱ፣ የክልሉ ሁሉን አቀፍ የእድገት እና የብልጽግና ርምጃ እንዲፋጠን ሁነኛ ሚና ተጫውታለች፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ባህል እንዲሆን፣ የንባብ ባህል፣ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ እንዲያድግ   ከፍተኛ ሚና መጫወቷንም የሚያረጋግጡት በርካቶች ናቸው፡፡

የተፈጥሮ ሀብቶቻችን እንዲሁም የመስህብ ሀብቶቻችን እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ፣ የክልሉ ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ሥነ ጽሑፍ  እንዲያድግ ያለማሰለስ ሠርታለች፡፡

የበኩር ጋዜጣ የዛሬው ግዙፍ ተቋም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) እንዲመሠረት እና በዕድገት ጎዳና እንዲራመድ ፋና ወጊ ሆና አገልግላለች፡፡ የበኩር መሥራቾች በፈተና ውስጥ ሆኖ ሥራ መጀመርን፣ ጀምሮም በችግሮች ሳይበገሩ ሥራን በጽናት መቀጠልን፣ ማሳደግን እና ለስኬት መብቃትን ፋና ወጊ ሆና ማስተማሯ  አሚኮ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች መረጃዎችን እና ማስታወቂያዎችን በመላው ዓለም ለሚገኙ አንባቢያን፣ አድማጮች እና ተመልካቾች  እያደረሰ ከሚገኝበት የዕድገት ማማ ላይ እንዲወጣ  መሠረት ሆና አገልግላለች፡፡

በኩር ፈተና ሆኖባት ከኖረው የሥርጭት ውሱንነት ወጥታ ዘመኑ ያፈራው ቴክኖሎጅ ይዞት በመጣው ዕድል በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለመሆን ብትችልም ቴክኖሎጂው ሌሎች የብዙኃን መገናኛ አማራጮችን ይዞ እንደመጣ እና ይህ ክስተት አንባቢያንን እንደሚሻማ መረዳት ያሻል፡፡ ይህን እውነታ ተረድቶም በዘርፉ ውስጥ ብርቱ ተፎካካሪ ብሎም ተመራጭ ሆኖ ለመዝለቅ  ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ ግድ ይላል፡፡

በኲር የታኅሳስ 7   30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here